ለኢኮኖሚያዊ ሙስና የሚሰጠው ትኩረት ለፖለቲካዊ ሙስናም ይሰጥ!!

በተፈለገው ፍጥነት፣ መጠን፣ ስፋትና ክብደት ባይሆንም ለሙስና ትኩረት እየተሰጠና ትግል እየተካሄደ ነው፡፡ ዕርምጃም እየታየ ነው፡፡
ውሳኔው ለፍርድ ቤት የሚተው ቢሆንም፣ መንግሥት ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩ በርታ ተበራታ የሚያስብል ነው፡፡
በግልጽ ልናነሳቸው የሚገቡ በሙስና ትግል ዙሪያ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለጊዜው አንድ ዓብይ ጉዳይ እናንሳ፡፡ 
ሙስና ከገንዘብ ጋር ብቻ የተያያዘ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ጉቦ መቀበል፣ ገንዘብ መስረቅ፣ ያላግባብ የጨረታና የግዥ ጥቅማ ጥቅም ማግኘት፣ ወዘተ ተግባራት እየተፈጸሙ ናቸው፡፡ በዚህም የመንግሥት አካላትና ከመንግሥት ውጭ ያሉ የግሉ ዘርፍ አካላትም ተጠያቂ እየሆኑ ናቸው፡፡ 
ቁም ነገሩ ተጠቃሎ ሲታይ የሕዝብና የመንግሥት ገንዘብ አላግባብ ተመዘበረ፣ ተሰረቀ፣ ተሰጠ፣ ተወሰደ፣ ተመነተፈ፣ ተዛወረ፣ ወዘተ ነው፡፡ ገንዘብ ወይም ንብረት ያለበት ወንጀል ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊና ቢዝነስ ነክ ሙስና ነው፡፡ 
ይህ አደገኛ የሙስና ዘርፍ ስለሆነ ልንዋጋውና ልንታገለው ይገባል፡፡ የአገር ልማትን፣ የኢንቨስትመንት ሒደትንና ከድህነት ለመላቀቅ የሚደረገውን ጥረት የሚያሰናክል ነውና፡፡ 
ሙስና ግን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ፖለቲካዊ ሙስናም አለ፡፡ 
የተሰጣቸውን ሕዝባዊ ኃላፊነት ተጠቅመው አገርንና ሕዝብን ከማገልገልና ለሕገ መንግሥትና ለሕግ ተገዥ ሆኖ ከመሥራት ይልቅ የኃላፊነት ወንበሩን፣ ሕገ መንግሥቱን፣ ሕጉን፣ መመርያውንና ደንቡን እየጣሱ የሚፈልጉትን ለመጥቀምና የማይፈልጉትን ለማጥቃት መንቀሳቀስም አለ፡፡ 
ይህ ድርጊት የገንዘብና የንብረት ጥቅም ላይኖርበት ይችላል፡፡ ነገር ግን ፖለቲካዊ ሥልጣንን ተጠቅሞ ያላግባብ መጥቀምና ያላግባብ ዜጋን መጉዳት ይታይበታል፡፡ 
እከሌና እከሊት ጠላቶቼ ስለሆኑ መሬት እንዳያገኙ ከልክሏቸው፣ ፈቃድ እንዳይሰጣቸው፣ የያዙትንም ቀሙዋቸው፣ የባንክ ብድር እንዳያገኙ፣ የብቃት ማረጋገጫ እንዳትሰጧቸው፣ የሥራ ፈቃዳቸው እንዳይታደስ፣ ወዘተ እየተባለ መጉዳት፣ ማንከራተትና ሕገወጥ ተግባር መፈጸም እየተለመደ ነው፡፡ 
ለማጥቃት የተፈለገውን ድርጅት ወይም ግለሰብ ሕግና ሥርዓቱን በመጣስ ባልሆነ ወንጀል መክሰስ፣ ፋይል ማስከፈትና ማስፈረድ ይታያል፡፡ በተፃራሪው ደግሞ ወዳጅ ለሆነና ከራስ ፍላጎት ጋር የሚስማማ ሥራ ላለው ደግሞ ሕግ ቢጣስም እንዳይጠየቅ፣ እንዳይያዝ፣ እንዳይከሰስ፣ ከተከሰሰም ፋይሉ እንዲዘጋና ክሱ እንዲሰረዝ ይደረጋል፡፡ ይህ ሁሉ የማይቻል ከሆነም ሳይያዝ ወደ ውጭ አገር እንዲሸሽ ማድረግም አለ፡፡
እንዲህ የሚያደርግ ሙሰኛ ሹም የገንዘብ ጥቅም ላያገኝ ይችላል፡፡  ቤትም ላይኖረው ይችላል፡፡ ንብረትም ላያገኝ ይችላል፡፡ ከገንዘብና ጥቅማ ጥቅም አንፃር ተጠቃሚነት የሌለው ይመስላል፡፡ ነገር ግን ከፖለቲካ ሥልጣን አጠቃቀም አንፃር ሲታይ ግን ሥልጣንን መከታ በማድረግ የሚፈጸም አደገኛ የፖለቲካ ሙሰኛ ሊሆን ይችላል፡፡ 
መንግሥት በሙስና ላይ እዘምታለሁ ሲል ሁሉንም የሙስና ገጽታና ይዘት ለማጥፋት መረባረብ አለበት፡፡ 
ስንት ቪላ አለው? ስንት መኪና አለው? ስንት ብርና ዶላር አለው? ብሎ አንድን ተጠርጣሪ መመርመር አንዱ ገጽታ ነው፡፡ የስንት ሰው መብት ጣሰ? ስንት ዜጋ ጎዳ? የትኛውን ሕግ ጣሰ? ሕገ መንግሥቱን እንዴት ረገጠ? የማንን መብት አፈነ? ከየትኛው ሕገወጥ ጋር ቆመ? ጠበቃ ሆነ? ብሎ መመርመርም ያስፈልጋል፡፡ 
ሙስናን በማንኛውም መልኩ እንዋጋው፣ እንታገለው፡፡ ሙስና መልከ ብዙና ፈርጀ ብዙ ነውና፡፡ ራሱን የቻለ ጥናትና ምርምር ያስፈልገዋል፡፡ የሕዝብና የአገር ገንዘብና ንብረት የሚዘርፉ ሙሰኞች እንዳሉ ሁሉ፣ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት፣ ሕግና ሥርዓት ለግል ክብርና ዝና የሚጠቀሙበትና የሚጥሱት አሉ፡፡ እነዚህም አደገኛ ሙሰኞች ናቸው፡፡
ለኢኮኖሚና ለቢዝነስ ሙስና ትኩረት የሚሰጠውን ያህል ለፖለቲካ ሙስናም ትኩረት ይሰጥ፡፡ ሁላችንም!! አሁኑኑ!!
16 OCTOBER 2013 ተጻፈ በ  

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር