የፊቼ ጫምባላላ በዓል ይፋዊ አከባበር ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል በጉዱማሌ ተከበረ።
በበዓሉ ላይ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማት መሪዎች፣ የሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተወከሉ እንግዶች ታድመዋል።
በዓሉ በጎሳ መሪዎች የምርቃት ስነ ስርዓት ነበር የተጀመረው።
የጎሳ መሪዎች በአሮጌው ዘመን በማህበረሰቡ ዘንድ የታዩ በጎ ነገሮች እንዲጎለብቱ መልክዕታቸውን አስተላልፈዋል።
በአንፃሩ በማኅበረሰቡ ዘንድ በአሮጌው ዘመን የታዩ አፍራሽ ተግባራት ደግሞ እንዳይደገሙ ነው የጎሳ መሪዎቹ ያሳሰቡት።
አዲሱ ዘመኑ የሰላም፣ የብልጽግናና የልማት ይሆን ዘንድም ምኞታቸውን በማስተላለፍ የዕለቱን ፕሮግራም አስጀምረዋል።
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ፍቼ ጨምባላላ የዘመን መለወጫ ብቻም ሳይሆን ሰላምን፣ አብሮነትንና እርቅን ያቀፈ መሆኑን ገልጸዋል።
እውነተኛ የፌዴራል ስርዓት እንዲጠናከር ግብዓት የሚሆን እና በአራያነት የሚጠቀስ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት የተጋበዙት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፥ የፊቼ ጨምበላላ እሴት በሆነውን ይቅር መባባል በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ ያሉ መቃቃሮችን በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዞ ቀን ከሌት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በዓሉ የሰላም፣ የመቻቻልና የአብሮነት እሴት የያዘ ከመሆኑም ባሻገር ከሰው አልፎ ለእንስሳትና እፅዋት እንክብካቤ የሚደረግበት ነው ብለዋል።
የኢፌዲሪ የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው ኢትዮጵያ በብዘሃ ባህል የታደለች በዘመናት ውጣ ውረድ ሳይበረዙና ሳይከለሱ ቱባ ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው ለአሁኑ ትውልድ ከደረሱት መካከል የሲዳማ ዘመን መለወጫ ፍቼ ጨምበላላ በዓል መሆኑን ገልፀው፥ በዓሉን በመጠበቅ ለአሁኑ ትውልድ ላደረሱ አባቶችና እናቶች ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አያይዘውም የአሁኑ ትውልድ እነዚህን የባህል ሀብቶችን በማጥናትና በመሠነድ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ሚኒስቴሩ የብሔር ብሔረሠቦችን ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ እንዲጠኑ፣ እንዲጠበቁ እና እንዲለሙ እንደሚሠራና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው ያረጋገጡት።
ይፋዊ የበዓሉ አከባበር የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በቀጣይ ሳምንታት በልዩ ልዩ ወረዳዎች በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ለማወቅ ተችሏል።

Comments
Post a Comment