የሻምበል አበበ ብቂላ ማራቶን በሐዋሳ ተካሄደ


የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የሻምበል አበበ ብቂላ ማራቶን ባለፈው እሑድ በሐዋሳ ከተማ ሲካሄድ በወንዶች የፌዴራል ፖሊስ ስንታየሁ ለገሰ፣ በሴቶች ደግሞ የመከላከያዋ አፀደ ባይሳ አሸናፊ ሆነዋል፡፡
በ1956 በሮም፣ እንዲሁም በ1960 ዓ.ም. በቶኪዮ በተዘጋጁት የኦሊምፒክ ውድድሮች በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ከአገሩ አልፎ አፍሪካን እንዳኮራ የሚነገርለት ሻምበል አበበ ብቂላ አሁንም ድረስ በስመ ገናናነቱ ይጠቀሳል፡፡ በተለይ ደግሞ በሮም አውራ ጎዳናዎች 42 ኪሎ ሜትር ከ195 ሜትር የሚሸፍነውን ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበበት ታሪኩ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ እየተዘጋጀ ዛሬ ላይ ለደረሰው ዘመናዊ ኦሊምፒክ ተምሳሌት እንደሆነም ይገኛል፡፡
‹‹ኢትዮጵያና አትሌቲክስ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ›› ሆነው እንዲቀጥሉ ፈር ቀዳጅ መሆኑ ለሚመገርለት ሕያው አትሌት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በስሙ የማራቶን ውድድር ማዘጋጀት ከጀመረ ሦስት አሠርታት አስቆጥሯል፡፡
በዚሁ መሠረት ባለፈው እሑድ ሰኔ 15 ቀን 2006 ዓ.ም. በሐዋሳ ባከናወነው ማራቶን በወንዶች ከፌዴራል ፖሊስ ስንታየሁ ለገሰ ርቀቱን 2 ሰዓት፣ 13 ደቂቃ፣ 28 ሰከንድ፣ በሆነ ጊዜ አጠናቆ አንደኛ ሲወጣ፣ ረጋሳ ምንዳዬ ከኦሮሚያ 2 ሰዓት፣ 13 ደቂቃ፣ 30 ሰከንድ ከፌዴራል ፖሊስ ገዛኸኝ አበራ 2 ሰዓት፣ 13 ደቂቃ፣ 32 ሰከንድ በመግባት ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነዋል፡፡
በሴቶች ከመከላከያ አፀደ ባይሳ 2 ሰዓት፣ 45 ደቂቃ፣ 60 ሰከንድ፣ እንዲሁም ከዚሁ ክለብ እመቤት ኢተአ 2 ሰዓት፣ 47 ደቂቃ፣ 25 ሰከንድ ስትወጣ፣ በግል የቀረበችው ሻሾ     2 ሰዓት፣ 47 ደቂቃ፣ 26 ሰከንድ ሦስተኛ በመሆን አጠናቃለች፡፡ በቡድን ወንዶች ፌዴራል ፖሊስ፣ በሴቶች ደግሞ መከላከያ አሸናፊ ሆነው የዋንጫ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር