በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲያዊ አገልግሎት ምደባ ወደ ፖለቲከኞች እያዘነበለ ነውን?
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለትችት ከዳረጓቸው ጉዳዮች መካከል የአሜሪካ የውጭ ዲፕሎማሲ ሥራ ላይ የሚመድቧቸው ሰዎች ማንነት አንዱ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ እ.ኤ.አ. በ2012 ለድጋሚ ፕሬዚዳንትነት በተወዳደሩበት ወቅት ለቅስቀሳ ከፍተኛ ገንዘብ ሲያሰባስቡ የነበሩ ግለሰቦች ፕሬዚዳንት ኦባማ በድጋሚ ወንበራቸውን ካገኙ በኋላ የተወሰኑት በተለያዩ አገሮች በአምባሳደርነትና በዲፕሎማትነት ተመድበዋል፡፡
ለምሳሌ በቅርቡ በአምባሳደርነት የተመደበው ማቲው ባርዙን ለፕሬዚዳንቱ የምርጫ ቅስቀሳ ወጪ ከተሰበሰበው 700 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 2.3 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነውን በግሉ አሰባስቧል፡፡
በተመሳሳይ ጆን ፊሊፕስ ለኦባማ የምርጫ ዘመቻ 500 ሺሕ ዶላር ከሰበሰበ በኋላ በጣሊያን ሮም የአሜሪካ ዲፕሎማት ሆኖ ተመድቧል፡፡ ጆን ኤመርሰን 1.5 ሚሊዮን ዶላር ያሰባሰበ ሲሆን፣ የተመደበው ጀርመን በሚገኘው ኤምባሲ ነው፡፡ ጄን ስቴትሰን 2.4 ሚሊዮን ዶላር አሰባስቦ፣ የተመደበው በፈረንሳይ ፓሪስ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የአሜሪካ ፕሮፌሽናል ዲፕሎማቶች ማኅበርና ጡረታ የወጡ የአገሪቱ አምባሳደሮች የፕሬዚዳንት ኦባማን ድርጊት ከመውቀስ አልፈው ‹‹የመንግሥት ቢሮን የመሸጥ ያህል ነው›› በማለት ድርጊቱን ተችተዋል፡፡
ይህ ዓይነቱ የፈጠጠ የጥቅም ግንኙነት ያለበት የውጭ ዲፕሎማቶች አመዳደብ በኢትዮጵያ ባይስተዋልም የግለሰቦችን ነፃነት የሚጋፋ አካሄድና በሕግ የማይመራ አመዳደብ ለበርካታ ዓመታት ሥር ሰዶ የከረመ እንደነበር የተወሰኑ ዲፕሎማቶች ይናገራሉ፡፡
በተለይ በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ፈተና ውስጥ ገብቶ የነበረ መሆኑን የተገነዘበው ገዥው ፓርቲ ከገባበት አጣብቂኝ ከወጣ በኋላ የአባላቱን ቁጥር ለማብዛት በገጠር፣ በክልል ከተሞችና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በትምህርት ቤቶች ሲንቀሳቀስ የውጭ ግንኙነት መዋቅሩንም እንዳልተወው በወቅቱ በዲፕሎማሲ ሥራ ውስጥ የነበሩ ገልጸውታል፡፡
የገዥው ፓርቲ አባል በመሆን ወራዊ ክፍያ እያዋጡ እንዲቀጥሉ በመገደዳቸው ሥራቸውን ጥለው በተመደቡበት አገር ጥገኝነት ጠይቀው የቀሩ ስለመኖራቸውም አስተያየት ሰጪዎች ጠቁመዋል፡፡
ልማዳዊ የውጭ ግንኙነት
በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት በውጤታማነቱና በዘመናዊነቱ ከተጠራ በንጉሡ ዘመን የነበረው ወደር የለውም ሲሉ የሚከራከሩ አሉ፡፡
የውጭ ግንኙነት ትምህርትን በተለያዩ የውጭ አገሮች እንዲቀስሙ ተልከው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን የተደራጀ የዲፕሎማሲ ሥራ ይከውኑ እንደነበር በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ የሚገኙ አምባሳደሮች ይናገራሉ፡፡ የዲፕሎማሲ ሥራ በዕውቀትና በልምድ የተጠናከረ በመሆኑም በወታደራዊው ሥርዓት ወቅት ምንም እንኳን የርዕዮተ ዓለም መሠረታዊ ለውጥ ቢኖርም መቀጠላቸውን ይናገራሉ፡፡ የእነዚህ አንጋፋ ዲፕሎማቶች አገልግሎት የኢሕአዴግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ መቀጠል አልቻለም፡፡ በምትኩ በደርግ አገዛዝ ተገፍተው በውጭ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንና በኢሕአዴግ ትግል ውስጥ የተሳተፉ በአብዛኛው መመደባቸውን አንዳንድ ጽሑፎች ያስገነዝባሉ፡፡
ኢሕአዴግ በሥልጣን ቆይታው ልምድ እያካበተ በመጣ ቁጥር ይህ ዘመናዊ ያልሆነ አሠራር ይለወጣል የሚል እምነት በፓርቲው ውስጥ እንዲሁም በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ ቢኖርም፣ በፓርቲ ሥራ ላይ እንዲሁም በመንግሥት ሥራ አስፈጻሚነት ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ ግለሰቦች በዲፕሎማሲ ሥራው ላይ መመደብ ቀጥሏል፡፡
በተለይ ከ2002 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ በአምባሳደርነትና በዲፕሎማት የተመደቡ 36 ግለሰቦች ይህንኑ ልማዳዊ አሠራር ፍንትው አድርጐ የሚያሳይ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በወቅቱ በነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቅራቢነት የተሾሙት አምባሳደሮች፣ ከሹመታቸው ቀደም ብለው በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ ይህም ማለት የአጭር ጊዜ ሥልጠናዎችን አገኙ እንጂ ‹‹ኬርየር ዲፕሎማት›› (የረዥም ጊዜ የዲፕሎማሲ አገልግሎት ልምድና ዕውቀት ያላቸው) አልነበሩም፡፡ ከዚህ ባለፈም በባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ማዕረግ፣ በልዩ መልዕክተኛና በአምባሳደርነት ማዕረጐች የተለያዩ ግለሰቦች በአንድ አገር ተመድበዋል፡፡
በ2004 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ግን ይህንን ልማዳዊ የዲፕሎማቶች ምደባ ለማስቀረት በፍጥነት መንቀሳቀስ መጀመራቸው ይነገርላቸዋል፡፡
ለአብነት ያህልም ዶ/ር ቴድሮስ ወደ ውጭ ጉዳይ ከመምጣታቸው አንድ ዓመት ቀደም ብሎ የተሾሙ 36 አምባሳደሮች ሁኔታን በማጥናት 18 የሚሆኑት ዲፕሎማቶች ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡ በዚያው ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለማቅረብ ፓርላማ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ 18ቱ አምባሳደሮች ለምን እንደተመለሱ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀው ነበር፡፡
ከተጠሩት 18 አምባሳደሮች መካከል ሁለቱ በድጋሚ በሌላ ቦታ መመደባቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የተጠሩበት ምክንያት ዲፕሎማቶቹ ያለ አግባብ በአንድ ቦታ በመደራረባቸውና ይህም የሥራ መደናቀፍን የፈጠረ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
‹‹በአንድ አገር ሁለት አምባሳደር ሊኖር አይችልም፡፡ ሊኖር የሚችልበት ምክንያት የሚመደቡበት አገር እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገኙ ከሆነና በመንግሥት በኩል እንደነዚህ ያሉ ተቋማት በአምባሳደሮች እንዲወከሉ ከተፈለገ ነው፡፡ ነገር ግን ሹመቱ የተሰጠው በዚህ አግባብ አልነበረም፡፡ ለበጐ ዓላማ የተሰጠ ሹመት ቢሆንም ስህተት በመሆኑ ተጠርተዋል፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ይህንን ልማዳዊና ባህላዊ አሠራር ማስቀረት የሚቻለው የዲፕሎማቶች አመዳደብ በዕውቀት፣ በችሎታና በውድድር ላይ የተመሠረተ ሥርዓት መፍጠር ሲቻል ነው፡፡
ከዶ/ር ቴድሮስ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት መምጣት በኋላ ዘመናዊ የውጭ ግንኙነት ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተረቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2005 ዓ.ም. ቀርቦ ፀድቋል፡፡ ይህ አዋጅ ‹‹ስለ ውጭ ግንኙነት የወጣ አዋጅ›› የሚል መጠሪያ የተሰጠውና ዓላማውም የውጭ ግንኙነት አገልግሎቱ ወጥነት ባለውና በተቀናጀ ተቋማዊ የአሠራር ሥርዓት ለማስተዳደር በመፈለጉ መሆኑን የአዋጁ መግቢያ ያብራራል፡፡
የአዋጁ መግቢያ እንደሚያስረዳው ሙያዊ አቅሙ፣ ብቃቱና ክህሎቱ የዳበረና የተጣለበትን አገራዊ ተልዕኮ በታማኝነትና በቁርጠኝነት የሚወጣ ጠንካራ የሰው ኃይል ማፍራት ትልቅ ግብ ነው፡፡
አዲሱ የውጭ ግንኙነት አዋጅ ምን አመጣ?
ዘሪሁን መገርሳ ይባላል፡፡ የ27 ዓመት ወጣት ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት በሠልጣኝ ዲፕሎማትነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤትን ተቀላቅሏል፡፡
በ2004 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በሔራልድ ጋዜጣ ላይ በወጣ ማስታወቂያ መሠረት ማመልከቻውን እንዳስገባ የሚናገረው ወጣት ዘሪሁን፣ ልክ እንደእርሱ ያመለከቱ ወጣቶች ብዛት 680 እንደነበሩ ያስታውሳል፡፡ በወቅቱ ካመለከቱት ወጣቶች ለቃል ፈተና የተጠሩት ደግሞ እርሱን ጨምሮ 108 እንደነበሩ በመጨረሻም ሁሉን መስፈርት ማሟላት የቻሉት 50 እንደነበሩ ያስታውሳል፡፡
ከዚያ በኋላም በሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሥር በሚገኘው የዲፕሎማቶች ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ውስጥ የፖሊሲና ስትራቴጂ ሥልጠና ለሁለት ወራት ከወሰዱ በኋላ ለቀጣይ ስምንት ወራት ደግሞ የዲፕሎማሲ ሥልጠና ማግኘታቸውን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ ዓለም አቀፍ ሕጐች፣ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አደረጃጀት፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጨምሮ በአጠቃላይ 24 ኮርሶችን መውሰዳቸውን ይገልጻል፡፡ እነዚህ ሥልጠናዎች ከእንግሊዝ፣ ከህንድ፣ ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ጡረታ ከወጡ አምባሳደሮች በተውጣጡ አሠልጣኞች የተሰጡ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በብሪቲሽ ካውንስል አማካኝነት ‹‹ዲፕሎማቲክ ኢንግሊሽ›› የተሰኘ በዲፕሎማሲ ቋንቋ ላይ ያተኮረ ሥልጠና ወስደዋል፡፡
ዘሪሁን በሲቪክስና ሥነ ምግባር ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘ ቢሆንም፣ ወደ ዲፕሎማሲው መስክ ለመግባት የ12 ወራት ሥልጠናን ማግኘት የግድ ብሎታል፡፡ በዚህ ብቻ ሳያበቃ ዘሪሁን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ተመድቦ የሥራ ላይ ሥልጠና ለአንድ ዓመት ወስዷል፡፡ ዘሪሁን በአሁኑ ወቅት በዚሁ ክፍል ውስጥ በቋሚነት በአታሼ ደረጃ ተመድቦ የዲፕሎማሲ ዘመኑን መቁጠር ጀምሯል፡፡ ስለውጭ ግንኙነት የወጣው አዋጅም ‹‹የኬርየር ዲፕሎማትን›› ማፍራት የሚችለው በዚህ መልኩ መሆኑን ያስረዳል፡፡
አዋጁ የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ዘርፎችን ከፍተኛ፣ መካከለኛ፣ መጀመሪያና የቆንስላ አገልግሎት ምድብ በማለት በአራት ደረጃ ይከፍላቸዋል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የዲፕሎማቲክ አገልግሎት ምድብ ሁለተኛና ሦስተኛ ጸሐፊዎችና አታሼዎች የሚገኙበት ነው፡፡ በከፍተኛው ደረጃ ላይ ደግሞ አምባሳደሮች፣ ልዩ መልዕክተኞችና ሁለገብ አምባሳደሮች የሚመደቡበት ነው፡፡
ይህ አዋጅ ከወጣ በጥቂት ወራት ውስጥ ስምንት አምባሳደሮች የተሾሙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ በርካቶቹ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት ያገለገሉ ቢሆንም ‹‹ኬርየር አምባሳደር›› መባል የሚችሉ አይደሉም፡፡ ከዚያ በኋላም የቀድሞ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው ጐበዜና የማዕድን ሚኒስትሯ ወ/ሮ ስንቅነሽ እጅጉ በአምባሳደርነት ተሹመዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ደግሞ በኢሕዴድ መሥራችነትና ታጋይነት እንዲሁም በተለያዩ የመንግሥት ተቋማትና የክልል ፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት አቶ ኩማ ደመቅሳ እንዲሁም ለ15 ዓመታት ገደማ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ወ/ሮ ሳሚያ ዘካሪያና ሌሎች አራት ግለሰቦች በአምባሳደርነት ተሹመዋል፡፡
የተቀሩት አራቱ ማለትም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዳይሬክተር ጄኔራልነት ሲያገለግሉ የነበሩት አምባሳደር ግሩም ዓባይ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የነበሩት አምባሳደር ዲና ሙፍቲና የተቀሩት ሁለቱ አምባሳደር ነጋሽ ክብረትና አምባሳደር ዋህድ በላይ ከ20 እስከ 35 ዓመታት በተለያዩ ኃላፊነቶች በዲፕሎማትነት ያገለገሉ ‹‹ኬርየር አምባሳደሮች›› ናቸው፡፡
በጉዳዩ ላይ ለሚዲያ የመናገር ኃላፊነት እንደሌላቸው በመግለጽ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የውጭ ጉዳይ የረዥም ጊዜ አምባሳደር፣ ኢትዮጵያ ሁለቱንም ዓይነት የፖለቲካ ሹመትንም በዲፕሎማሲ ሙያ ላይ የቆዩትንም በውጭ አገልግሎት ላይ ትመደባለች ይላሉ፡፡ ይህ አቋም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚደገፍ ነው፡፡
‹‹በፖለቲካ የሚመደቡ አምባሳደሮች ለረዥም ጊዜ የመንግሥትን ፖሊሲ ሲያስፈጽሙ የቆዩ በመሆናቸው የአጭር ጊዜ የዲፕሎማሲ ሥልጠና ወስደው እንዲመደቡ ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም የፖሊሲ ሥልጠና በአጭር ጊዜ ሰጥቶ አምባሳደር ማድረግ ስለማይቻል፤›› በማለት አቶ ጌታቸው ያስረዳሉ፡፡
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ ‹‹ኬርየር ዲፕሎማቶች›› በተለይ ‹‹ጥልቅ የሆነ የዲፕሎማሲ ሥራ የሚጠየቅባቸው እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሚገኙባቸው አገሮች ይሾማሉ፡፡ የመንግሥት ፍላጐት ለምሳሌ ዳያስፖራውን ማንቀሳቀስ ከሆነ በፖለቲካ ሹመት የሚመደብ አምባሳደር ይኖራል፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
በአጠቃላይ ይህ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት አዋጅ ከወጣ በኋላ በይፋ የተመደቡ አምባሳደሮች ብዛት 16 ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አራቱ ብቻ ‹‹ኬርየር ዲፕሎማት›› የሚባሉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሌሎች ስምንት የሚሆኑትም በዲፕሎማሲው መስክ የተሻለ አገልግሎት ያላቸው በመሆኑ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት በሥርዓት መመራት ጀምሯል ማለት ይቻላል፡፡
‹‹ሥልጠናውን አልፈን በውጭ ጉዳይ ከተመደብን በኋላ ሥርዓቱን ስናየው ቀድሞም በዚህ መልኩ ነበር መሆን የነበረበት አስብሎናል፤›› በማለት ዘሪሁን አሁን ያለው ሥርዓት ልምድ ያላቸውን ዲፕሎማቶች ለማፍራት እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
‹‹በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ በአምባሳደርነት የምመደብ ይመስለኛል፡፡ ከሆነልኝ የምፈልገው በቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት በአምባሳደርነት መመደብ ነው፤›› በማለት ዘሪሁን ምኞቱን ይገልጻል፡፡
አሜሪካ ‹‹ፎሪን ሰርቪስ አክት›› የሚል ስያሜ ያለው የዲፕሎማት አመላመልና ምደባን የሚመራ ሕግ ቢኖራትም፣ ሹመት የመስጠት ኃላፊነቱ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በሥራ አስፈጻሚ የበላይ የሚፈጸም በመሆኑ የምርጫ ዘመቻ አስተባባሪዎችን ለመካስ በአምባሳደርነት በመሾም ተመዝብሯል፡፡ በኢትዮጵያ አሁን እየተፈጠረ ያለው ሥርዓትን ከዚህ መሰሉ አደጋ መጠበቅ ለዘመናዊ የዲፕሎማሲ አገልግሎትና ውጤት ትልቅ መሠረት መሆኑ የሚያሻማ አይደለም፡፡
Comments
Post a Comment