የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

የለበሰው ያደፈ ቁምጣና ሹራብ ከቅዝቃዜው አላዳነውም፡፡ ካፊያው ልብሱን አርሶታል፡፡ ሽው እያለ ከሐይቁ የሚነሳው ነፋስ የሚፈጥረው ቅዝቃዜ ያንቀጠቅጠዋል፡፡ የተጫማው ያረጀ ሲሊፐር እግሩን ከምንም አላዳነውም፡፡ በባዶ እግሩ የሚራመድ ያህል ጨቅይቷል፡፡ ተደባዳቢ ይመስል ፊቱ የተሞነጫጨረ ነው፡፡ ገና 12 ዓመቱ ቢሆንም፣ ቁመናው እንደ ትልቅ ሰው ግዙፍ ነው፡፡
የሚለብሰውን እንደ ልቡ ባያገኝም፣ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ቤሳቢስቲን የሌላቸው ወላጆቹን አያስቸግርም፡፡ ከቤተሰቦቹ ጋር ከሚኖሩበት ታቦር ተራራ ጀርባ ወዳለው ሐዋሳ ሐይቅ ከወረደ እንኳንስ የራሱን የቤተሰቦቹንም የዕለት ጉርስ የሚሸፍንበት ገንዘብ አያጣም፡፡
የአስጎብኚነት ዕውቀት፣ ከሐይቁም ውስጥ ዓሳ የሚያጠምድበት መረብም ሆነ ፈቃድ የለውም፡፡ ሙሉቀን (ስሙ ተቀይሯል) እና ጓደኞቹ ሐይቁን ለመጎብኘት የሚሄዱ ጎብኚዎች በካሜራቸው ጥሩ ፎቶ እንዲያስቀሩ ድባቡን የማሳመር ሥራ ይሠራሉ፡፡ ካሜራውን ይዞ ቁጭ ብድግ እያለ ጥሩ ፎቶ ለማንሳት ጥረት የሚያደርግ ሲያዩ፣ ቆርጠው የያዙትን የዓሳ ሥጋ ይዘው ጠጋ ጠጋ ይላሉ፡፡ ቁርጥራጩን የዓሳ ሥጋ ምግብ ለሚቀሙት አባኮዳዎች ሻሞ ይላሉ፡፡ የተወረወረላቸውን ቀድመው ለመቅለብ አባኮዳዎቹ ክንፋቸውን እየመቱ ወደ ላይ ብድግ ይላሉ፡፡ የናሽናል ጆግሪፊ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ያነሱት ዓይነት ፎቶዎች ሳያስቡት ያነሳሉ፡፡ በሁኔታው ተደስተው ደጋግመው ድንቅ ፎቶዎችን ለመውሰድ ሲዘጋጁ እነ ሙሉቀንም አጀንዳቸውን ይፋ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡
የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት
አቶ ዳዊት አብርሃም

‹‹አንዱን ዓሳ በአሥር ብር ገዝቼ ነው እንዲህ የማዘጋጀው፤›› በማለት በቅድሚያ  መረጃ ይሰጣሉ፡፡ ለቀጣዩ ዜና በዚህ መልኩ እንዲዘጋጁ ካደረጉ በኋላ፣ ሌሎች ሰዎች መቶም ሁለት መቶም ብር እንደሚሰጧቸው ቀለል አድርገው ይገልጻሉ፡፡
ዳርዳርታቸው ይገባዎትና እጅዎን ወደ ኪስ ሲያስገቡ፣ በሌሎች የተለዩ ተሰጥኦ አለን በሚሉ ልጆች ይሳባሉ፡፡ ማየት መፈለግ አለመፈለግዎን የሚጠይቅ የለም፡፡ ከየት እንደመጣ ያላወቁት ልጅ ተወንጭፎ ከተፍ ይላል፡፡ ፎቶ እንዲያነሱ ያግዛል፡፡ ወይም ጠብ እርግፍ ብሎ ይደንሳል፡፡ ሁኔታው እስኪገባዎ አብረው ሊጨፍሩ፣ ሊዘፍኑ ይችላሉ፡፡ ከዚያ ግን ያሎትን መክፈል ነው፡፡ ሙሉ ቀን ምርጥ የፎቶ ድባብ ፈጥሮ እስከ 200 ብር ሲከፈለው፣ ጓደኛው ሰሎሞን (ስሙ ተቀይሯል) ደግሞ በአንዴ እስከ አንድ ሺሕ ብር ያገኛል፡፡
የለበሰው ቱታ አጥሮታል፡፡ ‹‹12 ዓመቴ ነው››፣ ቢልም ከዚያ የሚያንስ ይመስላል፡፡ ከፊቱ ኑሮ እንዳልተመቸው ይመሰክራል፡፡ በቅዝቃዜው ቀጭ ይዞታል፡፡ አፍንጫውም ረጥቧል፡፡ እንደ ሙሉቀን ሁሉ እሱም ይንቀጠቀጣል፡፡
የሦስተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፣ ከትምህርት ቤት መልስ ቀጥታ ወደ ሐዋሳ ሐይቅ ፈትለክ ይላል፡፡ ገና ከርቀት እንግዳ ሲመለከት፣ ጠጋ ብሎ መደነስ ይጀምሯል፡፡ የሰሎሞን ቅጽል ስም ሻኪራ ነው፡፡ ሻኪራ ያሉት የሻኪራን ሙዚቃ እንደ እሷ መቀመጫውን እያወዛወዘ ስለሚጫወት ነው፡፡ በእኩዮቹ ዘንድ ዝና ያተረፈለትን የሻኪራን ሙዚቃ አማርኛም፣ እንግሊዝኛም ቀላቅሎ ይዘፍናል፡፡ በተለይ አርቲስቷ እ.ኤ.አ. በ2010 ደቡብ አፍሪካ ዓለም ዋንጫን ስታዘጋጅ በመክፈቻው ያቀነቀነችውን ዋካ ዋካ የተባለውን ሙዚቃዋን ጠንቅቆ የሚያውቅ ስለሚመስለው፤ እሱም ጓደኞቹም ይመርጡታል፡፡ ‹‹ታሚናሚና›› እያለ ሙዚቃውን ሲጫወት እንደሷ አስመስሎ ለመደነስ ይሞክራል፡፡
የሚያስቸግሩትን ቃላት እንደፈለገ እየገደፈ ይዘፍናል፡፡ ሙዚቃውን እየተጫወተ ‹‹ኮንጎ ጫማሽን አድርገሽ›› የሚል ከየት እንደመጣ ያልታወቀ ሐረግ ጨምሯል፡፡ ብዙዎች ግን ልብ አላሉትም፣ ጭፈራውን ቀጠለ፡፡
የሰሎሞን አካላዊ ሁኔታ ቢያሳዝንም ልጅነቱና ልበ ሙሉነቱ ደስ ይላል፡፡ እንዳሻው እየተንቀሳቀሰ አፉ ያመጣለትንና የመሰለውን ሲዘፍንም፣ በዙሪያው ያሉትን ያዝናናል፡፡ አብሮት የሚንቀሳቀስ እንግዳም አይጠፋም፡፡ የዕድሜ እኩዮቹም ሰሎሞን እንደሻኪራ ሲሾር ቆመው ማየት ብቻ ሳይሆን አብረውት ይዘፍናሉ፡፡ እንደ ሰሎሞን ወገባቸውን፣ መቀመጫቸውን እያወዛወዙ ይጨፍራሉ፡፡ በጭፈራው የደከመው የተሰጠውን ተቀብሎ ዞር ይላል፡፡
ሐዋሳ ሐይቅ ለዓሳ አስጋሪዎች ብቻ ሳይሆን እንደነ ሙሉቀን ላሉ ታዳጊዎች ህልውናም ነው፡፡ በዙሪያው የዓሳ ሬስቶራንቶች ከፍተው ከሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች ባሻገርም፣ በርካቶች በጌጣጌጥ ንግድ፣ ዓሳ በመበለትና በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርተው ኑሯቸውን ይገፋሉ፡፡ በሐይቁ ዳርቻ ላይ የሚኖሩት አባኮዳዎችም በአካባቢው ያለው የሰዎች እንቅስቃሴ ለሕልውናቸው መሠረት የሆነ ይመስላል፡፡ ከሚወረወርላቸው ቁርጥራጭ ሥጋ ባሻገር በዳርቻው ከሚበለተው ዓሳ ተረፈ ምርቱን ይመገባሉ፡፡ ለሐይቁ ልዩ ድባብ የሚፈጥሩለት አባኮዳዎች ወደ ላይ ባኮበኮቡ መጠን እነ ሙሉቀን ብር ይሰበስባሉ፣ የጎደላቸውን ይሞላሉ፣ የተቸሩ ወላጆቻውን ይረዳሉ፡፡ ከሐይቁ የሚወጣው የዓሳ ምርት በአካባቢው ያሉ አስጋሪዎችን እንዲሁም ነዋሪዎችን ይመግባል፡፡
አቶ ዳዊት አብርሃም የሐዋሳ ሐይቅ ዓሳ አስጋሪዎች ሁለገብ የኅብረት ሥራ ማኅበር ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ማኅበሩ 495 አባላት አሉት፡፡ በሐይቁ ትሩፋት ላይ የተመሠረተው ማኅበሩ፣ ለ250 የቀን ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ 20 ለሚሆኑ ቋሚ ሠራተኞችም እንዲሁ ሠርተው እንዲገቡ አስችሏል፡፡
የሐዋሳ ሐይቅ ደግሞ አይነጥፍም፡፡ ወቅቱ ጥሩ ሲሆን፣ በቀን 5ሺሕ ብር፣ አነሰ ከተባለ ደግሞ በቀን ሦስት ሺሕ ብር፣ ሲከፋ ደግሞ በአንድ ሺሕ ብር ዓሳዎች ይሸጣል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ከነሐሴ 15 እስከ ጥር ድረስ የሐይቁ የዓሳ ምርት የተትረፈረፈ ይሆናል፡፡ ነፋስና ማዕበል በሚበዛበት ወቅት ግን ምርቱ የመቀነስ አዝማሚያ አለው፡፡
የሐይቁ ውኃ በሚቀዘቅዝበት ጊዜም እንዲሁ ምርቱ ይቀንሳል፡፡ ለወትሮው የሐይቁ የላይኛው ክፍል ላይ ሲርመሰመሱ የሚውሉ ዓሳዎች ቅዝቃዜውን ሽሽት ወደ ሐይቁ የታችኛው ክፍል ወርደው ይተኛሉ፡፡ ሞቅ ሲል ግን ምሽጋቸውን ለቀው ወደላይኛው የሐይቁ ክፍል በመውጣት ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በማጥመጃ መረቡ ውስጥ በርከት ያሉ ዓሳዎች ይገባሉ፡፡ የማኅበሩ ጊቢም አብሮ ከፍ ይላል፡፡ እነ ሙሉቀን ለአባኮዳዎች የሚወረውሩትን ቁርጥራጭ የዓሳ ሥጋም በነፃ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
የሐዋሳ ሐይቅ የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎችን ያፈራል፡፡ ከዓሳ ዝርያዎቹ ለገበያ የሚቀርቡት ሁለቱ ዓይነት እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ዳዊት፣ የሚያድጉ ትንንሽ የዓሳ ዝርያዎች በብዛት ለዓሳዎች ምግብነት እንደሚውሉ ገልጸዋል፡፡
ከሚያድጉት የዓሳ ዝርያዎች መካከል ኢግል የተባለው ዝርያ አንዱ ሲሆን፣ ትልልቆቹ ዓሳዎች የሚመገቡት መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ የአምባዛ ዓሳ ዝርያ የሆነው ጦቂና ቆሮሶ በብዛት ለወጥ የሚውሉ ናቸው፡፡ ቆሮሶ የሚባለው ዝርያ ደግሞ ለጥብስ፣ በለብለብና በጥሬው የሚበላ ነው፡፡ በጥሬው የሚበሉ የዓሳ ዝርያዎችን በማፍራት የሚታወቀው የሐዋሳ ሐይቅ፣ ዙሪያው እንደ መርካቶ ተጨናንቆ ይውል ነበር፡፡ አንድ ዓሳ ከአሥር እስከ 13 ብር የሚቸበቸብበት ሰፊ የንግድ መዳረሻም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በከተማዋ ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ መቀዛቀዝ ታይቶበታል፡፡ የጎብኚዎችም ቁጥር እንደ ቀድሞው ባለመሆኑ የእነሙሉቀንና የእነሰሎሞን ገዥም ቀዝቀዝ ብሏል፡፡ ሁኔታውን ሰሎሞን ሲገልጽ ‹‹ሽቀላ የለም›› ብሏል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር