የሰሞኑ ዝናብ ያልተለመደ ነው

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 28 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሄራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ በአሁኑ ወቅት በመስከረም ወር እየጣለ ያለው ዝናብ ያልተለመደ መሆኑን ገለጸ ።
በኤጀንሲው የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ድሪባ ቆሪቻ እንደገለጹት ፥
ከባለፈው መስከረም 20 ጀምሮ አብዛኛውን የሃገሪቱን ክፍል የሸፈነ የዝናብ ስርጭት ተስተውሏል።
ዳይሬክተሩ በተለይም በአማራ ፣ ኦሮሚያ ፣ ደቡብና ሃረሪ ክልሎች እንዲሁም በሶማሌ ክልል ሰሜናዊ አጋማሽ ድሬዳዋን ጨምሮ ይህ ያልተለመደ ዝናብ ያለማቋረጥ መዝነቡን እና በተለይም የአማራ መካከለኛው ምስራቅ ፣ ደቡብ ኦሮሚያ እና የደቡብ ክልል ሰሜናዊ አጋማሽ ከበድ ያለ ዝናብን  ያስተናገዱ አካባቢዎች እንደነበሩ ገልጸዋል ።
ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ ግን ይህ የዝናብ ስርጭት በሃገሪቱ ሰሜናዊ ክፍለ የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱን ነው አቶ ድሪባ የተናገሩት ።
በተመሳሳይ በቀጣዮቹ አራት ቀናት ውስጥ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑትና በዚህ ወቅት ሰብል መሰብሰብ በሚጀምሩት  የሃገሪቱ ሰሜን ፣ ሰሜን ምስራቅና የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የዝናብ ስርጭቱ እንደሚቀንስ አቶ ድሪባ አስረድተዋል ።
የሜትዮሮሎጂ ትንበያ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሃገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ የዝናብ ስርጭቱ በመጠንም ሆነ በሽፋን እየተስፋፋ እንደሚሄድ ይጠበቃል ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የወቅቱ ዝናብ ዘግይተው ለተዘሩ ሰብሎች ጥቅም ሊኖረው እንደሚችል ነው ሀላፊው የገለጹት።
በቀጣይ ግን እንደባለፈው ሳምንት የተስፋፋ ዝናብ እንደማይጠበቅ ፥ ይሁንና በአንዳንድ ስፍራዎች ያልተጠበቀ ዝናብ ሊከሰት ስለሚችል የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ረገድ አርሶ አደሩ ጥንቃቄ እንዲወስድ አሳስበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ በየጊዜው የአየር ሁኔታውን እየተከታተለ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን እንደሚሰጥ ሃላፊው ተናግረዋል ።
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ዳኛቸው በየነ በበኩላቸው ፥ እየጣለ ያለው ዝናብ የሚፈጠረው እርጥበት በተለይ ሽምብራና ምስር የመሳሰሉትን እህሎች ቶሎ ለመሰብሰብ ከማገዝ ባለፈ በቂ የእንስሳት መኖ እንዲኖርም የሚያደርግ ነው ብለዋል።   ።
ዶክተር ዳኛቸው አሁን በተለያዩ አካባቢዎች እየተሰተዋለ ያለው ዝናብ በጥቂት ቀናት ውስጥ ስርጭቱ ስለሚቀንስ ብዙ የሚያሰጋ ነገር እንደማይኖር  እና ጥቅምት እና ህዳር ወር መጨረሻ ላይ ሊኖር ይችላል የተባለውን ዝናብም ፥  ለቀጣይ የመስኖ ስራዎቻችን የሚያግዝ ሊሆን ስለሚችል እንጠቀምበታለን ሲሉም ነው የተናገሩት ።
ሃላፈው በደረሱት እህሎች ላይ የሚደረገው ጥንቃቄ እንዳለ ሆኖ ከብሄራዊ ሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ ጋር በጋራ በመስራት ቀጣይ ክትትሎችን እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር