ስጋት ያጠላበት የሃዋሳ ሃይቅ
ከአለት ጋር እየተጋጨ የሚመለሰው ውሃና ቁር ቁር የሚለው የእንቁራሪቶች ድምፅ ሀይቁን አጅበውታል፡፡ ወጀብም አልነበረውም፡፡ አልፎ አልፎ በውስጡ የበቀሉ ይታያሉ፡፡ ሀይቁ ዳርና ዳር የሰፈሩት ሌዊና ሀይሌ ሪዞርት ለሃዋሳ ሀይቅ ልዩ ድባብ ሆነውታል፡፡ በመብራትና በተለያዩ እፅዋት የደመቀውን የሪዞርቶቹን ድባብ ሀይቁም ተጋርቷቸዋል፡፡ ሀይቁም ለሪዞርቶቹ ልዩ ግርማ ሞገስ ሆኗቸዋል፡፡ ጀምበር መጥለቅ ስትጀምር በሀይቁ ላይ የሚኖረው እንቅስቃሴ አብሮ ይቀዘቅዛል፡፡ ጥንድ ጥንድ ሆነው የሚዝናኑ ፍቀረኛሞችንና ጎብኚዎችን ይዘው ቀኑን ሙሉ ሀይቁን ሲቀዝፉ የሚውሉ ጀልባዎችም ጥግጥጉን ይይዛሉ፡፡ በውሃ ግፊት ቦታቸውን እንዳይለቁም ከቃጫ በተሰራ ገመድ ከአለቶችና ከዛሆች ጋር ታስረዋል፡፡ ፍፁም ሰላም የሰፈነበትን ሃይቁን በተመስጦ የሚያዩና በዙሪያው የሚዝናኑ እዚህም እዚያም ይታያሉ፡፡ በስልካቸው ፎቶ የሚነሱም ብዙ ናቸው፡፡ ለአይን ያዝ ሲያደርግ ብዙ ደንበኞች አይገኙምና አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉ ደንበኞችን ቀድሞ ለመውሰድ የሚደረገው ሽሚያ ቀልብ ይስባል፡፡ በአዋሳ ፍቅር ሀይቅ ዙሪያ ያሉትን መዝናኛና ምግብ ቤቶች አልፈው ወደ ሀይቁ ከመጠጋትዎ ደንበኛ በሚሻሙ የጀልባ ካፒቴኖች ይከበባሉ፡፡ በየርቀቱ የሚያስከፍሉት ዋጋ ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ደንበኛው አንዱን እስኪመርጥ ዋጋቸውን ደጋግመው ይነግሩዎታል፡፡ የት መሄድ እንደሚፈልጉም በጥያቄ ያዋክቡዎታል፡፡ አንዱን እንደመረጡ ትተዎት ይበታተናሉ፡፡ ሌላ ደንበኛ መጠባበቅም ይጀምራሉ፡፡ ዋና ለማይችሉ ሰዎች በጀልባ መጓዝ የሚያስጨንቅ ስሜት ይፈጥራል፡፡ በተለይም በተፈጥሯቸው ውሀ ለሚፈሩ ሰዎች ጭንቀቱ ከባድ ነው፡፡ ሀዋሳ ደርሶ ሀይቁን በጀልባ ሳያቋርጡ መመለሱ ያስቆጫልና ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስ ጀልባው ውሀ ያስገባል?