የኢትዮጵያ ቡና ደረጃዎች ከአሥር ወደ ስድስት ዝቅ እንዲሉ ተወሰነ
በአሥር ደረጃዎች ተከፋፍሎ ለገበያ ሲቀርብ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና ምርት ወደ ስድስት ደረጃዎች ዝቅ ብሎ ለግብይት እንዲበቃ ተወሰነ፡፡
ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ እስካሁን የአገሪቱ የቡና ምርት በአሥር ደረጃዎች ተከፋፍሎ እንደየደረጃው ዋጋ እየተሰጠው ሲሸጥ ቆይቷል፡፡
ይህ የደረጃ አሰጣጥ ግን ለአሠራርም ሆነ የአገሪቱ የቡና ምርት ሊያገኝ የሚገባውን ዋጋ እንዳያገኝ በማድረጉ በአዲስ አሠራር እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡ በቡና ደረጃዎች አሰጣጥ ላይ የተደረገ ጥናት አዋጭ የሚሆነው አሥር የነበሩትን የቡና ደረጃዎች ዝቅ ማድረግ እንደሚገባ ነው፡፡
እንደ አቶ ኤርሚያስ ገለጻ፣ በዚህ ውሳኔ መሠረት ለምሳሌ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተብሎ ደረጃ ይሰጣቸው የነበሩትን በአንድ ደረጃ ማጠቃለል ያስችላል፡፡ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው የቡና ዓይነቶች ዋጋ ልዩነት ተቀራራቢ በመሆኑ በአንድ ዋጋ እንዲሸጡ ያስችላል፡፡ የተሻለ ዋጋም ያስገኛል፡፡ በመጋዘን አሠራርም አሥር ቦታዎች ከፋፍሎ ከማስቀመጥ በስድስት ቦታዎች ማስቀመጥ ጊዜና ጉልበትን ይቆጥባል ብለዋል፡፡
በአዲሱ የምርት ዘመን ከታኅሳስ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው ይህ አሠራር፣ በቡና አቅራቢዎችም መደገፉን የምርት ገበያው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከአንድ እስከ አምስት ደረጃ የተሰጣቸው ለኤክስፖርት የሚቀርቡ ሲሆን፣ ደረጃ ስድስት የተሰጠው ቡና ደግሞ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚውል ነው፡፡
Source:http://www.ethiopianreporter.com
Source:http://www.ethiopianreporter.com
Comments
Post a Comment