ኢትዮጵያ በአይ ኤስ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ ትችል ይሆን?

(ኤፍ.ቢ.ሲ) በየማህበራዊ ድረ ገፁ አይ ኤስ በኢትዮጵያዊያን ላይ የፈፀመውን የሽብር ጥቃት አስመልክቶ የተለቀቁ ምስሎችም ሆኑ ፅሁፎች ስር “በቀል እንፈልጋለን”፣ “ወታደራዊ እርምጃ ይወሰድልን” እና የመሳሰሉ አስተያየቶች ይነበባሉ።
በእርግጥ ለኢትዮጵያ ወታደራዊ እርምጃ አማራጭ መሆን ይችላል ወይ? አለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎችስ ስለ ጉዳዩ ምን ይላሉ?
የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት፣ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ጦርነትና ጦር መሳሪያን በተመለከቱ አለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ የሰሩትን ዶክተር ምፅላል ክፍለኢየሱስ በጉዳዩ ላይ አናግረናቸዋል።
ባለሙያዋ በመንግስታቱ ድርጅትም 3ኛ ዲግሪያቸውን በሰሩበት ዘርፍ በአማካሪነት ያገለገሉ የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያ ናቸው።

አይ ኤስ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያንን ለማጥቃት ለምን መረጠ?
የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዋ እንደሚያነሱት አይ ኤስ ኢትዮጵያውያን ላይ ይህን ዘግናኝ ድርጊት  የፈፀመው በአጋጣሚ አይደለም።
ቡድኑ ከመነሻው በቀጣይ ግዛቱን አስፍቶ ስለሚመሰርተው አገር እቅዱን ሲያስቀምጥ ኢትዮጵያ በዚያ ካርታ  ውስጥ  ትገኛለች፤ አሁን የፈፀመውም ድርጊት ይህን ህልሙን ማሳኪያ አንዱ መንገድ ነው ብለው ያምናሉ።
ኢትዮጵያውያንን በእንደዚህ መልኩ ሲገድል አገሪቱ በወሳኝ የፖለቲካ ምእራፍ ላይ መሆኗን ያምናል የሚሉት ዶክተር ምፅላል፥ ከወር በኋላ የሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ነው ይህ ታላቅ የፖለቲካ  ምእራፍ ይላሉ።
እናም ይህ ኢትዮጵያን መዳረሻው  ለማድረግ የተነሳ አሸባሪ ቡድን ይህንን ወሳኝ ምእራፍ ተጠቅሞ በቀላሉ የኢትዮጵያውያንን እና የመሪዎቿን አትኩሮት ለመረበሽ ፈልጎ ሊሆን እንደሚችል ትንታኔያቸውን አስቀምጠዋል።
አይ ኤስ በባህሪው ትኩረት በመሳብ እውቅናን ማግኘት የሚፈልግ አሸባሪ ቡድን እንደመሆኑ ዓላማውን ለመሳካትና አባላትን ለማግኘት ሲል የሰው ለሰውና የህዝብ ለህዝብ ልዩነቶችን ማስፋት ይፈልጋል፤ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የፖለቲካ ምዕራፍም ልዩነትን ለመፍጠርና የተፈጠረውንም ለማስፋት አሸባሪ ቡድኑ ይመቻል ብሎ ስለሚያምን ጥቃቱን ከዚህ አንጻርም ሊፈጽም ይችላል ነው የሚሉት ባለሞያዋ።
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ህዝቦቿ አሸባሪ ቡድኑ በሚፈልገው እና  ባቀደው መንገድ እንዳይጓዙለት ጥንቃቄን የተሞላ እርምጃን እና ውሳኔን ሊያሳልፉ ይገባል ሲሉ ባለሞያዋ ይመክራሉ።

በአይ ኤስ ላይ ምን እርምጃን መውሰድ ትችላለች?
ኢትዮጵያ በዜጎቿ ላይ በአይ ኤ አይ ኤስ የተፈፀመውን የሽብር ድርጊት ተከትሎ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ትችል ይሆን ወይ ለሚለው ጥያቄ፥ የእርሳቸው ምላሽ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ እርምጃውን መውሰድ ከባድ ነው በማለት በቀዳሚነት የደንቡን ጥያቄ ያነሳሉ።
“ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሀገር በሌላ ሀገር ወታደራዊ እርምጃ የምትወስደው ድንበሯ ሲነካባት ነው፤ ከሰሞኑ የተፈፀመው ጥቃት ግን በአሸባሪ ቡድኑ እንጂ የሊቢያ መንግስት በኢትዮጵያዊያን ላይ የቃጣው ባለመሆኑ ሀገሪቱ በቀጥታ በሊቢያ ላይ እርምጃ እንዳትወስድ ያደርጋታል ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ  እውቅና የተሰጠው የሊቢያ መንግስት ደግሞ ድርጊቱን በማውገዝ ሀዘኑን መግለፁ ሌላው ምክንያት ነው፤ ይህም ለድርጊቱ ተጠያቂ ቡድን እንጂ ተጠያቂ መንግስት አለመኖሩን ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ።
ለዚህ ማስረጃ የሚሉት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፅድቆ ዓለም አቀፋዊ ህግ የሆኑት ሁለት የደህንነት ስጋቶች ብቻ ናቸው፤ የግዛት እና የመከላከያ ደህንነት። 
አሁን አሁን የሰብዓዊ ደህንነት ጉዳይ ቢነሳም ዓለም አቀፋዊ ሀግ ሆኖ አገራት በሰብዓዊ ደህንነት ላይ ስምምነት መግባት አልጀመሩም።
የሀገራቱ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥም ሌላው ጥያቄ ነው የሚሉት ዶክተር ምፅላል ኢትዮጵያ በመከላከያ ሃይሏ ጥንካሬ ከአፍሪካ 2ኛ ደረጃን ብትይዝም ያንን ሁሉ ሃገር አቆራርጣ ወታደራዊ እርምጃ ልውሰድ ብትል ዋጋው እጅግ ከባድ ነው ይላሉ።
ሌላው የአንዲትን ሀገር ሉአላዊነት ጥሶ መንግስት ለመንግስት ያልሆነ ጦርነት ውስጥ መግባትን የሚፈቅድ አለማቀፋዊ ህግ የለም ያሉት ባለሙያዋ፥ በሊቢያ ያለው ሁኔታ አስፈርቶኛልና ጦርነት ላውጅ መብቴ ነው ማለት የማይሆን ነው ባይ ናቸው ባለሙያዋ።
“ለምሳሌ ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ጥቃት እያደረሰችብኝ ነው ብላ ካመነች አፀፋውን የመመለስ መብት ቢኖራትም፥ ሀገራት ለደህንነቴ ስጋት ሆነዋልና ጥቃት ለማድረስ እፈልጋለሁ ካለች ለመንግስታቱ ድርጅት ጥያቄዋን አቅርባ ተቀባይነት ማግኘት አለበት” ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሊቢያ ያለው ሁኔታ ለዜጎቼ ደህንነት አስፈርቶኛል በሚል ወደ ሊቢያ ወታደሮቿን ወደ ሊቢያ እንድታሰማራም አለማቀፍ ህጉ እንደማይፈቅድ ነው የጠቀሱት።
“ከደህንነት ስጋት አንፃር አለም የተስማማበት ስጋት በግዛት እና በመከላከያ ሃይል ላይ የተደቀነ ስጋት ሲኖር ነው፤ ኢትዮጵያ ውጭ ባሉ ዜጎቼ ላይ የደህንነት ስጋት ተፈጥሯል ብትል እንኳን በሰዎች ላይ የተፈጠረ የደህንነት ስጋት ለጦርነት እንደ መንስኤ ተደርጎ አይቆጠርም” ነው ያሉት ዶክተር ምፅላል።
ሽብርተኝነት የአለም ስጋት መሆኑ እውቅና ስለተሰጠው አሸባሪዎች ላይ መዝመት ማን ይከለክላታል የሚለው ጉዳይ ግን ክርክር ያስነሳል።
“በዚህ ረገድ የአለም መንግስታት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በመንግስታቱ ድርጅት በኩል በደረሱበት ስምምነት መረጃ መለዋወጥና ተባብሮ መስራትን እንጂ በተናጠል ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ላይ አይደለም” የሚሉት ባለሙያዋ፥ ይህን ለማድረግ በአሸባሪዎች እየተናጠች ያለችው ሃገር ሁኔታው ከአቅሜ በላይ ሆኗል በሚል የሃገራትን ጣልቃ ገብነት መጠየቅ አለባት፤ የሊቢያ መንግስት ግን እስካሁን መሰል ጥሪ አለማቅረቡ ኢትዮጵያ በተናጥል እርምጃ እንዳትወስድ ያደርጋታል” ብለዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዙዎች የግብፅን ሁኔታ ያነሳሉ።
በእርግጥ ግብፅ በአይ ኤስ 21 ዜጎቿ ሊቢያ ውስጥ ሲገደሉ ያለማንም ፈቃድ ሊቢያ ላይ የአየር ላይ ጥቃት ፈፅማለች፤ ይህም ህግን የጣሰ ቢሆንም ከግምት ውስጥ መግባት ያለበት ጉዳይ መኖሩን ነው ዶክተር ምፅላል የሚናገሩት።
በሊቢያ ጉዳይ የኢትዮጵያንና ግብጽን ሁኔታ ማነፃፀር ይከብዳል የሚሉት ዶክተር ምፅላል፥ “ግብፅ ከሊቢያ ጋር ድንበር ትጋራለች፤ ስለ ሀገሪቱ በርካታ መረጃዎችም አሏት፤ ኢትዮጵያ ግን ስል ሊቢያ እና አሸባሪ ቡድኑ ስለተሰገሰገባቸው አካባቢዎች መረጃዎችን ለማግኘት ሰፊ ጊዜ ያስፈልጋታል” ብለዋል።
“ግብፅ ከሊቢያ ጋር በምትጋራው ድንበር የመጣ አይ ኤስ ድንበሯን አቋርጦ እንዳይገባ ትስጋለች፤ ኢትዮጵያ ዘንድ ግን ያ ስጋት የለም” ነው ያሉት ባለሙያዋ።
ሌላው ኢትዮጵያ ወታደራዊ እርምጃ ብትወስድ አያዋጣትም የሚባለው የአይ ኤስ ሁኔታ መሆኑንን የሚገልጹት ዶክተር ምፅላል፥ “አሸባሪ ቡድኑ በትክክል የሰፈረበትን ቦታ መለየት አይቻልም፤ ያለ መረጃ የአየር ላይ ጥቃት መውሰድ ብትጀምር ደግሞ ለንፁሃን ሞት ምክንያት ሆኖ ከሊቢያም ጋር ሊያጣላና ወደማያልቅ ጦርነት ሊመራት ይችላል” ባይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ በአንድ በኩል የአይ ኤስን ፍላጎት እንደማሳካትም ይቆጠራል ነው የሚሉት የወታደራዊ ባለሙያዋ።
አይ ኤስ የራሱን የጦርነት ስትራቴጂ የሚከተል በመሆኑም ኢትዮጵያ ሳታስብበት በእርሱ ስትራቴጂ ብትገባ ውጤቱ ሽንፈት እንደሚሆንም ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ለበቀል ተብሎ የሚወሰድ እርምጃ ዘላቂ መፍትሄ አለመሆኑንና ምናልባትም አሻበሪ ቡድኑን በሌላ እኩይ ተግባር ማነሳሳት እንዳይሆን ሊታሰብበት እንደሚገባ ዶክተር ምፅላል አፅንኦት ሰጥተውታል።
ለጊዜያዊ መፍትሄ ተብለው የሚወሰዱ የበቀል እርምጃዎች በሊቢያም ሆነ በሌሎች ሀገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ሌላ የከፋ ችግር ሊፈጥር እንደሚችልም አብራርተዋል።
“በእርግጥም በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሊቢያን ጨምሮ ሰላም ባጡና ባልተረጋጉ ሃገራት ስለሚገኙም እርምጃው እነሱንም በሌላ የሽብር ተግባር ማስፈጀት እንዳይሆን ያሰጋል” ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ አማራጭ
የሰላም እና ደህንነት ምረምር ባለሙያው አቶ አበበ አይነቴ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ  በሊቢያ በሚንቀሳቀሰው የአይ ኤስ ቡድን ላይ ወታደራዊ እርምጃ  እንዳትወስድ የሚያደርጉ ምክንያት ናቸው የሚሉትን ይዘረዝራሉ።
ተመራማሪው አንዱ የሚሉት፥ ኢትዮጵያ ከሊቢያ  ጋር ያላት ርቅትን ነው። ቡድኑ ቋሚ የሆነ መገኛ ስፍራም ሆነ ወታደራዊ ካምፕ የሌለው መሆኑ ደግሞ ሁለተኛው ምክንያት ነው ይላሉ።
በመሆኑም ኢትዮጵያ  በቀጠናው ግብፅን ከመሰሉ የአይ ኤስ ሰለባ ከሆኑ አገራት ጋር ተባብራ የቡድኑን መስፋፋት መግታት መፍትሄ ነው ብለው ያስቀምጣሉ።
በተለይም ከግብፅ አንፃር ፕሬዚዳንቷ አብዱልፋታህ ኤል ሲሲ ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ  ይፋዊ ጉበኝት ላይ በነበሩበት ወቅት ሁለቱ አገራት  የተፈራረሙት  ሽብርተኝነትን  በጋራ የመከላከል እና የመዋጋት ስምምነት ለዚህ  ያግዛታል ብለው አቶ አበበ ያምናሉ።
ዶክተር ምፅላል በተጨማሪ የሊቢያ መንግስት በሀገሪቱ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ ሌላው የኢትዮጵያ አማራጭ  መሆኑን ተናግረዋል።
 “በሶሪያና በኢራቅው እየተወሰደ ያለውን አይነት እርምጃ በሊቢያ እንዲወሰድ የሃገሪቱን መንግስት ጥሪ እንዲያቀርብ ከማግባባት አንስቶ የመንግስታቱ ድርጅት አሸባሪ ቡድኑ ላይ እርምጃ እንዲወሰድ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያመነጭና እንዲያፀድቅ መጠየቅ እንደምትችልም ገልፀዋል።
“ያኔም የዜጎቻችንን ደም ከመበቀል በላይ ሽብርተኝነት የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ ይቻላል” ብለዋል የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዋ ዶክተር ምፅላል ክፍለኢየሱስ።
ከዚህም በላይ አይ ኤስ ልዩነትን ለመፍጠር የሚያደርጋቸውን ጥረቶች በመረዳት ኢትዮጵያውያን ቀድሞ ያዳበሩትን የመቻቻልና ልዩነትን አስጠብቆ አብሮ የመኖር እሴትን የበለጠ በማጠናከር አሸባሪ ቡድኑ የተመኘውን መለያየት ማክሸፍ ይቻላል ባይ ናቸው። 
ትናንት በተካሄደው ህዝባዊ ሰልፍ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በአገር ውስጥ ቀዳዳ ያጡ ሽበርተኞች በተለያዩ አገራት ባሉ ዜጎቻችን ላይ መሰል የሽብር ድርጊት እንዳይፈፀሙ ለመከላከል ኢትዮጵያ  ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም በማለት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በጥምረት ለመስራት ያላትን ዝግጁነት አስታውቀዋል።

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር