አዲስ አበባን እና ሃዋሳን ጨምሮ በ24 ከተሞች የመሬት ይዞታ ምዝገባ ሊጀመር ነው


አዲስ አበባ ፣ የካቲት 18 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በአዲስ አበባና በ23 ከተሞች የመሬት ይዞታ ምዝገባን ለማከናወን የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች መጠናቀቃቸውን የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የፌዴራል የከተማ መሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ ኤጀንሲ ተጠባባቂ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ከበደ እንዳሉት፥ የመሬት ይዞታ ምዝገባው ከተሞች ያሏቸውን ለልማት ዝግጁ የሆኑ መሬቶች እንዲያውቁ ከማስቻሉም በላይ የይዞታ ይገባኛል ክርክርን ያስቀራል።
ለኢንቨስትመንት አጋር የሆኑት ባንኮችም ከስጋት ነጻ የሆነ የብድር አገልግሎት እንዲቀርቡ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።
ምዝገባውን በከተሞቹ ለመጀመር አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ማለትም የከተሞች ካርታ ስራና የሲስተም ልማት ስራዎች ተጠናቀዋል ብለዋል።
የመሬት ይዞታ ምዝገባው በተመረጡ 69 ከተሞችም በቀጣይ እንደሚከናወንም ገልፀዋል።
በአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልልች ስርአቱን የሚያግዙ ማዕከላት ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን፥  የይዞታ መሬት ምዝገባው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚከናወን ይሆናል ሲሉ አክለዋል።
ምዝገባው በህግ ወጥ መልኩ ተይዘው የነበሩ ይዞታዎችን ወደ መሬት ባንክ እንዲመለሱ የሚያደርግ ሲሆን፥ ሀገሪቱ ለልማት የምታውለው ተጨማሪ መሬትም እንድታገኝ ያስችላታል ነው የተባለው።
አሰራሩ የሀገሪቱን የመሬት ሀብት ከአንድ ማዕከል ማወቅ የሚቻልበት አሰራር ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

Comments

Popular posts from this blog

የሲዳማ ክልል ባለስልጣናትን ጨምሮ የተገለገሉት የሰሞኑ የቻርተር አውሮፕላን በረራዎች!

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ብሔር በሰፊው የሚታወቀው የ"አፊኒ" ባህላዊ የዳኝነት ስርዓትና የአዋጅ ረቂቅ ተሞክሮ በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ቀረበ