ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ለፊቼ ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ


ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዓሉን አስመልክተው ያሥተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም የሚከተለውን ይመስላል።
እንኳን የሲዳማ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓል ለሆነው ለታላቁ የጨምበላላ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤አደረሰን፡፡
አይዴ ጨምበላላ!
ዘመን የሰው ልጆች የታሪክ፣ የማንነት፣ የባሕል፣ የሥነ ልቡና እና የህልውና መከተብያ፣ መሳያ፣ መበየኛ፣መንደፍያ እና ማቆያ ትንግርታዊ ሰሌዳ ነው፡፡ይህንን ድንቅ ሸራ በመቁጠር – በመቀመር – በማስላት እና በተፈጥሮ ዑደት ውስጥ የሚዘወርበትን ሥርዓት በመዘርጋት የሚጠቀምበት ማኅበረሰብ ደግሞ እርሱ ከዘመን ጋር የማይሄድ ከዘመንም ጋር የማይመጣ በዘመን ገላ ላይ ትናንት በአባቶቹ – ዛሬ በራሱ እና ነገም በልጆቹ ህያው የሚሆን ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ የሲዳማ ሕዝብ ይህን ታላቅ የሥልጣኔ አበርክቶ አጥሮ፣
ጠብቆ አቆይቶልናል፡፡
የሰው ልጅን የለውጥ፣ የጥበብ፣ የአዝማናት የሥልጣኔ ጫፍ እና ያለፉበትን የታላቅነት የዘመን መልክ የሚያጠኑ ጠበብት በአንድ ቃል እንደሚስማሙት እነዚህ ዘመንን ከዘመን የሚያሰናስሉ አዕማድ የሚለኩባቸው እና የሚመዘኑባቸው ዐበይት መሥፈሪያዎች አሉ፡፡
ከእነዚህ ዐበይት የሥልጣኔ እናየታላቅነት ማሳያ አብነቶች ውስጥ አንዱ፤ ምናልባትም ዋነኛው – የማኅበረሰቡ የዘመን ቀመር ዕውቀት ቀዳሚ እንደሆነ አብዛኛዎቹ ልሂቃን ይስማማሉ፡፡ በዚህ ዋና ባልነው መለኪያ ስንመዝነው ደግሞ የሲዳማ ሕዝብ በፀሐይ፣ በጨረቃ እና በከዋክብት ድንቅ የተፈጥሮ ዑደት ውስጥ ያለውን ጥልቅ የምልዐተ ዓለም (Universe) ምሥጢር በመመርመር ጊዜን እያሰላ ዘመንን የሚቆጥርበት ጥበብ እጅጉን የሚደንቅ እናየሁላችንም የኩራት ምንጭ ነው፡፡
የሰው ልጅ ከጊዜ (Time) እና ከቦታ (Space) ውጪ ለማሰብ፣ ለማሰላሰል፣ ለመፍጠር፣ እና ተፈጥሮን ለመመርመርም ሆነ እራሱን ለማረቅ እጅጉን ይቸገራል፡፡ ጊዜን የምናሰላበት መንገድ እና ዘመንን ኢትዮጵያ: አዲሲቷ የተስፋ አድማስ Ethiopia: A New Horizon of Hope 2 የምንቀምርበት ጥበብም እንደ ሰውም ሆነ እንደ ማኅበረሰብ ለሁለንተናዊ ሥልጣኔያችን እና ራሳችንንም ሆነ ዙሪያችንን ለምንቀርጽበት ሰብእናችን ብዙ ዐቅም ይቸረናል፡፡ ተጠቃሚዎችም ያደርገናል፡፡
በሲዳማ የዘመን አቆጣጠር ጥበብ ውስጥ እስከ ማይክሮ ሰከንድ ሽርፍራፊ የጊዜ ቅንጣት ድረስ የሚወርድ ጊዜን የመለኪያ ጥበብ አለ፡፡ ይህ ደግሞ ለሲዳማ አባቶቻችን ያለንን ክብር እና ፍቅር እጅጉን ከፍ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም ይሄንን የሲዳማን ሕዝብ የአዲስ ዓመት በዓል እና የዘመኑን አዲስነት ለማወጅ ጊዜን የሚቆጥርበትን ግሩም ዕሴት መላው ኢትዮጵያዊ ወገናችን ክብሩንም ሆነ በዓሉን ከልብ ይወደዋልወዶም እንደ ሁልጊዜው በጋራ ያከብረዋል፡፡
ከራስ የሚነሣ የዘመን ቀመር ባለቤት ለመሆን መቻልያለጥርጥር ታላቅነት ቢሆንም ባሰሉት ዘመን፣ በቀመሩት ቀመር፣ ባሠመሩት የዘመን መሥመር ላይዘመን የሚሻገር እና የእኛን እና የልጆቻችንን የዘመን ካብ የሚያተያይ ደማቅ አሻራ ለማኖር መቻል ደግሞ ከታላቅነትም የሚልቅ እጹብ ታላቅነት ነው፡፡
ከዋዜማው የፍቼ ትእይንት እስከ ዋናው የጨምበላላ በዓል ድረስ አስደማሚ የዘመን መለወጫ የአከባበር ሂደት እና ሁሌም እንደ አዲስ የሚያስደምም ግሩም ሥርዓት አለው፡፡ የሲዳማ ሕዝብ በዘመናት ቅብብሎሽ በሚደንቅ ጥበብ ጠብቆ ያቆየው በመሆኑ ለዚህ ዘመን አይሽሬ የሀገር እና የዓለም ህያው አእምሯዊ ሀብት ያለኝን ከፍ ያለ ክብር እና አድናቆት በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
በመጨረሻም ዘመኑ የሰላም፣ የይቅርታ፣ የፍቅር እና የአንድነት እንዲሆንልን መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ፡፡
አይዴ ጨምበላላ
መልካም በዓል
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!”
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ግንቦት 22 ቀን 2011 ዓ.ም

Comments

Popular posts from this blog

የሲዳማ ክልል ባለስልጣናትን ጨምሮ የተገለገሉት የሰሞኑ የቻርተር አውሮፕላን በረራዎች!

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ብሔር በሰፊው የሚታወቀው የ"አፊኒ" ባህላዊ የዳኝነት ስርዓትና የአዋጅ ረቂቅ ተሞክሮ በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ቀረበ