በተመድ የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛ መንግሥት ለሕዝብ ፍላጎት ምላሽ እንዲሰጥ ጠየቁ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ኒኪ ሐሌ ሰኞ ጥቅምት 13 ቀን 2010 ባደረጉት ቆይታ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸው ታወቀ፡፡ በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ከሪፖርተር ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፣ አምባሳደር ሐሌ ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ የሚሰማውን መግለጽ፣ መንግሥትም ለሕዝብ ፍላጎት ምላሽ መስጠት እንዳለበት መጠየቃቸውን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ሁሉንም አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲፈጠርና ገንቢ ውይይቶች እንዲካሄዱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር መነጋገራቸው ተገልጿል፡፡ አምባሳደሯ የወጣቶች ድምፅ እንዲሰማ፣ ወጣቶች መጪውን ጊዜ ብሩህ ለማድረግ ሚና እንዳላቸው ጠቁመው የአፍሪካ መሪዎችም የዜጎቻቸውን መብቶች ማክበር እንዳለባቸው ማሳሰባቸው ታውቋል፡፡
አምባሳደሯ በትዊተር አካውንታቸው ላይ እንደገለጹት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለኢትዮጵያ፣ ኢጋድና ደቡብ ሱዳን፣ እንዲሁም በኮንጎ ስላሉ ወቅታዊ ጉዳዮች መወያየታቸውን ጽፈዋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ቀጣይነት ባለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት፣ በሰላምና በመረጋጋት ላይ መነጋገራቸውን የአሜሪካ ኤምባሲ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ቀረቤታ እንዳላቸው የሚነገርላቸው ሴናተር ጀምስ ኢንሆፍ ካደረጉት ጉብኝት አንድ ሳምንት በኋላ የመጣው የአምባሳደሯ ጉብኝት፣ በአኅጉራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡
ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያገኙት ሴናተር ኢንሆፍ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚታየው የፖለቲካ ውጥረት ላይ መነጋገራቸው ይታወሳል፡፡
የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከወጣ በኋላ በትልቅነቱ የመጀመርያው የሆነው የአምባሳደር ኒኪ ሐሌ አኅጉራዊ ጉብኝት፣ በዋናነት በአፍሪካ ውስጥ ስላለው ግጭትና የተፈጥሮ አደጋዎች ተጎጂ ለሆኑ ሰዎች እየተደረገ ስላለው ዕርዳታ ለመታዘብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ፣ በደቡብ ሱዳንና በኮንጎ የስድስት ቀናት ጉብኝት ፕሮግራም ይዘዋል፡፡
ከአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽነር ሚናታ ሳማቴ ጋር ተገናኝተው የተወያዩት አምባሳደር ሐሌ፣ ኅብረቱ በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮና በደቡብ ሱዳን ስላለው ሁኔታ ተነጋግረዋል፡፡
በተለይ ከደቡብ ሱዳን ጋር በተያያዘ አምባሳደሯ ከኮሚሽነሯ ጋር በመሆን ባወጡት መግለጫ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርን በነገር ወርፈዋል፡፡ አምባሳደር ሐሌ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የሚመሩት ሕዝብ በመቸገሩ ደንታ ቢስ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡  

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር