የ2012 የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ፊቼ ጫምበላላን በታላቅ ድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
የ2012 የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ፊቼ ጫምበላላን በታላቅ ድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ገለፀ::
የከተማው ህዝብ ግንኙነት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ተፈራ እንዲሁም የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መስፍን ዴቢሶ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፊቼ ጫምበላላ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ በዓል በመሆኑ በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ስጋት እንዲጠናቀቅ እንደ ከተማ መጠነ ሰፊ ስራ የተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በዚህም በፀጥታ ዙሪያ ሊከሰቱ የሚችሉ ስጋቶችን በመለየት በቁጥጥር ስር ለማዋል ይረዳ ዘንድ ከሰላም ወዳድ የከተማዋ ህብረተሰብ ጋር ከከተማ እስከ ቀበሌ ድረስ የዘለቁ ሰፊና ፍሬያማ ውይይቶች መካሄዳቸውንም ነው ኃላፊዎቹ የገለፁት፡፡
ፊቼ ጫምበላላ ሰዎች እርስ በእርሳቸው የሚቀራረቡበት፣ የሰላም፣ የደስታ የፍቅር በዓል ነው ያሉት ኃላፊዎቹ በበዓሉ አከባበር ላይ ለመሳተፍ ከኢትዮጵያ ከተሞችና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት በርካታ እንግዶች ወደ ሀዋሳ ይተማሉም ብለዋል፡፡
እንግዶቹን በደማቅ ሁኔታ ለመቀበልና በዓሉ ያለምንም ችግር በሰላም እንዲከበር በከተማ አስተዳደሩ በቂ ዝግጅት መደረጉን የገለፁት ኃላፊዎቹ የከተማው ፖሊስ ከከተማው ህብረተሰብ፣ ከኤጄቶዎች፣ ከሲዳማ ዞን፣ ከፌደራል እና ከክልል የፀጥታ ሀይል ጋር በመቀናጀት የክትትል፣ የቁጥጥር እና የጥበቃ ስራ እየተሰራ መሆኑንም በማመላከት ነው፡፡
ፊቼ ጫምበላላ የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ፣ የኢትዮጵያውያን መገለጫ እንዲሁም የዓለም ቅርስ ነው ያሉት አቶ መልካሙ በዓሉን የሚመጥን የዝግጅት ስራ መሰራቱን አመላክተዋል፡፡
በዓሉን በሰላም ማክበር የከተማውም የገጠሩም ነዋሪ ፍላጎት ነው ያሉት ኮማንደር መስፍን በበኩላቸው ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰላም ዋጋ ያልገባቸው አይታጡምና ፖሊስ ያራሱን በቂ ዝግጅት ማድረጉን አመላክተዋል፡፡

Comments
Post a Comment