የቀድሞው የፌዴራል ቤቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ተፈሪ ፍቅሬ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 19 ፣ 2006 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞው የፌዴራል ቤቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ተፈሪ ፍቅሬ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
ተከሳሹ የፌዴራል ቤቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ከ2002 እስከ 2005 ዓመተ ምህረት ያገለገሉት  አቶ ተፈሪ ፍቅሬ የፌደራል የስነ ምግባርና  ፀረ ሙስና  አቃቢ ህግ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት ክስ መስርቶባቸዋል ።
በግለሰቡ ላይ የተከፈተው  የክስ መዝገብ ተከሳሹ የተሰጣቸውን የመንግስት ሃላፊነት ያለአግባብ ተጠቅመው የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና ለሌሎች ለማስገኘት በማሰብ ፤
በቀድሞው ወረዳ 23 ቀበሌ 12 በውጭ ምንዛሬ ተከራይቶ የነበረውን የቤት ቁጥር 106 የመንግስት ቤት ለኢትዮጵያውያን እንዲከራይ ግምት እንዲሰራ በታዘዘው መሰረት በባለሙያዎች 1 ሺህ 998 ብር ተመን ከወጣለት በኋላ ፤
የኤጀንሲውን የተለመደ አሰራር በመጣስና የባለሙያዎችን የኪራይ ግምት ውድቅ በማድረግ ለአንዲት ግለሰብ ተመኑን ቀንሰው አከራይተዋል።
በዚህም ከ2002 እስከ 2005 ዓመተ ምህረት መንግስት ከቤቱ ማግኘት የነበረበትን 17 ሺህ 420 ብር በማሳጣትና በመንግስት ላይ ጉዳት አድርሰው ተከራይን ያለአግባብ ተጠቃሚ አድርገዋል ይላል ።
በቀድሞው ወረዳ 21 ቀበሌ 01 የቤት ቁጥር 112/40 የሆነውን የመንግስት መኖሪያ ቤት ባሰፋ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት፥ ለመኖሪያነት አገልግሎት በጨረታ አሸንፎ 7 ሺህ 650 ብር እየከፈለ ይኖርበት የነበረውን ቤት፤
ተከሳሹ ከተከራይ ድርጅቱ ጋር በመመሳጠር ቤቱ ለመኖሪያ ቤትነት እንደተሰጠ እየታወቀ ለስራ አልተመቸኝም በማለት እንዲያመለክቱ አድርገው ፤ የኤጀንሲውን መመሪያ ወደጎን በመተው በዚሁ ቀበሌ የሚገኘውን የቤት ቁጥር 394/23 የሆነን የድርጅት ቤት በመኖሪያነት ተቀይሮ እንዲሰጣቸውና የቤቱን የኪራይ ዋጋ መጠንም ከብር 5 ሺህ 126 ወደ 1 ሺህ 93 ብር በማውረድ እንዲከራዩት ስልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ወስነዋል ይላል  የክስ መዝገቡ ።
በዚሁ በወረዳ 21 ቀበሌ 01 የቤት ቁጥር 112/40 የሆነውን የመንግስት ቤት ከ2003 እስከ 2005 ዓመተ ምህረት ድረስ ፥ በየወሩ ከቤቱ የኪራይ ተመን 7 ሺህ ብር በመቀነስ መንግስት ከቤቱ ማግኘት የነበረበትን 244 ሺህ ብር እንዲያጣ ማድረጋቸው ተጠቅሷል ።
በወረዳ 23 ቀበሌ 23 የቤት ቁጥር 394/ 23 ከሆነው ቤት ላይ ደግሞ በወር 4 ሺህ 33 ብር በመቀነስ ከ2003 እስከ 2005 ዓመተ ምህረት ፥ 129 ሺህ 56 ብር በመቀነስ በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስና ተከራይን ያለአግባበብ ተጠቃሚ ማድረጋቸው በክሱ ተጠቅሷል።
ቀድሞ ወረዳ 18 ቀበሌ 06 የቤት ቁጥር 008/14 ተከራይ የነበሩ ግለሰብ ከሚሰሩበት ተቋም ወይም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት የተፃፈላቸው የድጋፍ ደብዳቤ ሳይኖር ከተከሳሹ ጋር ባላቸው የግል ቀረቤታ፥ ለግለሰቡ ቀድሞ 7 ሺህ 600 ብር ተከራይቶ የነበረውን የቤት ቁጥር 112 /40 ፥ በ650 ብር እንዲከራዩት በማድረግ ቅያሬ ቤት በመስጠት ግለሰቡ ያለአግባብ እንዲጠቀሙ አድርገዋልም ሲል  ይዘረዝራል 
 ኤጀንሲው ከሚያስተዳድራቸው የመንግስት ቤቶች ውስጥ ለተወሰኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅት ሰራተኞችና ሃላፊዎች ተመድበው የነበሩ 28 የመንግስት ቤቶችን ፥ በመኖሪያ ቤቶች አዋጅ መሰረት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ማፅደቅ እየተገባው ፤ ተከሳሽ ራሳቸው በ2004 ዓመተ ምህረት ያወጡት መመሪያ ይፈቅድልኛል በሚል ከስልጣናቸው በላይ በመስራትና በመወሰን ፤
እንዲሁም ለመንግስት መስሪያ ቤቶች ማበረታቻ ተመድበው የነበሩትን የመንግስት ቤቶች ከታሰበለት ዓላማ በመውጣት፥ በግለሰቦች ስም በማዞር እና በማከራየት አሰራርን እየጣሱ ግለሰቦችን ያለአግባብ ተጠቃሚ አድርገዋል ይላል የስነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ በክሱ።
በአጠቃላይ ተከሳሹ ህግ እና አሰራርን በመጣስና በዜጎች መካከል ልዩነት በመፍጠርና የመንግስትን መብትና ጥቅም በሚጎዳ መንገድ በመስራት፤ በጥቅሉ ከ33 ቤቶች መንግስት ማግኘት የነበረበትን 370 ሺህ 446 ብር ተቀንሶ እንዲከራይ የማድረግ ስልጣን ሳይኖራቸው ከአሰራር ውጪ እየወሰኑ በመንግስት ላይ ጉዳይ ያደረሱና ግለሰቦችን ያለአግባብ ተጠቃሚ በማድረጋቸው ተከሰዋል።
ችሎቱ ክሱን ከተመለከተ በኋላ ግለሰቡ የዋስትና መብታቸው ተነስቶ በማረሚያ ቤት ሆነው የክስ ሂደታቸውን እንዲከታሉ ተዕዛዝ በመስጠት ፥ የክስ መግለጫውን ለማድመጥም ለህዳር 3 ቀን 2006 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር