የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብ ትዝብት ውስጥ እንዳይወድቁ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደውን አምስተኛ ዙር አገር አቀፍ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጓል፡፡
ቦርዱ የፊታችን ግንቦት የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ ለማካናወን የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ የሚያደርጉበት፣ መራጮች የሚመዘገቡበት፣ ምርጫው የሚካሄድበትና ውጤቱ ይፋ የሚደረግበት የጊዜ ሰሌዳ ታውቋል፡፡ 
ምርጫው ሊካሄድ ሰባት ወራት የቀሩት ሲሆን፣ በአገሪቱ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ምርጫ ለመሳተፍ፣ የቻሉትን ለማሸነፍ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን የሚያዘጋጁበት፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ ለመጀመር የቤት ሥራቸውን የሚያጠናቅቁበትና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን የሚያሟሉበት ጊዜ ነው፡፡ ወቅቱ የምርጫ በመሆኑ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብ ትዝብት ውስጥ እንዳይወድቁ ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡ 
እስካሁን አራት አገር አቀፍ ምርጫዎች በአገሪቱ የተካሄዱ ቢሆንም፣ ምርጫ 97 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጥሎት ያለፈው ትዝታ ግን የሚረሳ አይደለም፡፡ በአገሪቱ ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ታዳጊ የሚባል ቢሆንም፣ በምርጫ 97 ታይቶ የነበረው የተስፋ ጭላንጭል የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ዕድገት ያፋጥነዋል ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ያለመታደል ሆኖ በወቅቱ የነበረው የሕዝብ እንቅስቃሴ በቀጣዩ የ2002 ዓ.ም. ምርጫ ሳይታይ ቀረ፡፡ ሳይሟሟቅና ግለቱ ሳይሰማን አለፈ፡፡ ለዚህ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ የነበሩት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ 
በቅርቡ እንደሰማነው ዘጠኝ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር መሥርተዋል፡፡ ትብብሩን የመሠረቱት የተቃዋሚ ፓርቲዎች የትብብሩ ዓላማ ነፃ፣ ፍትኃዊና ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ ብሎም የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በእርግጥ ሁልጊዜም ቢሆን አንድነትንና ትብብርን የሚጠላ አካል የለም፡፡ ነገር ግን ሊጣመሩ የማይችሉ ወገኖች ሲጣመሩ ኋላ ላይ ኪሳራው ከፍተኛ ይሆናል፡፡ በተለይ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል መርህ ብቻ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲጣመሩ የመጨረሻ ውጤታቸው እንደማያምር ምርጫ 97 ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ በወቅቱ በፖለቲካ መርሃቸው አንድ ላይ የማይሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገዥው የኢሕአዴግ ፓርቲን በአንድነት ሆነው ከሥልጣን ለማስወገድ የፈጠሩት ቅንጅት፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ይዘት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሷል፡፡ እንደሚታወሰው በምርጫ 97 ማግስት በተፈጠሩ አለመግባባቶች በርካታ ዜጐች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ እያደገ የነበረው የዴሞክራሲ ሥርዓትም ቁልቁል እንዲመለስ አድርጐታል፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጥምረትና አንድነት በሚያደርጉበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ 
ጥምረታቸውም በመርህ ላይ የተመሠረተና በርዮተ ዓለም የተጣጣመ መሆን አለበት፡፡ በመሆኑም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ካለፉት ምርጫዎች ትምህርት በመውሰድ አሁንም የሕዝብ ትዝብት ውስጥ እንዳይገቡ ይጠንቀቁ፡፡ 
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሌላው ችግር በውስጣቸው ያለው ሽኩቻ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች ቤታቸው ውስጥ ያለው መቃቃር ለራሳቸው ጠላት እየሆነባቸው ነው፡፡ ፓርቲዎቹም ጠንካራ እንዳይሆኑ ከማድረጉም ባለፈ፣ ሕዝቡ እንዲታዘባቸው ዕድል ፈጥሯል፡፡ 
በቅርቡ እንኳ ከአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የአንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት ከሥልጣናቸው መልቀቃቸውን ሲያስታውቁ፣ ፓርቲው በሁለት ጐራ ተከፍሎ ታይቷል፡፡ ፓርቲው ወዲያውኑ ምርጫ በማካሄድ የፕሬዚዳንቱን ተተኪ ቢሾምም፣ በሌላ በኩል ግን የቀድሞ ፕሬዚዳንቱን ከሥልጣን መልቀቅ በመቃወም ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ ያቀረበ ወገን ነበር፡፡ እንግዲህ ፓርቲው ለምርጫ በዝግጅት ላይ ነኝ በሚልበት ዋዜማ እንዲህ ዓይነት ንትርክ ውስጥ መግባቱ በሕዝብ ዘንድ ትዝብት ውስጥ ይጥላል፡፡ 
ከዚህም ባለፈ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚፈጥሯቸው ጥምረቶች ይኸው የእርስ በርስ ሽኩቻቸው ቀጥሏል፡፡ በመድረክና በአንድነት መካከል ያለው አለመግባባት እየሰፋ መምጣቱም ሌላው ማሳያ ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ያለባቸውን የውስጥ አለመግባባት በመፍታት ራሳቸውን አጠናክረው ካልወጡ፣ አሁንም ትዝብት ውስጥ ይወድቃሉ፡፡ 
እዚህ ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔዎቻቸውን በወቅቱ በማካሄድ የሚያራምዱት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ፣ ፓርቲዎቹን የሚያስመሰግንና በዚሁ ቀጥሉበት የሚያስብል እንደሆነ ግን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ሆኖም ለቀጣዩ ምርጫ የቤት ሥራቸውን በሚገባ ሊሠሩ ይገባል፡፡ ካለፉት ምርጫዎች ትምህርት በመውሰድ፣ ከሕዝብ ትዝብት ራሳቸውን በማዳን፣ በአገሪቱ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ የራሳቸውን ሚና ይጫወቱ፡፡ 
ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም በሕዝብ ትዝብት ውስጥ እንዳይወድቅ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ ኢሕአዴግ የፖለቲካ ምኅዳሩን በማጥበብ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይወቅሳሉ፡፡ ኢሕአዴግ ገዥ ፓርቲ ከመሆኑም በላይ መንግሥት እንደመሆኑ መጠን ለአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር መጥበብ ተጠያቂ ነው፡፡ 
ምርጫ በደረሰ ቁጥር ተቃዋሚ ፓርቲዎችና አባሎቻቸው ከፍተኛ ወከባና ጫና እንደሚያደርስባቸው ይገልጻሉ፡፡ ምንም እንኳ ኢሕአዴግ በአገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲሰፍን ተግቼ እየሠራሁ ነው ቢልም፣ ይህ ግን ከቃል ባለፈ በተግባር አይታይም፡፡ ኢሕአዴግ በአገሪቱ ካሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ሲወያይ አይታይም፡፡ በአገሪቱ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ እንደሌለ ኢሕአዴግ ራሱ ቢናገርም፣ ለዚህ ችግር ግን ራሱ ከተጠያቂነት አያመልጥም፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰላማዊ ሠልፍ፣ ሕዝባዊ ስብሰባና መሰል ተግባራትን ለማካሄድ ሲንቀሳቀሱ የተለያዩ መሰናክሎች ይፈጠራሉ፡፡ መንግሥት በትንሹም በትልቁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባሎችን ያስራል፡፡ ለሚያቀርቧቸው ጥያቄዎችም ተገቢውን ምላሽ አይሰጥም፡፡
ኢሕአዴግ ገዥ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በበለጠ ለአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዋነኛ ተጠያቂ ነው፡፡ ኃላፊነትም አለበት፡፡ ስለዚህ በመጪው ምርጫ ተሳታፊ ለሚሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምኅዳሩን ሊያሰፋ ይገባል፡፡ ገዥው ፓርቲ ከበፊት ምርጫዎች ትምህርት በመውሰድ ራሱን ከሕዝብ ትዝብት ያድን፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብ ትዝብት ውስጥ አንዳይገቡ ይጠንቀቁ፡፡  

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር