ማህበሩ ከራሱ አልፎ ሌሎችንም እየጠቀመ ነው

ከውቢቷ ሃዋሳ ገፀበረከቶች ዋናውና አንደኛው የሃዋሳ ሐይቅ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ሐይቁ የከተማዋ ውበት፣የቱሪስት መስህብና ለብዙዎች ደግሞ የዕለት ገቢ ማግኛ መሆኑ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ለከተማዋ ወጣቶች በርካታ የሥራ ዕድሎችን ፈጥሯል፡፡ በሐይቁ ዙሪያ በማህበር በመደራጀት ለአገር ውስጥና ለውጭ ቱሪስቶች የጀልባ አገልግሎት ከሚሰጡ ማህበራት ውስጥ የሃዋሳ ፍቅር ሐይቅ የጀልባ መዝናኛ ሁለገብ ህብረት ሥራ ማህበር አንዱ ነው፡፡ ማህበሩ ጎዳና ላይ ወድቀው የነበሩ ታዳጊዎችን በማንሳትና አባል በማድረግ ሥራ እንዲሰሩና ራሳቸውን እንዲችሉ ብሎም ትምህርታቸውን እንዲማሩ በማድረግ አርአያነት ያለው ተግባር በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡
ታዳጊ አዳነ ከበደ ወላጆቹን በሞት አጥቷል፤ ከዘመዶቹ ጋር ባለመስማማቱ ከሚኖርበት አሩሲ ነገሌ ወደ ሃዋሳ በመምጣትም ያለፉትን ሁለት ዓመታት በጎዳና ላይ እንዳሳለፈ ይናገራል፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም ፀሐይና ብርድ ሲፈራረቅበት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ነገር ግን የማህበሩ አባላት ከጎዳና ላይ አንስተው ካመጡት በኋላ በብዙ መንገድ ተጠቃሚ እንደሆነም ይገልፃል፡፡ወደ ማህበሩ ከመጣም ወዲህ ፑል ማጫወትና ሌሎች ሥራዎችንም ይሰራል፤ ማህበሩም ቁርስ፣ ምሳና እራት እንዲሁም ማደሪያውን እገዛ እንደሚያደርግለት ገልጾ በቀጣዩ ዓመትም ትምህርት ለመማር ማሰቡን ይናገራል፡፡
ወጣት አብነት እርዳቸው የ12 ዓመት ታዳጊ እያለ ከሲዳማ ለኩ ከተባለች ቦታ ከቤተሰቡ ጋር ባለመግባባቱ ወደሃዋሳ እንደመጣ ያስረዳል፡፡ ልክ እንደ ታዳጊ አዳነ ሁሉ በጎዳና ህይወት ማሳለፉን ይገልጻል፡፡ ጎዳና ላይ በቆየባቸው ዓመታትም ለበርካታ ችግሮች ተጋልጦ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ነገር ግን አሁን ወደ ማህበሩ ከተቀላቀለ በኋላ ቀደም ሲል የነበረው ህይወቱ መሻሻሉንና ትምህርት መጀመሩንም፤ ለትምህርት የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ ማህበሩ እያሟላለት ከመሆኑም በላይ ለጥናት የሚሆን ጊዜም እንደሚሰጠው ያስረዳል፡፡ በትምህርቱም ጥሩ ውጤት በማምጣቱ ማህበሩ በአሁኑ ወቅት የተሻለ ትምህርት ቤት አስገብቶ እያስተማረው ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ወደ 12ኛ ክፍል እንደተሸጋገረ ያስረዳል፡፡ በቀጣይም ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ሥራው ዓለም ሲቀላቀል ያሳደገውን ማህበር መልሶ የማገልገል ፍላጎት አለው፡፡ እንደእርሱ ጎዳና ላይ ያሉ ወጣቶችም የሥራ ዕድል ካገኙና ፍላጎቱ ካላቸው ሰርተው ህይወታቸውን መቀየር እንደሚችሉ ይመክራል፡፡
ቀደም ሲል በጎዳና ላይ ህይወታቸውን ይመሩ የነበሩ ነገር ግን አሁን በማህበሩ ባገኙት ድጋፍ በተለያዩ ሥራዎች ተሰማርተው ራሳቸውን ያሻሻሉ ወደ 27 የሚጠጉ ታዳጊዎች እንዳሉ የሚጠቅሱት አቶ መላኩ ጋምቡራ የሃዋሳ ፍቅር ሐይቅ የጀልባ መዝናኛ ሁለገብ ህብረት ሥራ ማህበር አባል ናቸው፡፡
ማህበሩ ቁርስ፣ ምሳና እራት በመመገብም ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንና በቀጣዩ በጀት ዓመትም ትምህርታቸውን መከታተል የሚፈልጉ ታዳጊዎችን ትምህርት ቤት በማስገባት ለማስተማር ዕቅድ መያዙን ያስረዳሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር በማህበሩ ውስጥ ታዳጊዎቹ የራሳቸውን ሥራ በመፍጠር ገቢ በማግኘት ራሳቸውን የሚችሉበትን አማራጮች እያመቻቹ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡« ለወግን ደራሽ ወገን» ከመሆኑ አኳያም እያደረጉት ያለው ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡
አቶ ግዛቸው ጥላሁን የሃዋሳ ፍቅር ሐይቅ የጀልባ መዝናኛ ሁለገብ ህብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ ናቸው። እርሳቸውም እንደሚሉት በማህበር ተደራጅተው ሥራ ከመጀመራቸው በፊት የነበራቸው ህይወት ችግር የበዛበት አስቸጋሪ ነበር፡፡አሁን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን ሲጀምሩና ህይወታቸው ሲቀየር ከፍ ያለ ነገርም ማሰብና በተመሳሳይ እነሱ ባሳለፉበት መንገድ ጎዳና ላይ ወድቀው ያሉ ታዳጊዎችን በማንሳት እገዛ ማድረግ መጀመራቸውን ነው ያብራሩት፡፡ ማህበራቸው ጎዳና ላይ የወደቁ ልጆችን ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች የተቸገሩና ሥራ አጥ የሆኑ ወጣቶችንም ጭምር ይረዳሉ፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር