በሮመዳን ጾም ወቅት ያሳየነውን አብሮነት አጠናክረን እናስቀጥላለን….በሀዋሳ የእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታዮች

ግንቦት 22/2011 በሮመዳን ጾም ወቅት ያሳዩትን አብሮነት አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ የሀዋሳ ከተማ የእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታዮች ተናገሩ፡፡
በሀዋሳ ከተማ የሚኖሩት አቶ አለሙ ሙርጉ እንዳሉት በሮመዳን ጾም ከሙስሊምና ክርስቲያን ወገኖቻቸው ጋር በመሆን የአፍጠር ሰዓትን አብረው የማሳለፍ የቆየ ልምድ አላቸው።
በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ከወዳጅ ዘመድና ጎረቤቶቻቸው ጋር ተሰባስበው ሲያፈጥሩ ባገኘናቸው ወቅትም የሮመዳን ፆም ከአምስቱ የእስልምና አስተምህሮት ማዕዘናት አንዱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የሮመዳን ወር የመተዛዘን፤ የመስጠትና የአብሮነት ወቅት መሆኑንም ተናግረዋል ፡፡
በተለይ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ወቅት የሚያሳዩት ሙስሊም ከሙስሊም፤ ሙስሊም ከክርስቲያን ያላቸው መደጋገፍና አብሮነት በሌላ ክፍለ ዓለም የማይስተዋል መሆኑን ነው የገለፁት ፡፡
ቀደም ባሉ ጊዜያት ሙስሊሙን ከሙስሊም እንዲሁም ሙስሊሙን ከክርስቲያን ለማጋጨት የሚደረጉ ጥረቶች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ አለሙ፣ “ነብዩ መሀመድ ያስተማሩን ፍቅርን እንጂ በእምነት ምክንያት ሌላውን መጥላትና ጠብን አይደለም” ብለዋል ፡፡
በረሞዳን ወቅት የሚታየውን የአብሮነት እሴት በሌላ ጊዜም አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ገልጸው “በመካከላችን ገብተው ለሚያውኩን ኃይሎች ዕድል አንሰጥም” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በቤተሰባቸው ውስጥ የእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታዮች መኖራቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ መነን ወልዴ በበኩላቸው ከክርስቲያን ቤተሰቦቻቻቸውና ጎረቤቶቻቸው ጋር በመከባበርና በመፈቃቀድ እንደሚኖሩ ገልጸዋል።
የእስልምና አስተምህሮትም ይህን እንደሚፈቅድ ነው የተናገሩት፡፡
እንደ እናትም እንደ ማህበረሰብ አባልም የራሴንም ሆነ የጎረቤቶቼን ልጆች የተስተካከለ አመለካከት እንዲኖራቸውና ኢትዮጵያዊ የአብሮነት እሴቶችን ተቀብለው እንዲያስቀጥሉ የማሳወቅ ግዴታዬን እወጣለሁ ብለዋል ፡፡
“ከዚህ ቀደም ግለኝነት እንዲስፋፋ ብሎም በመካከላችን መጠራጠር እንዲኖር የሚያደርጉ ብዙ ነገሮች ተፈጥረዋል” ያሉት ወይዘሮ መነን፣ በአሁኑ ወቅት በሀገር ደረጃ ጥሩ ነገር እየታየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አቶ ከድር ሉምቤዎ በበኩላቸው እርስ በርሳችን እንድንከፋፈል የሚጥሩ ኃይሎች ከበስተጀርባ የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚሰሩ ናቸው” ብለዋል፡፡
የሮሞዳን ወር ሙስሊሙ ከክርስቲያኑ ጋር ያለውን ትስስር የሚያጠናክርበት የቸርነትና በጎ የመስራት ወር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ግንኙነቱ በዚህ ብቻ የሚያበቃ ባለመሆኑ በዕድር፣ በእቁብና በሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮች አንድነቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ከአቶ አለሙ ቤተሰብ ጋር ሁሌም በአፍጥር ሰዓት የማይለዩትና የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑት አቶ አዳነ ተስፋዬ በበኩላቸው ከአምልኮታዊ ሥርዐት ልዩነት ውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሙስሊሙና የክርስቲያን እምነት ትስስር ከሚነገረው በላይ መሆኑንም ገልፀዋል ፡፡
“ለወደፊቱም ልዩነቶቻችን እንደተጠበቀ ሆኖ በሰውነት አንድ መሆናችንን ከምንም ነገር በላይ በማስቀደም በመፈቃቀድና በመተሳሰብ መኖርን ለትውልዱ ማውረስ ይገባናል” ብለዋል ፡፡
ለዓመታት ከአቶ አለሙ ቤተሰብ ጋር የሮመዳንን ወር በጋራ እያሳለፈ መቆየቱን የሚናገረው ወጣት ነስረዲን ቁምዲን በበኩሉ፣ “የሮመዳን ወር አልቆ ቀጣይ ሮመዳን እስኪመጣ ድረስ ከሙስሊሙና ክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር አብረን የምናሳልፈው የአፍጥር ሰዓት ይናፍቀናል” ብሏል ፡፡
ይህንን መልካም እሴት ተቀብሎ በሌላም ጊዜ በተሸለ መልኩ እንዲቀጥል የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም መሆን እንዳለበት ተናግሯል፡፡
ወጣቱ ትውልድ ወደኢትዮጵያዊ ማንነቱ ሊመለስና አባቶች ያቆዩለትን አብሮነት ጠብቆ ሊያቆይ እንደሚገባም ነው ያመለከተው ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

የሲዳማ ክልል ባለስልጣናትን ጨምሮ የተገለገሉት የሰሞኑ የቻርተር አውሮፕላን በረራዎች!

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ብሔር በሰፊው የሚታወቀው የ"አፊኒ" ባህላዊ የዳኝነት ስርዓትና የአዋጅ ረቂቅ ተሞክሮ በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ቀረበ