ሙስናን በክልሎች ለመከላከል መንግሥት የፖለቲካ ውሳኔ መስጠት አለበት ተባለ

‹‹በፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ጣልቃ መግባት ሕገ መንግሥቱን መጣስ ነው››
አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ
በክልሎች፣ ብልሹ አሠራርና ሙስናን ለመከላከል፣ የክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች በአመራሮች ተፅዕኖ በአግባቡ መሥራት ባለመቻላቸው የፌዴራል መንግሥት ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ የፌዴራል የሥነ ምግባር የፀረ ሙስና ኮሚሽን አሳሰበ፡፡
ኮሚሽኑ የአገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጥምረት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አሥረኛ መደበኛ ስብሰባውን ኅዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ለግማሽ ቀን ባካሄደት ወቅት እንደገለጸው፣ በየክልሉ ያሉ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ተቋማት በነፃነት እንዳይሠሩ የክልሎቹ አመራሮች ተፅዕኖ እያደረሱባቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ በአቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ ሰብሳቢነት በተካሄደው አሥረኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የተወሰኑ ባለድርሻ አካላት ብቻ ተገኝተዋል፡፡
የአገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጥምረትና የፌዴራልና የክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽኖች የ2006 በጀት ዓመት ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ፣ በተገኙት ጥቂት ባለድርሻ አካላት የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ በተለይ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በሶማሌ ክልሎች የፀረ ሙስና ተቋማት በነፃነት እየሠሩ እንዳልሆነና ያላቸውን ከፍተኛ ሀብት እንደ አገር መጠቀም አለመቻሉን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡ በክልል የሚገኙ አመራሮች እነሱ እንዲከሰስ የፈለጉትን የኮሚሽኑ ኃላፊዎች ካልከሰሱ ወይም መከሰስ የሌለባቸውን ከሰው ከተገኙ፣ ከኃላፊነታቸው እንደሚያነሷቸውና በፈለጉት ቦታ እንደሚመድቧቸው ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የአፋር ክልል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙና ኮሚሽን ኃላፊ እንደሌለው የጠቆሙት የስብሰባው ተሳታፊዎች፣ የሶማሌ ክልልም ኮሚሽነሩን በማንሳት ያለተቆጣጣሪ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ 
የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ክልሎች ማንን መሾምና  ማንን መሻር እንዳለባቸው የሚያዝ ሥልጣን እንደሌለው የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ የፌዴራል ሥርዓቱ የፈቀደውን ዕድል በአግባቡ እየተጠቀሙበት አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ክልሎቹ በተለይ አፋርና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ባለሀብቶችን የመሳብ ኃይል ቢኖራቸውም፣ ባለሀብቶቹ ተማምነው ሀብታቸውን ለማፍሰስ የተቸገሩበት ሁኔታ እንዳለም አክለዋል፡፡
በቤንሻንጉል ጉሙዝ በዕምነበረድ ማዕድን ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶች ሕጋዊ መንገድን ተከትለው ለመሥራት ቆርጠው የተነሱ ቢሆንም በዶማና ባካፋ የሚሠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ከሹማምንቱ ጋር ባላቸው የጥቅም ግንኙነት የማዕድን ቦታውን የወሰዱት በመሆኑ፣ ሀብቱን በአግባቡ ተጠቅሞ አገር የሚያስፈልገውን ገቢ እንዳያገኝ እየተደረገ መሆኑን አንድ የስብሳባው ተሳታፊ ገልጸዋል፡፡ 
ክልሉም ከማዕድን ማግኘት የሚገባውን ገቢ ማግኘት አለመቻሉንም አክለዋል፡፡ የክልሎቹ አመራሮች የፀረ ሙስና ኮሚሽነሮቹን ከማጠናከር ይልቅ በማዳከም ላይ በመሆናቸው፣ አፋጣኝ የፖለቲካ ውሳኔ ካልተሰጠበት በክልሉ የሚኖረው የሙስናና የብልሹ አሠራር ተባብሶ እንደሚቀጥል ሥጋታቸውን አስረድተዋል፡፡ ሌሎቹም ክልሎች አፈጻጸማቸው ከጊዜ ጊዜ የተለያየ መሆኑንና ከሦስቱ ክልሎች አንፃር ሲታይ የተሻሉ ቢሆኑም፣ በእነሱም ላይ ክትትል ማድረግና አመራር መስጠት ተገቢ መሆኑን ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ ‹‹መንግሥት ፖለቲካዊ ውሳኔ መስጠት አለበት›› ለሚለው አስተያየት በሰጡት ምላሽ፣ ክልሎች የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት አለባቸው፣ በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ፌደራል መንግሥት ጣልቃ መግባት አይችልም፤ ጣልቃ ከገባ ሕገ መንግሥቱን መጣስ ይሆናል፤›› ካሉ በኋላ ያለባቸው ችግር ተጠንቶ ለውይይት ከቀረበ በውይይት ላይ በማንሳት የሚስተካከልበትን ሁኔታ መፈለግ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ 
የፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በተለይ በአገልግሎት ዘርፍ የሚታዩትን ብልሹ አሠራሮች እስከ ወረዳ ድረስ ወርዶ መከታተል እንዳለበትም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በፍርድ ቤቶች የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት በተለያየ ምክንያቶች እየተጓተተና ሕዝቡ እየተማረረ እንደሚገኝ፣ መከሰስ የሌለበት ሰው ተከሶ ሲንገላታ ከከረመ በኋላ ነፃ መባሉ ደግሞ አግባብ አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የክስ አመሠራረት ብቃት እንደሚጎድለውና ሌሎችም ይታያሉ የተባሉ ችግሮች በውይይቱ ተነስተዋል፡፡ ውይይቱን ከአቶ አስመላሽ ጋር በመሆን የመሩት ኮሚሽነር ዓሊ ሱሌይማን ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፈደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎን ጨምሮ የተወሰኑ ተቋማት ተወካዮች በስብሰባው ታድመዋል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

Israel Eshetu back to his childhood club

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት