ከዶ/ር አንበሴ ተፈራ የምርምር ስራዎች መካከል...

የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችና ቋንቋዎቻቸው አጭር ቅኝት

( የዚህ አጭር ጽሁፍ አዘጋጅ ዶ/ር አንበሳ ተፈሪ ሲዳማ ውስጥ ይርባ በምትባል ቦታ በ1962 ተወለዱ።በ1984 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፡ በ1987 ደግሞ ሁለተኛቸውን፡ በቋንቋ ጥናት ተቀበሉ።ከ1984 ጀምሮም፡ ወደ እስራኤል እስከተሰደዱበት 1990 ድረስ፡በተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በመምህርነት አገልግለዋል።ከ1990 ጀምሮ ደግሞ በእስራኤል በተለያየ ቦታ በሚገኙ፡ ዩኒቨርስቲዎች፡እንዲሁም)የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ጭምር አማርኛንና የቋንቋ ጥናትን አስተምረዋል።መልካም ንባብ!)

ኢትዮጵያ በተለምዶ 3 ሺ ዘመን ታሪክ ያላት ሲሆን በአንዳንድ ታሪካዊና የአርኪኦሎጂያዊ ቁፋሮ መረጃዎች ግን ይህ ታሪካዊ ዕድሜ እስከ 5 ሺ ዓመት ሊደርስ ይችላል። ይህቺ ረጅም ታሪክ ያላት አገር በአሁኑ ጊዜ በኦፊሲዬላዊነት 73 “በሕይወት ያሉ” ቋንቋዎች አሏት።

የኢትዮጵያ 73 ቋንቋዎች የሚመደቡት በ2 የቋንቋ ቤተሰቦች ውስጥ ነው።እነዚህም አፍሮ-እስያዊ እና ኒሎ-ሰሐራዊ (ዓባይ-ሰሐራዊ) ናቸው። አፍሮ እስያዊ ቋንቋዎች በሰሜን አፍሪቃና በደቡብ ምዕራብ እስያ የሚነገሩ ሲሆን 6 ንዑሳውያን ቤተሰቦች አሉት። እነዚህም ጥንታዊ ግብጽ፣ በርበር፣ ቻዳዊ፣ ኩሻዊ (ሐማዊ)፣ ኦሞአዊና ሴማዊ ቋንቋዎች ናቸው። ከእነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ውስጥ 3ቱ ማለትም ጥንታዊ ግብጽ፣ በርበር እና ቻዳዊ በኢትዮጵያ የማይነገሩ ሲሆን የተቀሩት 3ቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ይነገራሉ። እነዚህም ኩሻዊ (ሐማዊ)፣ ኦሞአዊና ሴማዊ ቋንቋዎች ናቸው። በዕድሜ ረገድ ኩሻዊና ኦሞአዊ ጥንታዊ ቋንቋዎች ሲሆኑ ሴማዊ ቋንቋዎች ከእነሱ ቀጥለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ናቸው።

ሴማዊ ቋንቋዎች የሚባሉት ግዕዝ፣ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ የጉራጌ ቋንቋዎች፣ አርጐባ፣ ሐረሪ (አደርኛ)፣ ናቸው። ግዕዝ በአሁኑ ጊዜ የማይነገር ቢሆንም ዋነኛ አገልግሎቱ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ነው። የሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪዎች በተለይም የአማርኛና ትግርኛ ተናጋሪዎች በኢትዮጵያ ታሪክ ሂደት በተለይም በጦር አመራርና አስተዳደር ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፣ በመጫወትም ላይ ናቸው። በተጨማሪም ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ሀገሮች የተለየ የሚያደርጋት የጽሕፈት ሥርዓት ከሴማውያን ቋንቋዎች የተገኘ ነው። ከሌሎቹ ቋንቋዎች ሲወዳደር ስለሴማዊ ቋንቋዎች አመጣጥ በድፍረት መናገር ይቻላል። ምክንያቱም በሰሜን ኢትዮጵያ ድንጋይ ላይ የተቀረጹ ጽሑፎችና ሌሎችም ማስረጃዎች ስላሉ ነው። በግምት የዛሬ 3 ሺህ ዓመት የተለያዩ የሳባውያን ነገዶች ከየመን እና ደቡብ አረቢያ በመነሣትና ቀይ ባሕርን በመሻገር ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፈሩ። ከእነዚህም ነገዶች አንዱ ሐበሻት የሚባል ሲሆን ይህም ስም ሐበሻ ለሚለው ቃልና ቀድሞ የኢትዮጵያ ስም ለሆነው አብሲኒያ ምንጭ ሆኗል። በሳባውያን ቋንቋና በጊዜው ሰሜን ኢትዮጵያ ይነገሩ በነበሩ ቋንቋዎች ዘገምተኛ ውኅደት ግዕዝ ሊወለድ በቃ። ግዕዝ ከአማርኛና ሌሎች ኢትዮ-ሴማዊ ቋንቋዎች ጋር ሲወዳደር “ንጹሕ” ሴማዊ ቋንቋ ነው። ግዕዝ የአክሱም ዘመነ መንግሥት ቋንቋ ሲሆን እስከ 10ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ዋነኛ የመግባቢያ ቋንቋና ልሳነ ንጉሥ ነበር። ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ግን ሙሉ በሙሉ መነገር አቆመ።

ግዕዝ እስከከሰመበት ጊዜ ድረስ ከፍተኛ አገልግሎት ነበረው። ዛሬም ቢሆን ግዕዝን “ሕያው” ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ። ምክንያቱም ግዕዝን አፍ መፍቻቸው ያደረጉ ልጆች ስለሌሉ በደረቅ ሥነ-ልሳናዊ አመለካከት “ለዘላለም አሸልቧል” ቢባልም የኢትዮጵያ ቤተ-ክህነት ሆነች እንደዚሁም የኢትዮጵያውያን ይሁዲ ቄሶች ለጸሎት የሚጠቀሙበት እንደዚሁም እስካሁን ድረስ ቅኔ የሚዘረፍበት/የሚቀኝበት ቋንቋ በመሆኑ ነው። አንዳንድ ሰዎች “ግዕዝን ለልጆች የአፍ መፍቻ በማድረግ ሕያው እንዲሆን ማድረግ ይቻላል” ብለው ሐሳብ ያቀርባሉ። ለዚህም በምሳሌነት የሚያቀርቡት፣ ብዙም ርቀን ሳንሄድ እዚህ እስራኤል አገር የሚነገረውን ዕብራይስጥን ነው። ከዛሬ 125 ዓመት በፊት ዕብራይስጥ የንግግር ቋንቋ አልነበረም። ለኤሊኤዜር ቤን-ይሁዳ ታላቅ ምሥጋና ይግባውና ዛሬ ሕይወት ዘርቶ በእስራኤል ውስጥ ለመነጋገሪያ ብቻ ሳይሆን የከፍተኛ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቋንቋ በመሆኑ ሁሉም የዩኒቬርሲቲ ትምህርቶች የሚሰጡት በዕብራይስጥ ነው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አብዛኛዎቹ ሠለጠኑ የሚባሉ ሀገሮች (አሜሪካ ፣ አውሮፓ ፣ ጃፓን ፣ እስራኤል ፣ ኮሪያ ወዘተ.) የራሳችውን ቋንቋዎች የሚጠቀሙ መሆናቸው ታውቋል። ስለሆነም “የአፍሪካ ሀገሮች የአውሮፓ (ቅኝ) ቋንቋዎችን ከሚኮርጁ የየራሳቸውን ቋንቋዎች ቢያዳብሩና ቢጠቀሙ ለዕድገታቸው አስተማማኝ መሠረት ይጥላሉ” በሚል ባለፈው ነሐሴ ወር አዲስ አበባ ላይ የተካሄደው 5ኛው የአፍሪካ ሥነ ልሳን ምሁራን ኮንግሬስ ውሳኔ አውጥቷል።

ግዕዝ ከ13ኛ ክፍለ ዘመን ጀምሮ መነገር በማቆሙ ቀሰ በቀስ በሰሜን ትግርኛ፣ በማዕከላዊው ክፍል ደግሞ አማርኛ የግዕዝን ቦታ ያዙ። አብዛኞቹ የሥነ ልሳን ምሁራን አማርኛና ትግርኛ በቀጥታ ከግዕዝ የተወለዱ ናቸው ሲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ሁለቱ ቋንቋዎች የተወለዱት ከግዕዝ ሳይሆን ከሌላ የግዕዝ ቋንቋ እኅት ከነበረና ምንም ማስረጃ ትቶ ካላለፈ ሌላ ቋንቋ ነው ይላሉ። አማርኛ ልሳነ ንጉሥ የሆነው በ1272 ዓ.ም. ከዛጔ ሥርወ መንግሥት በኋላ አጼ ይኩኖ አምላክ ሰሎሞናዊውን ሥርወ መንግሥት መልሶ ሲያቋቁም ነበር። አማርኛ ልሳነ ጽሑፍ መሆን የጀመረው በ14ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሲሆን ይህንንም ያደረገው ሁሉንም የግዕዝ ፈደላትን በመውሰድና 6 አዳዲስ የላንቃ ፊደላትን (ማለትም ሸ ሸ ፣ ቸ ቸ ፣ ኘ ኘ ፣ ዠ ፣ ጀ ጀ ፣ ጨ) እና ኸን በመጨመር ነበር። ነገር ግን በጽሑፍ ይበልጥ መስፋፋት የጀመረው ከአጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ ሲሆን ለዚህም በተለይ አስተዋጽኦ ያደረገው ጸሐፊያቸው ደብተራ ዘነብ ነው። አማርኛ በተለይ የተስፋፋው የዳግማዊ አጼ ምኒሊክን የግዛት ማስፋፋት ዘመቻ ተከትሎና እንዲሁም ዘመናዊ ትምህርት ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጀመረ በኋላ ነበር።

አማርኛ ከሴማዊ ቋንቋዎች ውስጥ ከዓረብኛ ቀጥሎ 2ኛ ሲሆን በአፍሪካ ውስጥ ደግሞ ከምዕራብ አፍሪካው ሐውሳና Ha_Huከምሥራቅ አፍሪካው ስዋሂሊ ቀጥሎ 3ኛውን ቦታ የያዘ ነው። አማርኛ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ሲሆን 5 ሚሊዮን ሰዎች እንደ2ኛ ቋንቋ ይናገሩታል። በታሪካዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሣ የኢትዮጵያውያን የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ( lingua franca ) ከሆነም ቆየት ብሏል።

ይሁን እንጂ እስከ 1992 ድረስ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና እንደዚሁም ብሔረሰቦች ተገቢው ቦታ አልተሰጣቸውም ማለት ይቻላል። የተለያዩ ብሔረሰቦች እነሱ የማይቀበሉት ስም የተሰጣቸው፣ ባህላቸው የተናቀ፣ ቋንቋቸውን ደግሞ በአደባባይ ለመናገር የሚፈሩ ነበሩ። ከ1993 ጀምሮ በወጣው አዲስ ሕገ-መንግሥት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የቋንቋ፣ ባህል፣ ኢኮኖሚና አስተዳደር ነጻነት በመታወጁና ልጆቹን በራሱ ቋንቋ ማስተማር ይችላል ስለተባለ ትምህርቶች እየተሰጡ ያሉት በ20 ያህል የብሔረሰብ ቋንቋዎች ነው። ይህ ውሳኔ ሁለት ጥቅሞች አሉት። የመጀመሪያው የብሔረሰቦችን እኩልነትና መሠረታዊ ዲሞክራሲ መብት ማስከበሩ ነው። ብሔር ብሔረሰቦች የሚከባበሩትና በእኩል ዓይን የሚተያዩት ቋንቋቸው፣ ባህልና ወጋቸው፣ የኢኮኖሚ መብታቸው፣ ወዘተ. ከሌላው ጋር እኩል ሲከበር ነው። ሌላው ደግሞ ዩኔስኮ ያወጣውን ውሳኔ ተግባራዊ ያደርጋል። በዩኔስኮ አመለካከት በ1ኛ ደረጃ ት/ቤት የሚማር ልጅ የመጀመሪያ ትምህርቱን በአፍ መፍቻ ቋንቋው ቢማር በጣም ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም የሚማረውና ትኩረቱን የሚሰጠው ለትምህርት ብቻ ስለሆነ ነው። የራሱ ያልሆነና ሌላ 2ኛ ቋንቋ በሚጠቀምበት ጊዜ ትምህርቱን ብቻ ሳይሆን 2ኛውን ቋንቋ ጭምር መማር ስላለበት በትምህርት ወደፊት አይራመድም። እርግጥ መታወቅ ያለበት አንድ ተማሪ አንድ የተወሰነ ክፍል ላይ ሲደርስ የአገሪቱን ፌዴራላዊ የሥራ ቋንቋ የሆነውን አማርኛን መማር ያስፈልገዋል። አለበለዚያ በኢትዮጵያውያን መካከል መግባባት አይኖርም እንደዚሁም የሚያስተሳስራቸው ነገር አይኖርም ማለት ነው።

ፕሮፌሰር ባየ ይማም “የአማርኛ ሰዋስው” (1986፡ ገጽ 4-5) በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደሚያስረዱት አማርኛ አሁን ያለው ብሔራዊ መልክ (ከተናጋሪዎቹ ብዛትና ሥርጭት አንጻር) የቋንቋውን ብሔራዊ ታሪክ ያንጸባርቃል።እንደእሳቸውና ሌሎቹ የሥነ ልሳን ምሁራን አማርኛ የተወለደው በሴማውያን መሪዎችና በካማውያን (ኩሻውያን) ወታደሮች መካከል በተፈጠረው ግንኙነት ሳቢያ ቋንቋዎቻቸው በመደባለቁ ነው። ስለሆነም አማርኛ ቅይጥ ቋንቋ (pidgin) እንጂ ንጹሕ ሴማዊ አይደለም። ለምሳሌ ያህል መሠረታዊ ቃላት ሳይቀሩ ከኩሽ (ካም) የተዋሳቸው ናቸው። ምሳሌ፡- ውሃ ፣ ውሻ ፣ ሰንጋ ፣ ወዘተ. ግሱ በዓረፍተ ነገር መጨረሻ ላይ ስለሚመጣ የዓረፍተ ነገር ቅርጹም ሴማዊ አይደለም። ይህም የሚያስረዳው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ብቻ ሳይሆኑ ቋንቋዎቹ ጭምር ረጅም የርስ በርስ ትስስር እንደነበራቸው ነው።

ከላይ እንዳየነው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ከተለያዩ የቋንቋ ቤተሰቦችና ንዑስ ቤተሰቦች ውስጥ የፈለቁ ቢሆንም ብዙ የሚያመሳስላቸው የቋንቋ ጠባያት አሏቸው።
ከእነዚህም አንዳንዶቹ፡-Ethiopia Languges
(1) በተራ እግድ ድምጾችና ፈንጂ ድምጾች መካከል ያለው የትርጉም ልዩነት
ምሳሌ፡- (ሀ) ነካ – - ነቃ (ለ) ነች – - ነጭ (ሐ) መታ – - መጣ
(2) በ“ አለ” ላይ የተመሠረቱ ግሶች
ምሳሌ፡-(ሀ) ዝም አለ ፣ ቀስ አለ ፣ ብድግ አለ (ለ) እመጣለሁ ብሎ ሳይመጣ ቀረ።
(3) የግስ በዓረፍተ ነገር መጨረሻ መምጣትና በመድረሻ ቅጥያዎች ቃላትን መመሥረት
(4) በብዙ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ውስጥ ያለው መጣ – - ና ና የሚለው ሕገ-ወጥ
ግንኙነት (suppletion) [ልክ እንደእንግሊዝኛው go – went]

ይህ አጭር የምርምር ወረቀት የሚያሳየው ኢትዮጵያ ልሳነ-ብዙ መሆኗን፣እያንዳንዱ ብሔረሰብ የራሱ ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ፣ ወዘተ. ያለው መሆኑን ነው። እንግዲህ ይህ ልዩነት ነው ለኢትዮጵያ ውበት የሚሰጠው። ሁሉም ነገር አንድ ዓይነት ቢሆን ግን የራሱ ጥቅም ቢኖረውም አሰልቺ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ እያንዳንዱ ቋንቋ የተለየ ቢሆንም ብዙዎቹን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚያስተሳስሩ የድምጽና ሰዋሰዋዊ ጠባያት መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም። ይህም የመነጨው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በረጅሙ ታሪካቸው እርስ በርስ የማያቋርጥ ግንኙነት እንደነበራቸው ነው። ግንኙነቱም ከተራ ግንኙነት ጀምሮ የጋብቻ፣ የታሪክ፣ የንግድ፣ የቋንቋ፣ የባህል… ወዘተ. ግንኙነት እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።

ዝግጅትና ጥንቅር፡- – ዶ/ር አንበሴ ተፈራ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር