የዋሊያዎቹ ዕጣ ፈንታ ዛሬ በአልጀሪያ ይወስናል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወሳኙን የማጣሪያ ጨዋታውን ከአልጀሪያ ጋር ለማድረግ 20 ተጨዋቾችን በመያዝ ወደ ስፍራው አቅንቷል፡፡
ዋሊያዎቹ በጨዋታው ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው መመለስ ካልቻሉ አስተናጋጁ ሀገር ያልታወቀውን የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ዕድሉ አይኖራቸውም፡፡
ዋሊያዎቹ አልጀሪያን ማሸነፍ ከቻሉና ማላዊ ማሊን ነጥብ ማሳጣል ከቻለች ለዋሊያዎቹ  መልካም ዜና ይሆናል፡፡
አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ በአልጀርስ ድል ካልቀናቸው ግን የዋሊያዎቹ የ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ከማጣሪያ ጨዋታ ያልዘለለ ይሆናል፡፡
ከምድቡ 12 ነጥብ በመሰብሰብ አስቀድማ ማለፏን ያረጋገጠችው አልጀሪያ ጨዋታውን ለመርሃ ግብር ስትል ታደርጋለች፡፡
አልጀሪያ ባለፈው መስከረም አዲስ አበባ ላይ ዋሊያዎቹን 2ለ1 ማሸነፏ ይታወሳል፡፡
ዋሊያዎቹ ባለፈው አልጀሪያን ከገጠመው ቡድን የ8 ተጨዋቾች ለውጥ አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የፊት መስመር አጥቂዎቹ ሳልሃዲን ሰኢድ በጉዳት እንዲሁም ጌታነህ ከበደ በቅጣት እናበአሰልጣኙ ዕይታ ብቁ ያልሆነው አማካኙ አዳነ ግርማ ይገኙበታል፡፡
አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ባለፈው ሳምንት በኡጋንዳ 3ለ0 ከተሸነፉ በኋላ 5 ተጨዋቾችን ቀንሰዋል፡፡
ዴቪድ በሻህ፣ ሄኖክ ካሳሁን፣ ፉዋድ ኢብራሂም፣ ምንተስኖት አዳነ፣ ኤፍሬም አሻሞ እና እንዳለ ከበደ   የተቀነሱ ተጨዋቾች ናቸው፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊሱ ፋሲካ አስፋው ዋሊያዎቹን የተቀላቀለ አዲስ አባል ሆኗል፡፡ በጨዋታው ኡመድ ኡክሪ በጉዳትና በቅጣት የሳሳውን የፊት መስመር በበላይነት እንደሚመራው ይጠበቃል፡፡
ጨዋታው ዛሬ ምሽት በሱፐር ስፖርት 3 በቀጥታ ይተላለፋል፡፡
ምንጭ፦ ኢብኮ

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር