ስጋት ያጠላበት የሃዋሳ ሃይቅ

ከአለት ጋር እየተጋጨ የሚመለሰው ውሃና ቁር ቁር የሚለው የእንቁራሪቶች ድምፅ  ሀይቁን አጅበውታል፡፡ ወጀብም አልነበረውም፡፡ አልፎ አልፎ በውስጡ የበቀሉ ይታያሉ፡፡ ሀይቁ ዳርና ዳር የሰፈሩት ሌዊና ሀይሌ ሪዞርት ለሃዋሳ ሀይቅ ልዩ ድባብ ሆነውታል፡፡ በመብራትና በተለያዩ እፅዋት የደመቀውን የሪዞርቶቹን ድባብ ሀይቁም ተጋርቷቸዋል፡፡  ሀይቁም ለሪዞርቶቹ ልዩ ግርማ ሞገስ ሆኗቸዋል፡፡
ጀምበር መጥለቅ ስትጀምር በሀይቁ ላይ የሚኖረው እንቅስቃሴ አብሮ ይቀዘቅዛል፡፡ ጥንድ ጥንድ ሆነው የሚዝናኑ ፍቀረኛሞችንና ጎብኚዎችን ይዘው ቀኑን ሙሉ ሀይቁን ሲቀዝፉ የሚውሉ ጀልባዎችም ጥግጥጉን ይይዛሉ፡፡ በውሃ ግፊት ቦታቸውን እንዳይለቁም ከቃጫ በተሰራ ገመድ ከአለቶችና ከዛሆች ጋር ታስረዋል፡፡ ፍፁም ሰላም የሰፈነበትን ሃይቁን በተመስጦ የሚያዩና በዙሪያው የሚዝናኑ እዚህም እዚያም ይታያሉ፡፡ በስልካቸው ፎቶ የሚነሱም ብዙ ናቸው፡፡
ለአይን ያዝ ሲያደርግ ብዙ ደንበኞች አይገኙምና አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉ ደንበኞችን ቀድሞ ለመውሰድ የሚደረገው ሽሚያ ቀልብ ይስባል፡፡ በአዋሳ ፍቅር ሀይቅ ዙሪያ ያሉትን መዝናኛና ምግብ ቤቶች አልፈው ወደ ሀይቁ ከመጠጋትዎ ደንበኛ በሚሻሙ የጀልባ ካፒቴኖች ይከበባሉ፡፡ በየርቀቱ የሚያስከፍሉት ዋጋ ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ደንበኛው አንዱን እስኪመርጥ ዋጋቸውን ደጋግመው ይነግሩዎታል፡፡ የት መሄድ እንደሚፈልጉም በጥያቄ ያዋክቡዎታል፡፡ አንዱን እንደመረጡ ትተዎት ይበታተናሉ፡፡ ሌላ ደንበኛ መጠባበቅም ይጀምራሉ፡፡
ዋና ለማይችሉ ሰዎች በጀልባ መጓዝ የሚያስጨንቅ ስሜት ይፈጥራል፡፡ በተለይም በተፈጥሯቸው ውሀ ለሚፈሩ ሰዎች ጭንቀቱ ከባድ ነው፡፡
ሀዋሳ ደርሶ ሀይቁን በጀልባ ሳያቋርጡ መመለሱ ያስቆጫልና ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስ ጀልባው ውሀ ያስገባል? አያስገባም? የሚለውን በፍርሀት እየተንቀጠቀጥን፣ የታችኛውን የጀልባውን ክፍል በእግራችን መታ መታ እያደረግን ፈተሸን፡፡ ከዚያም የጀልባዋ ካፒቴን አብነት ትርዳቸው ሞተሩን አስነሳና ጉዞ ጀመርን፡፡
ወደ ጥቁር አረንጓዴ በሚያደላው የሃዋሳ ሀይቅ  የተለያዩ አእዋፋት፣ ጉማሬና ዘንዶ መኖሩን አብነት ሲነግረን ደነገጥን፡፡ ጉማሬና ዘንዶ ጀልባ ላይ አደጋ አድርሶ ያውቅ እንደሆነም ጠየቅነው፡፡ ሁኔታችንን አይቶ ሊያረጋጋን ፈልጎ ይሁን የምሩን እርግጠኛ መሆን ባንችልም አጋጥሞት እንደማያውቅ ነገረን፡፡ ይህንን መስማታችን እፎይታ ሰጠን፡፡
ከመካከላችን አንዱ በአንድ ወቅት የሰርግ ስነስርአታቸውን በጀልባ እየተጓዙ ሲያከብሩት የነበሩ ሙሽሮች አደጋ አጋጥሟቸው እንደነበር አስታወሰን፡፡ በጭንቀት እንደተዋጥን ምላሽ ፍለጋ ወደ አብነት ዘወር አልን፡፡ አደጋው የደረሰው በሌላ ሀይቅ እንደሆነ ነገረን፡፡ ሌላው ቢቀር በሀይቁ አሳዛኝ አጋጥሚ ተከስቶ አለማወቁን ሲነግረን ጥቂትም ቢሆን እፎይታ አልን፡፡
የጀልባ ካፒቴን ለመሆን ዋና መቻል ወሳኝ መሆኑን የሚናገረው አብነት፣ ወደዚህ ስራ የገባው በልጅነት እድሜው እንደሆነ ይናገራል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ካጋጠሙት ቀላል አደጋዎች ውጪ የከፋ ችግር አጋጥሞት እንደማያውቅ አወሳን፡፡ አስከፊው ነገር በአጋጣሚ የሚፈጠር አደጋ ሳይሆን ታስቦበት የሚከሰትና አንዳንድ በህይወታቸው ተስፋ የቆረጡ ራሳቸውን ለማጥፋት የሚወስዱት እርምጃ እንደሆነ ነገረን፡፡
እንደ አብነት ገለፃ፣ ከጀልባው ወደ ሀይቁ በመወርወር ራሳቸውን የማጥፋጥ ሙከራ የሚያደርጉ ሰዎች ያጋጥማሉ፡፡ እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ካፒቴኑ ጀልባውን አቁሞ ወደ ውሃ ውስጥ በመጥለቅ ሕይወት የማዳን ስራ ይሰራል፡፡ ግለሰቡ ዋና የማይችል ከሆነ ግን ህይወት የማትረፉን ስራ ከባድ ያደርገዋል፡፡ በሞትና በህይወት መካከል ሆኖ ስለሚፈራገጥ ህይወቱን ለማዳን ሲል ሊያድነው የገባውን ሰው ሳይቀር ጉዳት ሊያደርስበት ይችላል፡፡  
በሀይቁ ውስጥ ከሚኖሩ የተለያዩ እንስሳት መካከል ጉማሬ የተለየ ባህሪ እንዳለው አብነት ይናገራል፡፡ በአንድም ይሁን በሌላ ጉማሬዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ የሀይቁን ህልውና ላለመጉዳት የራሳቸውን ሚና የሚጫወቱ ያስመስላቸዋል፡፡ በሀይቁ ውስጥ የሚኖሩ ጉማሬዎች በሚቆስሉበት ጊዜ ወደ ሀይቁ ዳር ይወጣሉ፡፡ ይህም ሀይቁን ከቁስላቸው በሚወጡ ባክቴሪያዎች እንዳይበከል ያደርገዋል፡፡ ሲወልዱም ባልና ሚስቱ ብቻ ከመንጋው ተነጥላው ወደ ጥግ በመውጣት ነው፡፡ ሲሞቱም እንደዚሁ ወደ ዳር ወጥተው በመሆኑ ሀይቁ ውስጥ ሳይበሰብሱ አውጥቶ ሌላ ቦታ ለመጣል ያመቻል፡፡
ለሀይቁ መበከል ምክንያት እየሆኑ ያሉት ከየቤቱ የሚወጡ ፍሳሾች  ወደ ሀይቁ እንዲገቡ መደረጉ ነው፡፡ የሚሰነፍጥ ጠረን እንዲኖረውም አድርጓል፡፡ ‹‹ከኢንዱስትሪዎች፣ ከጋራጅ፣ ከሆቴል፣ ከህክም ተቋማትና ከየመኖሪያ ቤቶች የሚለቀቁ ፍሳሾች ሀይቁን እየበከሉት ይገኛሉ›› ያሉት በአዋሳ ከተማ የአካባቢ ጥበቃና የስራ ሂደት አስተባባሪው አቶ ደሳለኝ አለማየሁ ናቸው፡፡
የብዝሃ ሕይወት መጎዳትና የደለል ክምችትም  ሌላው በሀይቁ የተጋረጠ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም ‹‹ይህንን ያህል ብሎ ለማስቀመጥ ያስቸግራል እንጂ በሀይቁ ያለው የደለል ክምችት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው›› ብለዋል፡፡
እነዚህ ችግሮች በሀዋሳ ሀይቅ ላይ ብቻ የተወሰኑ ሳይሆኑ የሌሎቹም ሀይቆችና ግድቦች ችግር ነው፡፡ ከአያያዝና ከጥንቃቄ ችግር አንፃር ሀይቆች በደለልና በሌሎችም ችግሮች የመፈተናቸው ነገር መሰማት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በዚህ ረገድ የሀሮማያ ሀይቅ አይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡ ሀይቁ በዙሪያው ላሉት ለሀረር፣ ለሀረማያና ለአወዳይ ነዋሪዎች ዋነኛ የውሃ አቅርቦት ምንጭ ነበር፡፡
 በዙሪያው የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣትና ተገቢ ያልሆነ የአስተራረስ ዘዴ መከተል አካባቢውን ለአፈር መሸርሸር እንዳጋለጠውና የተሸረሸረውም አፈር ወደ ሀይቁ እንዲገባ ማድረጉን፣ ጤና አላምረው የተባሉ አንድ አጥኚ ‹‹ኤስቲሜሽን ኦፍ ግራወንድ ወተር ሪቻርጅ ኢን ዘ ሌክ ሀረማያ ወተር ሼድ›› በሚል እ.አ.አ. በ2011 ያወጡት ፅሁፍ ያሳያል፡፡ በጥናቱ መሰረት ሀይቁ አ.ኤ.አ በ1980ዎቹ ጥልቀቱ 8 ሜትር፣ ስፋቱ ደግሞ 4.2 ኪሎ ሜትር ነበር፡፡ የአያያዝ ችግርና ተገቢው ትኩረት አለመሰጠቱ ግን ሀይቁ አ.ኤ.አ በ2004 እንዲደርቅ ምክንያት ሆኗል፡፡
በአገሪቱ ከሀያ የሚበልጡ ትልልቅና አነስተኛ ሀይቆች ይገኛሉ፡፡ ጣና፣ ሃዋሳ፣ ላንጋኖ፣ አባያ፣ ጫሞ፣ ቢሾፍቱ፣ ዝዋይ፣ አቢያታ፣ ሻላ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ሀይቆች ለብዝሀ ህይወት ውድመት መጋረጡን በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሪፖርተር ባለፈው አመት ጥር ወር ላይ ባወጣው አንድ እትሙም የስምጥ ሸለቆ የአሳ ሀብት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡  
በዘገባው በስምጥ ሸለቆ አካባቢ በሚገኙ ሐይቆች የሚመረተው የዓሳ መጠንና ዓሳው የሚመረትበት አግባብ በዓሳ ሀብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በሕገወጥ የማጥመጃ መሣሪያዎች ማጥመድና ከሚፈቀደው መጠን በላይ ማስገር የችግሩ ዋነኛ መንስዔዎች ናቸው፡፡ ‹‹መመረት ያለበት ዓሳ ለምግብነት የደረሰ መሆን አለበት፡፡ ነገር ግን አስጋሪዎቹ ከመመርያና ከሚፈቀደው ውጪ ማንኛውንም ዓሳ በዘፈቀደ እያሰገሩ ይገኛሉ፡፡ ለምግብነት የደረሱትን ብቻ ማስገር ሲገባቸው ጫጩቶቹንም ሲያሰግሩ ይታያሉ፡፡ ይህም የምርቱን ቀጣይነት አደጋ ላይ ይጥለዋል፤›› በማለት ነበር የዓሳ ሀብት ልማት ባለሙያው አቶ ቡልቡል ረጋሳ በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚታየው የዓሳ ምርት ማሽቆልቆሉን የተናገሩት፡፡
የችግሩ ተጠቂ ከሆኑት መካከል የሆነው ዝዋይ ሐይቅ በዓመት ማምረት የሚችለው የዓሳ መጠን 3,100 ኩንታል ሲሆን፣ አስጋሪዎች ከመጠን በላይ በማስገር የማምረት አቅሙ እንዲሁም ቀጣይነቱ ላይ አሉታዊ ጫና መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡ አገሪቱ በዓሳ ሀብት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች አለመሆኑን፣ የማምረት አቅሟም በዓመት 185,000 ኩንታል እንደሆነና እየተገኘ ያለው ግን 12,000 ኩንታል ምርት ብቻ መሆኑንም አክለዋል፡፡  
በአካባቢው የሚገኙ ዓሳ አስጋሪዎች በልማድ ላይ ተንተርሰው እንደሚሠሩ የገለጹት ባለሙያው፣ የኦሮሚያ ክልል የዓሳ ሀብቱን ለማስከበር ያወጣውን መመርያ ነገሬ እንደማይሉትም ገልጸው ነበር፡፡ በሀይቁ ያለው የደለል ክምችትም ሌላው ትልቅ ችግር እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ለጉዳዩ አፋጣኝ መፍትሄ ካልተሰጠውም እንደሀሮማያ ሀይቅ ሊደርቅ እንደሚችል ስጋት አለ፡፡
ከሰሞኑ በጣና ሀይቅ ላይ የደረሰው የእንቦጭ አረም ወረርሽኝም የብዙሀኑን ቀልብ የሳበ ክስተት ነው፡፡ በአፍሪካ ከሚገኙ ትልልቅ ሀይቆች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው ጣና ሀይቅ 3111 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ የያዘ ነው፡፡ 50 በመቶ ለሚሆነው የአገሪቱ የውሃ አቅርቦት ምንጭ መሆኑም ይነገራል፡፡ ኑሯቸውን በዙሪያው ለመሰረቱ ሚሊዮኖችም ቤዛ ነው፡፡ ከ30 በላይ ታሪካዊ ገዳማትና ደሴቶችም መገኛ ነው፡፡ ከዚህ ሲያልፍም ለአባይ ወንዝ ገባር ነው፡፡ በአጠቃላይ ጣና ሀይቅ በዙሪያው ላሉ ህልውናቸው፣ ለመላው የኢትዮጵያን ደግሞ ኩራት ነው፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተንሰራፋና በሀይቁ ላይ ያለውን ይዞታ እያሰፋ የመጣው እንቦጭ አረም ግን ስጋት ሆኖበታል፡፡ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በሀይቁ ላይ መከሰቱ የሚነገርለት እንቦጭ፣ በሀይቁ ላይ ያለውን ይዞታ ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ ካደረሰ ውሎ አድሯል፡፡ ታዋቂው የባህል ሙዚቃ ተጫዋች ይሁኔ በላይም ሆበል ታደጉኝ ብሎ
ሆበል ጣና ጠርቶኝ
ሆበል የማልቀርበት
ሆበል ደቦ አለብኝ
ወገን ቶሎና ሆበልና እንገናኝ ጣና
ስጋት ያጠላባቸው ሀይቆችወገን ቶሎና እንድረስ ለጣና; በማለት ጉዳዩ አገራዊ ትኩረትና የብዙዎችን ርብርብ  የሚጠይቅ መሆኑን በዜማ ገልጿል፡፡ 
ከ50 ሺሕ ሔክታር በላይ ስፋት ያለው የሀይቁ ክፍል፣ በአረም መሸፈኑ አፋጣኝ ምላሽ ካልተሰጠው በቅርብ ዓመታት ሐይቁ ሊደርቅ እንደሚችል፣ ከመድረቅ የሚያድነው እንደማይኖር ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው፡፡ ሐይቁ ሙሉ በሙሉ በመድረቅ የአገሪቱን ገጽታ ከማበላሸት ባለፈ፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት እንደሚያስከትልም ተገልጿል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ከጎንደርና ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር ውይይት እያደርግን እንገኛለን ያሉት የባህርዳር ከተማ አስተዳዳር የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት መምርያ ኃላፊ አቶ በሰላም ይመኑ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ከተከሰተ ዓመታት ያስቆጠረው የእምቦጭ አረም ከዚህ ቀደም በአካባቢው ኅብረተሰብ አማካይነት ከሐይቁ ውስጥ እየተመነጠረ እንዲወጣ ተደርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ችግሩ በሳይንሳዊ መንገድ እንጂ በባህላዊ መንገድ የሚፈታ ባለመሆኑ በሳይንሳዊ መንገድ ለመፍታት ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር ጥናት በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡
ከአረሙ ባሻገር በጣና ሐይቅ ዳርቻ ከሚገኙ ሆቴሎች ሌሎች ተቋማት የሚወጣው ቆሻሻና ፍሳሽ ወደ ሀይቁ እንዲቀላቀል የሚደረግበት ሁኔታም በደለል እንዲሞላና ውሃው እንዲበከል ሌላው ምክንያት ነው፡፡  
ሀይቆች የበርካቶች መተዳደሪያ ለሆነው የዓሳ ሀብት ምንጭና የመዝናኛ ስፍራ ከመሆናቸውም በሻገር ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ከማንም የተደበቀ አይደለም፡፡ ይሁንና ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ በሆኑ መንገዶች ለችግሮች እየተጋለጡ ናቸው፡፡ የአገሪቱ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ሀይቆች የኢትዮጵያ ሀይቆች ለደለል ክምችት እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል፡፡
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የአገሪቱ የመልክ አምድር አቀማመጥ 110 ሜትር ከባህር ጠለል በታችና 4600 ሜትር ከበህር ጠለል በላይ መሆኑ፣ ለከፍተኛ የአፈር መሸርሸር ችግር እንድትጋለጥ አድርጓታል፡፡  የአካባቢ ማኔጅመንትና አናሊስስ ባለሙያው አቶ ጌትነት ወርቁ እንደሚሉት፣ ተራራማ መልክዓ ምድር ያላት አገሪቱ በርካታ ወንዞች አሏት፡፡ ወንዞቹ በፍጥነት የሚሄዱ እንዲሁም ከተራራማ ቦታዎች በከፍተኛ ኃይል የሚወረወሩ ናቸው፡፡ ይህም የታችኛው የመሬት ክፍል እንዲቦረቦርና አፈር እንዲታጠብ የሚያደርግ ነው፡፡ በፍጥነት የሚጓዙት ወንዞችም ተሸክመው የሚወስዱት አፈር ሀይቆችና ግድቦችን የሚሞላና ያለ ዕድሜያቸው እንዲጠፉ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህም ልማትን ከማደናቀፍ ባሻገር መጪው ትውልድ የሚገባውን ጥቅም እንዳያገኝ ያደርጋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር