የፍቼ እና ጫምባላላ የሲዳማ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ባህል እና ቱርዝም ሚኒስቴር
በሲዳማ ፍቼና ጫምባላላ የማይነጣጠሉ የበዓሉ ሁነቶች ናቸው፡፡ ፊቼ የአሮጌው ዘመን መጠናቀቅ (ዋዜማ) ጫምባላላ የአዲሱ ዘመን (መባቻ) ብስራቶች ናቸው፡፡ ‹‹ፊቼ›› መጽሔት በ2006 ዓ.ም. ዕትሙ፣ ፊቼና ጫምባላ ታሪካዊ አጀማመር መቼ እንደሆነ በውል ባይታወቅም በዞኑ በሀቤላ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ከነበሩት ፊጦራ የሚባሉ ሰውዬ ሴት ልጃቸው ፊቾ አማካይነት መጀመሩን ለቅድመ ምዝገባ ጥናት የተሰበሰበው መረጃ ያመለክታል፡፡
ፊቾ የምትባለው የአቶ ፈጠራ ልጅ ለአቅመ ሔዋን ደርሳ ባል ስታገባ የሞቀ ትዳር፣ የተትረፈረፈ ሀብት ስታገኝ በብሔሩ ባህል መሠረት እናት አባቷን ቅቤ፣ የተሠራ ቆጮና የረጋ ወተት ይዛ እየመጣች በየዓመቱ ‹‹ቀባዶ›› ተብሎ በሚጠራው ቀን ትጠይቃቸው ነበር፡፡ ያመጣችውን ምግብ ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድና ጎረቤቶች ከበሉ በኋላ ከአባቷ ጋር ምርቃትና አድናቆታቸውን ይገልጹላታል፡፡ በእርግጥ በሲዳማ ባህል ልጆች የሚመገቡት ትላልቆቹና አዋቂዎቹ ከበሉ በኋላ ስለሆነ የቀረውን የቤተሰብና የጎረቤት ልጆች አንድ ላይ ተሰብስበው ይመገቡና ደስታቸውን ጫምባላላ (የዚህ አይነት ጥጋብ ዞሮ ይምጣ) እያሉ በዘፈን ይግልጻሉ፡፡ መሰል የፊቾ ጥየቃ በዘላቂነት መታወስ እንዳለበት በመግለጽ አባቷ አቶ ፌጦራ በየዓመቱ ደስታና ፋሲካ የምትፈጥረው ልጃቸው የምትመጣበት ቀን የሲዳማ ፌቼ ተብሎ እንዲከበር ከአካባቢው ኅብረተሰብ ተቀባይነት አግኝቶ በጎሳ መሪዎች የዘመን መለወጫ እንዲሆን መወሰኑን የጥናቱ መረጃ ያስረዳል፡፡ ይሁን እንጂ የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፊቼና የቀን አቆጣጠር ከፊቾ ታሪክ ጋር ስለመያያዙ ከአፈታሪክ መረጃ በስተቀር ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልገው ጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል በዘመናት ሂደት የብሔሩ ሊቃውንት የየዓመቱን ዙር መሠረት አድርገው የቀን፣ የወርና የዓመት አቆጣጠር ዘዴን በመቀመር ፊቼ የሲዳማ የዘመን መለወጫ በዓል እንዲሆን መወሰናቸውን ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ ተብራርቷል፡፡ ፊቼ ትርጉሙም የዘመን መለወጫ ድልድይ አዲሱ ዓመት የበረከት የደስታና ፍሥሐ ይሁንልን እንደማለት ነው፡፡ ከዋዜማ ቀጥሎ ያለው ቀን አዲስ ዓመት ወይም ጫምባላላ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ስለአለፈው ዓመት ለፈጣሪ ምስጋና፣ ስለቀጣዩ ደግሞ የመልካም ምኞት የሚገለጽበት የደስታና ፍንደቃ ዕለት ይሆናል፡፡
Comments
Post a Comment