የሲዳማ ክልል ህዝበ ውሳኔን በተመለከተ በብሄራዊ የምርጫ ቦርድ በዛሬው መግለጫ ምንም አዲስ ነገር የለም
ምርጫ ቦርድ ለቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ 3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር እንዲፈቀድለት ጠየቀ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 19 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ማስኬጃ 3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር እንዲፈቀድለት ለህዝብ ተወካዮች የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጠየቀ።
ቦርዱ ተቋማዊ ለውጥ ካስተዋወቀበት ጊዜ ጀምሮ እየሰራቸው ባሉ ስራዎች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም ለቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ 3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር እንዲፈቀድለት መጠየቁን አስታውቋል።
የለውጥ ስራዎቹ ቦርዱን በህዝብ ተዓማኒ የሆነ ተቋም በማድረግ ለቀጣዩ ምርጫ ለማዘጋጀት ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
ከዚህ ውስጥም ቦርዱ የህግ ማዕቀፎችን ማሻሻል፣ ተቋማዊ ማሻያዎችን ማድረግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ ማዘጋጀትና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ ማድረግ ይገኝበታል።
ከዚህ ባለፈም ከሲቪክ ማህበራት ጋር አብሮ መስራት የሚቻልበትን ሁኔታ ማሻሻልም ቦርዱ እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
በተጨማሪም ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በሚኖረው ትብብር ዙሪያ እየሰራቸው ያሉ ስራዎችንም በመግለጫው ጠቅሷል።
የህግ ማዕቀፎችን ከማሻሻል አንጻርም ቦርዱን መልሶ የሚያቋቁም አዋጅ ተረቆ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል።
በዚህም የቦርዱ አባላት ከ9 ወደ አምስት ዝቅ እንዲሉ የሚደረግ ሲሆን ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ መልኩም የሙሉ ገዜ ሰራተኞች እንዲሆኑ ተደርጓል።
የቦርዱ ጽህፈት ቤትም በፓርላማው ሳይሆን በቦርዱ አማካኝነት የሚደራጅ ሲሆን፥ እጩ የቦርድ አባላት አቀራረብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚከናወን ሆኖ በተሻለ ግልጽነት እንዲሰራ ስራዎች ተጀምረዋል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ የስነ ምግባር ህጎች እና የምርጫ አፈጻጸምና አስፈጻሚ አካላት ጋር በተያያዘም ህጎች በአንድ እንዲወጡ ታስበው ረቂቃቸው ቀርቦ ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።
ቦርዱ ካሉት አምስት የቦርድ አባላት ቀሪ አራቱን ለማሟላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እጩ አቅራቢ ኮሚቴን አዋቅረው ኮሚቴው ጥቆማዎችን በመቀበል ላይ መሆኑም ተገልጿል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ጋር በተያያዘም አሁን ላይ 24 ሀገር አቀፍና 42 ክልላዊ ፓርቲዎች በአጠቃላይ 66 ፓርቲዎች ሰርተፊኬት ማግኘታቸው ተገልጿል።
ቦርዱ ለቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ከጠየቀው በጀት ውስጥ 900 ሚሊየን ብሩን ከተለያየቱ አለም አቀፍ አጋር ሀገራት ለማሰባሰብ የታቀደ ሲሆን ቀሪው በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ይሆናል።
በመግለጫው ላይ የፓርቲዎች የእውቅና ጥያቄ፣ የድርጅታዊ መዋቅር ለውጥ፣ የምርጫ ዝግጅትና አፈጻጸም እንዲሁም ከሲዳማ ክልል የመሆን ጥያቄ ጋር በተያያዘ የቀረበ የህዝበ ውሳኔ ጥያቄ የቦርዱን አባላት መሟላት የሚጠይቁ ናቸው ተብሏል።
ከቀጣዩ ሃገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘም ሀገሪቱ ምርጫን ለማድረግ ከጸጥታ አንጻር ዝግጁ ናት ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ ተሰጥቶበታል።
በምላሹም ይህን አይነት ጉዳይ በቦርዱ እንደማይመለስና ጉዳዩን በተመለከተ አለም አቀፍ ባለሙያዎች ተቀጥረው ጥናት እየተካሄደ መሆኑ ተጠቅሷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም በየአካባቢው ያለው ግጭት ደረጃና በምርጫው ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ በተመለከተ በጥናቱ ታይቶና ውጤቱን መሰረት በማድረግ በምርጫው ላይ ውሳኔ ይሰጣል ነው የተባለው።

Comments
Post a Comment