የጉምሩክ አዋጅ ሊሻሻል ነው
- ክስ የማይመሠረትባቸው የጉምሩክ ጥፋቶች ተዘርዝረዋል - የምርት ሒደታቸውን ባላጠናቀቁ ምርቶች ላይ የቀረጥ ነፃ አሠራር ይፈቅዳል - ዋና ዳይሬክተሩ ክስ አለመመሥረት የሚችልባቸው አሠራሮች ተቀምጠዋል
በ2001 ዓ.ም. ፀድቆ ሥራ ላይ የዋለውን የጉምሩክ አዋጅ የሚያሻሽልና የአገሪቱን የማኑፋክቸሪንግ ዘመቻ የመደገፍ ግብ የያዘ የጉምሩክ ማሻሻያ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡ አዋጁ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ የምርት ሒደታቸውን ያላጠናቀቁ ምርቶች ከቀረጥ ነፃ ገብተው በጉምሩክ ቁጥጥር ሥር የምርት ሒደታቸውን እንዲያጠናቅቁ ይፈቅዳል፡፡
በአገሪቱ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት የሚጠይቀው የጉምሩክ አሠራርን ማካተት አስፈላጊ መሆኑን መንግሥት ስላመነበት ማሻሻያ ረቂቁ መዘጋጀቱን፣ ባለፈው ሐሙስ ለፓርላማ የቀረበው የአዋጁ ማብራርያ ይገልጻል፡፡
አዋጁን ለማሻሻል ምክንያት ከሆኑት መካከል የወጪና ገቢ ንግድ ዕድገት፣ በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት የሚጠይቃቸውን ቀልጣፋ የጉምሩክ አገልግሎት ለመስጠትና የተመጣጠነ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችሉ አሠራሮችን ሥራ ላይ ለማዋል፣ ዘመናዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ የጉምሩክ አሠራሮችን ለማስፈጸም የሚያስችል ሕግ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑ ይገኙበታል፡፡
አዋጁ ካካተታቸው ዋና ዋና ለውጦች መካከል የምርት ሒደታቸውን ሳያጠናቅቁ ወደ አገር የሚገቡ ዕቃዎች ያለቀረጥ የሚስተናገዱበትና በጉምሩክ ቁጥጥር ሥር የሚጠናቀቁበት አሠራር አንዱ ነው፡፡
ይህ አሠራር ከውጭ አገር የመጡ ዕቃዎች ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከመለቀቃቸው በፊት አገር ውስጥ የምርት ሒደታቸውን የሚያጠናቅቁበትና ለአገር ውስጥ ፍጆታ ሲለቀቁ ቀረጥና ታክስ እንዲከፈልባቸው የሚደረግበት አሠራር መሆኑን የአዋጁ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ አሠራሩ የቀረጥና ታክስ ክፍያን የማዘግየት ውጤት ያለው መሆኑንና ይህም ባለሀብቶች የመሥሪያ ካፒታላቸውን እንዳይያዝ የሚረዳና ኢንቨስትመንትን የሚስብ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
በጉምሩክ ቁጥጥር ሥር ምርታቸው እንዲጠናቀቅ የሚደረጉ ዕቃዎች በዚህ ሥነ ሥርዓት መሠረት የሚስተናገዱበት የምርት ሒደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ዕቃዎቹን ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ መልሶ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግ የማይችል መሆኑ ሲረጋገጥ ነው፡፡
በዚህ ሥርዓት መስተናገድ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ፈቃድ ይሰጣል፡፡ መሟላት የሚገባቸው መሥፈርቶች በዝርዝር በመመርያ እንደሚወሰኑ ረቂቁ ያስረዳል፡፡
በተመሳሳይም ዕቃዎች የጥገና ሒደታቸውን በአገር ውስጥ እንዲያጠናቅቁ በጊዜያዊነት መግባት እንደሚችሉና በዚህ ሁኔታ የገቡ ዕቃዎች ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ መውጣት እንዳለባቸው ረቂቁ ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም ዕቃዎች የምርትና የጥገና ሒደታቸውን በውጭ አገር እንዲያጠናቅቁ ሊፈቀድ እንደሚችል፣ ሆኖም የዚህ ሒደት ውጤት የሆኑ የማካካሻ ምርቶች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ አገር ውስጥ መመለስ እንዳለባቸው ረቂቁ ይገልጻል፡፡
ይህንን ማድረግ የተፈለገበት ምክንያት አምራች ኢንዱስትሪዎች የአንድን ምርት ሒደት በከፊል ከውጭ አገር በትዕዛዝ ተቀብለው እንዲሠሩና ዕቃዎቹ በምርት ሒደት ካለፉ በኋላ ተመልሰው የሚወጡበት ሁኔታን ለመፍጠር ነው በማለት ማብራርያው ያስረዳል፡፡ በተመሳሳይም በአገር ውስጥ ሊከናወን የማይችል የማምረት ሒደት በውጭ አገር ተከናውኖ ዕቃዎቹ ተመልሰው ወደ አገር እንዲገቡ ለመፍቀድ መሆኑን ይገልጻል፡፡
‹‹በዚህ አዋጅ መሠረት በጊዜያዊነት ወደ ውጭ የተላኩ ዕቃዎች የምርት ወይም የጥገና ሒደት ውጤት የሆኑ የማካካሻ ምርቶች ዕቃዎቹ በጊዜያዊነት በተላኩ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ አገር ውስጥ ተመልሰው መግባት አለባቸው፣ ሆኖም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ባለሥልጣኑ የጊዜ ገደቡ እንዲራዘም ሊፈቅድ ይችላል፤›› ይላል ረቂቅ አዋጁ፡፡
የጉምሩክ ጥፋቶችና ቅጣቶችን በተመለከተ በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 156 እስከ 176 የተቀመጡት ድንጋጌዎች የጉምሩክ ጥፋቶችን በሁለት ዓይነት ማለትም አስተዳደራዊ ቅጣትና የወንጀል ቅጣት በማለት ይዘረዝራቸዋል፡፡
በዚህም መሠረት በዴክላራሲዮን ላይ ከተመዘገበው ውጪ የቀረጥና የታክስ ልዩነት የሚያስከትል ወይም አነስተኛ ታክስ እንዲከፈል የሚያደርግ ድርጊት የፈጸመ ሰው አስተዳደራዊ ቅጣት ብቻ ይቀጣል፡፡
ይህም ማለት የተፈጸመው ጥፋት ከተከፈለው ቀረጥና ታክስ ጋር ሲነፃፀር በብልጫ የሚፈለገው ከአሥር በመቶ የማይበልጥ ከሆነ ያለ ቅጣት ታክሱን ብቻ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ ከተከፈለው በብልጫ የሚፈለገው ከአሥር በመቶ እስከ 50 በመቶ ከሆነ በዕቃው ላይ ሊከፈል የሚገባውን ቀረጥና ታክስ መክፈሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዚሁ ቀረጥና ታክስ 200 ፐርሰንት እጥፍ የሆነ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፡፡ የተገኘው ቀረጥና ታክስ ልዩነት ከ50 በመቶ በላይ ከሆነ ግን ድርጊቱ እንደ ኮንትሮባንድ ወንጀል ተቆጥሮ ክስ የሚመሠረት መሆኑን ረቂቁ ይገልጻል፡፡
የማጓጓዣ ባለቤቶች ጥፋት ሳይፈጽሙ በማጓጓዣቸው ወንጀል በመፈጸሙ ብቻ ከአሥር ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ብር ቅጣት የሚጥል የነበረው ድንጋጌ መሰረዙንም ረቂቁ ይገልጻል፡፡
ይህንን አስተዳደራዊ ቅጣት መደንገግ ያስፈለገው በጥቃቅን ጥፋቶች ምክንያት ይከሰት የነበረውን እንግልት ለማስቀረት እንደሆነ ማብራርያው ያስረዳል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር የሚከተሉት ምክንያቶች ሲኖሩት፣ የወንጀል ክስ እንዳይመሠረት ሊያደርግ እንደሚችል ይገልጻል፡፡
ምክንያቶቹም ወንጀሉን ፈጽሟል የተባለው ሰው በዕድሜ መጃጀት ወይም በበሽታ ምክንያት ጉዳዩን በፍርድ ቤት መከታተል የማይችል ከሆነ፣ ወንጀሉ በክስ ሒደት ውስጥ ቢያልፍ ብሔራዊ ጥቅምን ወይም ዓለም አቀፍ ግንኙነትን ይጐዳል ተብሎ ከታመነበት፣ ወንጀሉ ሥልጣን ላለው ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በመቆየቱ አስፈላጊነቱን ያጣ ከሆነ በማለት ያስቀምጣል፡፡
ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም በማለት ከሚዘረዝራቸው ወንጀሎች መካከል ማንኛውም የጉምሩክ ሹም ወይም የፌዴራል ፖሊስ አባል የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ አገልግሎቶችን ያጓተተ፣ የተሰጠውን ሹመት ወይም ሥልጣን በግልጽ ተግባር ወይም በግድፈት ያላግባብ የተገለገለ እንደሆነ፣ ከሦስት ዓመት በማያንስና ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል ይላል፡፡
ረቂቁ ለውይይት በቀረበበት ወቅት የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ በተለይ የውጭ ጉዳዮችና የመከላከያ ደኅንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ክስ እንዳይመሠረት ስለሚሰጥ ውሳኔ በሚል ለዋና ዳይሬክተሩ የተሰጡ መብቶች ከሕግ ጋር ያላቸውን ቅራኔ በማንሳት በድጋሚ ሊታዩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ክስ እንዳይመሠረት ከሚያደርግባቸው ምክንያቶች መካከል በዕድሜ መጃጀት ወይም በበሽታ ምክንያት ተብሎ የተቀመጠው ለትርጉም ክፍት መሆኑን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ በወንጀል ሕጉ መጃጀት ክስ እንዳይመሠረትባቸው ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ቢጠቀስም ዋና ዓላማው በመጃጀት ምክንያት በሕግ የሚጣል ኃላፊነትን መወጣት አይቻልም ከሚል እምነት እንደሆነ ይህንንም የሚወስነው ፍርድ ቤት መሆኑን በመግለጽ ይህንን የፍርድ ቤት ሥልጣን ለዋና ዳይሬክተሩ መስጠት በድጋሚ መታየት አለበት ብለዋል፡፡
‹‹መጃጀት ማለት ምን ማለት ነው? ስንት ዓመት ነው?›› ብለው የጠየቁት አቶ ተስፋዬ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነትን ይጐዳል ብለው ዳይሬክተሩ ካመኑ ክስ እንዳይመሠርቱ መፍቀድም ለትርጉም ክፍት በመሆኑ ከዚህ ይልቅ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ቢባል ይሻላል ብለዋል፡፡
ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀምን በተመለከተ የተቀመጡት ወንጀሉን የሚያቋቁሙ ፍሬ ነገሮች ከሙስና ወንጀል ጋር ወይም በፀረ ሙስና ሕግ ውስጥ ወንጀል ናቸው ተብለው የተቀመጡ በመሆናቸው መጣረስ ይታይባቸዋል ብለዋል፡፡
‹‹ቅጣቱ እስከ ሞት ድረስ ሊደርስ ይችላል ብለን በፀረ ሙስና አዋጁ አስቀምጠን፣ ይህንን ተመሳሳይ ወንጀል በሚፈጽሙ የጉምሩክ ሹሞች ላይ ቅጣቱን እስከ አሥር ዓመት ፅኑ እስራት መገደብ ተገቢ ባለመሆኑ በደንብ መታየት አለበት፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
‹‹ይህንን አዋጅ ብናፀድቅና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም በሚል የጉምሩክ ሹመኞች ላይ ክስ ቢመሠርት ተከሳሹ በጉምሩክ አዋጅ ነው መዳኘት ያለብኝ ብሎ ቢከራከር፣ ዳኛው ተከሳሹን የበለጠ የሚጠቅመውን ሕግ እንዲጠቅስ የወንጀል ሕጉ ስለሚያስገድደው በዚሁ ሕግ ሊዳኝ ይችላል፡፡ ይህም ከፀረ ሙስና ትግሉ አንፃር ይጋጫል፡፡ ስለዚህ ያለው መጣረስ ቢታይ ጥሩ ይመስለኛል፤›› ብለዋል፡፡ አዋጁ ለተጨማሪ ዕይታ ለሁለት ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርቷል፡፡
Comments
Post a Comment