በኦሮሚያ ክልል በአንድ ሳምንት ውስጥ 30 ሰዎች ሞተዋል
240 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል በኦሮሚያ ክልል በቡኖ በደሌ ዞንና በአምቦ ከተማ በአንድ ሳምንት ውስጥ 30 ሰዎች ሲሞቱ፣ 37 ያህል ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቡኖ በደሌ ዞን በገቺ፣ በደሌ፣ ጮራና ዴጋ ወረዳዎች ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ግጭት መቀስቀሱ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህ ግጭት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 20 መድረሱ ተገልጿል፡፡ በግጭቱ ምክንያት ወደ ሥፍራው አቅንተው የነበሩት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ጥቅምት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ወቅት የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ስለነበሩ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር ችሏል፡፡ በወቅቱ 14 ሰዎች መሞታቸውን፣ ከሃምሳ በላይ ቤቶች መቃጠላቸውን፣ በ14 ሰዎች ላይ ከፍተኛ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ 1,500 መፈናቀላቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡ አሁን በደረሰው መረጃ መሠረት 20 ሰዎች ሲሞቱ፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 14 ቢሆኑም፣ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ግን ከሦስት ሺሕ በላይ እንደሆነ አቶ ንጉሡ ገልጸዋል፡፡ አቶ ንጉሡ እንዳሉት ግጭቱ በተከሰተበት ዞን በአብዛኛው ሕይወታቸውን ያጡት የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ናቸው፡፡ የአማራ፣ የትግራይና የደቡብ ክልሎች ተወላጆችም ሕይወታቸውን እንዳጡ አክለዋል፡፡ የዚህ ግጭት ዋነኛ ምክንያት ምንድነው ተብሎ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ንጉሡ፣ ‹‹በኦሮሚያ ክልል ኅብረተሰቡ ቅሬታውን በሠልፍ እንደሚገልጽ እያስተዋልን ነው፡፡ ይህም አካባቢ ሠልፍ ከሚካሄድባቸው መካከል አንዱ እንደሆነ አይተናል፡፡ ሠልፉም በሰላማዊ ሁኔታ እንደተጠናቀቀ ሰምተናል፡፡ ነገር ግን ሠልፉ ከተካሄደ በኋላ ወደ ዘረፋና ብጥብጥ ነው ያመራው፡፡ ሕዝቡ ሠልፉን በሰላም