በሲዳማ ክልል ከ489 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ሊገነቡ ነው



በሲዳማ ክልል ሁለት ወረዳዎች ከ489 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ሊገነቡ መሆኑ ተገለጸ።

ለፕሮጀክቶቹ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ የመሰረተ ድንጋይ ተቀምጧል።

በዚህ ወቅት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው እንደገለጹት፤ የአንድ ቋት የመጠጥ ውሃና ሳንቴሽን ፕሮግራም አካል በሆነው በዋን ዋሽ ፕሮግራም በአገሪቱ የተለያዩ ወረዳዎችና ከተሞች የሚከናወኑ የውሃ ፕሮጀክቶች ይኖራሉ።

ዛሬ በሲዳማ ክልል ሁለት ወረዳዎች መሰረት ድንጋይ የተቀመጠላቸው የውሃ ፕሮጀክቶች በዋን ዋሽ እና በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮግራሞች አማካይነት የሚከናውኑ መሆኑን ተናግረዋል።

ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ ከ489 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን አስታውቀዋል።

የውሃ ፕሮጀክቶቹ 49 የሚደርሱ የውሃ ቦኖዎች፣ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች፣ የእንስሳት ውሃ ማጠጫዎችን እንዲሁም የጤናና ትምህርት ተቋማትን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ግንባታዎችን እንደሚያካትቱ አብራርተዋል።

የሲዳማ ክልል ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ከበደ ጋኖሌ በበኩላቸው፤ በሃዋሳ ዙሪያና ቦርቻ ወረዳዎች የሚገነቡት የውሃ ፕሮጀክቶች ከ60 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የነበረውን ከፍተኛ የውሃ ችግር የሚያቃልል መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለቱንም ፕሮጀክቶች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አቶ ፍሬው ፈለቀና አቶ አለሙ ሳና፤ የውሃ ችግራቸውን ለማቃለል የፌደራልና የክልሉ መንግስት ላደረጉት ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

የውሃ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።(ኢዜአ)

Comments

Popular posts from this blog

Israel Eshetu back to his childhood club

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት