በኦሮሚያ ክልል በአንድ ሳምንት ውስጥ 30 ሰዎች ሞተዋል

  • 240 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል
በኦሮሚያ ክልል በአንድ ሳምንት ውስጥ 30 ሰዎች ሞተዋልበኦሮሚያ ክልል በቡኖ በደሌ ዞንና በአምቦ ከተማ በአንድ ሳምንት ውስጥ 30 ሰዎች ሲሞቱ፣ 37 ያህል ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
በቡኖ በደሌ ዞን በገቺ፣ በደሌ፣ ጮራና ዴጋ ወረዳዎች ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ግጭት መቀስቀሱ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህ ግጭት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 20 መድረሱ ተገልጿል፡፡
በግጭቱ ምክንያት ወደ ሥፍራው አቅንተው የነበሩት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ወቅት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ስለነበሩ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ችሏል፡፡
በወቅቱ 14 ሰዎች መሞታቸውን፣ ከሃምሳ በላይ ቤቶች መቃጠላቸውን፣ በ14 ሰዎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ 1,500 መፈናቀላቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡ አሁን በደረሰው መረጃ መሠረት 20 ሰዎች ሲሞቱ፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 14 ቢሆኑም፣ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ግን ከሦስት ሺሕ በላይ እንደሆነ አቶ ንጉሡ ገልጸዋል፡፡
አቶ ንጉሡ እንዳሉት ግጭቱ በተከሰተበት ዞን በአብዛኛው ሕይወታቸውን ያጡት የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ናቸው፡፡ የአማራ፣ የትግራይና የደቡብ ክልሎች ተወላጆችም ሕይወታቸውን እንዳጡ አክለዋል፡፡
የዚህ ግጭት ዋነኛ ምክንያት ምንድነው ተብሎ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ንጉሡ፣ ‹‹በኦሮሚያ ክልል ኅብረተሰቡ ቅሬታውን በሠልፍ እንደሚገልጽ እያስተዋልን ነው፡፡ ይህም አካባቢ ሠልፍ ከሚካሄድባቸው መካከል አንዱ እንደሆነ አይተናል፡፡ ሠልፉም በሰላማዊ ሁኔታ እንደተጠናቀቀ ሰምተናል፡፡ ነገር ግን ሠልፉ ከተካሄደ በኋላ ወደ ዘረፋና ብጥብጥ ነው ያመራው፡፡ ሕዝቡ ሠልፉን በሰላም አጠናቆ ከሄደ በኋላ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ብሔሮችን ለማጋጨት ዘረፋ ተካሂዷል፤›› ብለው፣ ‹‹የተዘረፉ ከሁሉም ወገኖች አሉ፡፡ ግን የተወሰኑ ብሔሮች ላይ የተደረገ ጥቃት ለማስመሰልና ለይቶም ለማጥቃትና ብሔሮች ለማጋጨት ሙከራ ተደርጓል፤›› ብለዋል፡፡
በ1977 ዓ.ም. በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ረሃብ ከአማራና ከትግራይ ክልሎች እዚህ አካባቢ የሠፈሩ ዜጎች እንዳሉ አስታውሰው፣ ‹‹መጤና ነዋሪ ብሎ በመከፋፈል ማጋጨት እንደ መሣሪያ አድርጎ የመጠቀም ስልት ነበር፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ግን ግጭቱ የሕዝቡ አይደለም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
በዚህ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰው ግጭት የበርካቶች ሕይወት እንደጠፋ፣ ቤቶች እንደተቃጠሉና ነዋሪዎች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ ይታወቃል፡፡ ከአማራ ክልል፣ ከፌዴራል መንግሥትና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች ረቡዕ ጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ሥፍራው መሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡ በበደሌ ከተማ ከሕዝቡ ጋር በተደረገው ውይይትም ግጭቱ የአካባቢውን ሕዝብ የማይወክል መሆኑን ነዋሪዎች እንደተናገሩ አቶ ንጉሡ አስረድተዋል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ኃላፊነት መውሰዳቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተሽከርካሪ ጭምር በመታገዝ ከሌሎች ዞኖችና ክልሎች አቆራርጠው በመምጣት ጉዳት ለማድረስ እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላት እንዳሉ በመረጋገጡ፣ ከሕዝቡ ጋር በመሆን ለመመከት ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡
የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ላይ መንግሥት እየሠራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ንጉሡ፣ ከሁለት ሺሕ በላይ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው መመለስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
‹‹በእኛ በኩል የክልላችን መንግሥት ይህንን ኃላፊነት ሰጥቶ ሲልከን ወገኖቻችን ያሉበትን ሁኔታ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በመመርመር ከሕዝቡ ጋር መሆናችንን ለማሳየትና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በማንኛውም ረገድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ የምንደግፍ መሆናችንንና አብሮነታችንን ለማሳየት ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹ቀሪው ጉዳይ ዳግመኛ ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላት በመኖራቸው፣ ኅበረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ ሰላሙን እንዲጠብቅ፣ ውህደቱን እንዲያጠናክር የማድረግ፣  የተያዙና የሚጠረጠሩ ወገኖችን በሕግ ጥላ ሥር የማዋል ነው፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፣ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር 20 መድረሱን አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ ድርጊት የተሳተፉ ከ240 በላይ ግለሰቦች በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በአምቦ ከተማ ሐሙስ ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የአሥር ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡
የአምቦ ከተማ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ጋዲሳ ደሳለኝ ዓርብ ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ሕገወጥ ስኳር እየተዘዋወረ ነው ተብሎ በተነሳው ግጭት የአሥር ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ‹‹የሁለት ሰዎች አስክሬን ወደ ክሊኒክም ሆነ ሆስፒታል ሳይሄድ ቤተሰቦቻቸው እንደወሰዱ እማኞች ቢገልጹም፣ ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ አልተቻለም፤›› ብለዋል፡፡
የዚህ ግጭት ዋነኛ ምክንያት በአምቦ ከተማ ስኳር ከ60 ብር በላይ እየተሸጠ ለምንድነው እዚህ ክልል ውስጥ ተመርቶ ወደ አዲስ አበባ የሚሄደው የሚል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ከረቡዕ ጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ወጣቶች ከጉደር እስከ ጊንጪ ድረስ መንገዱን ዘግተው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ የመከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው ሲመጣ ተኩስ እንደተጀመረ ጠቁመዋል፡፡
‹‹ዶ/ር ከበደ የሚባሉ የጤና ባለሙያ እንደነገሩኝ 16 የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ክሊኒካቸው ሄደው፣ ከእነዚህ መካከል 15 በጥይት፣ አንድ ደግሞ በድንጋይ የተመቱ መሆናቸውን አረጋግጠውልኛል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን አንዱ ግንባሩ ላይ፣ ሌላኛው ደግሞ ልቡ ላይ በጥይት የተመቱ መሆናቸውን ነግረውኛል፤›› በማለት አቶ ጋዲሳ ተናግረዋል፡፡
እስከ ዓርብ ዕለት 23 የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በአምቦ ሆስፒታልና በግል ክሊኒኮች ዕርዳታ እያገኙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ‹‹እነዚህን ሰዎች የመከላከያ ሠራዊት ነው የገደላቸው፤›› ያሉት አቶ ጋዲሳ፣ ሠራዊቱ የመጣበት አቅጣጫም ከጉደርና ከአዲስ አበባ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የከተማዋ የፀጥታና የፖሊስ አካላት የመከላከያ ኃይል ከመምጣቱ በፊት ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ነበር በማለት አቶ ጋዲሳ ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ ሦስት ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውን የተናገሩት አቶ ጋዲሳ፣ አንደኛው ንብረትነቱ የዳንጎቴ ሲሚንቶ፣ ሁለተኛው የኢት ቴሌኮም፣ ሦስተኛው ደግሞ የማን እንደሆነ አልታወቀም ብለዋል፡፡
የዘንድሮ የኢሬቻ በዓል በተከበረ ማግሥት በኦሮሚያ ክልል በተካሄዱ የተቃውሞ ሠልፎች፣ የ38 ዜጎች ሕይወት አልፏል፡፡ ባለፈው ሳምንት በጫንጮና በገርባ ጉራቻ ከተሞች በተደረጉ የተቃውሞ ሠልፎችም በርካታ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸው ይታወሳል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በአምቦ የነበረውን ግጭት አስመልክቶ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ክልሉን የሁከት አውድማ ማድረግ የሚፈልጉ አካላት ባሠራጩት የሐሰት መረጃ የተፈጠረ ክስተት ነው፡፡ እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ ይህን ድርጊት የፈጸሙ አካላት፣ አዲሱ የኦሮሚያ ክልል አመራር የጀመራቸውን ለውጦች ከግብ እንዳያደርስ ያለሙ ናቸው፡፡ እነዚህን አካላትም የክልሉ መንግሥት በቁጥጥር ሥር አውሎ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል ብለዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ ሁከት የሚቀሰቅሱ አካላትን መከተል እንደሌለበት፣ የእነሱ ዓላማ ክልሉን ትርምስ ውስጥ መክተት ስለሆነ ካላስፈላጊ ድርጊቶች እንዲቆጠብ ጥሪ አድርገዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር