ሁላችንም ጉድለታችንን አውቀን ብናስተካክል ኖሮ ኢትዮጵያችን የትና የት በደረሰች ነበር?

ጉድለት መኖሩና ስህተት መፈጸም ምንጊዜም የትም ያለ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ጉድለት ለምን ታየ? ስህተት ለምን ተፈጸመ? የሚለው አይደለም፡፡
ችግራችንንና ጉድለታችንን ዓይተንና መርምረን እናስተካክላለን ወይ? የሚለው ነው ዋናው ጉዳይ፣ ዋናው ቁም ነገር፡፡ 
መንግሥትም እንደ መንግሥት ጉድለት አለበት ስህተት ይፈጽማል፡፡ ገዥው ፓርቲም እንደ ገዥ ፓርቲ ስህተት ይፈጽማል ጉድለት አለበት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ጉድለት አለባቸው ስህተት ይፈጽማሉ፡፡ የግል ዘርፉ ጉድለት አለበት ስህተት ይፈጽማል፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡም ጉድለት አለበት ስህተት ይፈጽማል፡፡ መገናኛ ብዙኃንም ስህተት ይፈጽማሉ ጉድለት አለባቸው፡፡
ግን! ነገር ግን! እነዚህ አካላት የራሳቸውን ስህተትና ጉድለት ያውቃሉ? ያያሉ? ወይስ በሌላው ስህተትና ጉድለት ላይ ብቻ ነው የሚያተኩሩት? የራሳቸውን ስህተት መረዳትና ማወቅ ብቻ ነው ወይስ ለማስተካከል ይጥራሉ? ይታገላሉ? 
የእኛ ፅኑ ዕምነት ሁላችንም ስህተታችንንና ጉድለታችንን ዓይተን፣ አውቀንና አምነን ብናስተካክል አገራችን የትና የት ትደርስ ነበር የሚል ነው፡፡ 
መንግሥት ከቃላት ባሻገር ከልብ በተግባር በመልካም አስተዳደር ላይ በተጨባጭ የሚታየው ጉድለትና ስህተት ምንድነው? ዲሞክራሲን እውን ለማድረግ፣ ሰብዓዊ መብት ለማክበር፣ ፍትሕ ለማንገስ፣ የፕሬስ ነፃነትን ዳር ለማድረስና ሙስናን ለማስወገድ ተጨባጭ ድክመቴ ምንድነው? ብሎ ለማወቅ ቢረባረብና ለማረም ቢታገል ትልቁ የአገር ችግር ይፈታል፡፡ አመቺ የሥርዓት ግንባታ ይዘረጋል፡፡ በሁሉም መስክ ታሪካዊ ለውጥ እውን ለማድረግ ጉዞው ቀላልና ብርሃን ይሆናል፡፡ 
ተቃዋሚዎች ራሳቸው የትም ይኑሩ የት በመንግሥት በኩል ያለውን ጉድለት ብቻ ለማየት ከመረባረብ ባሻገር ምን ዓይነት ጉድለትና ስህተት አለብን? ብለው ቢፈትሹ መልካም ነው፡፡ እኛ ተቃዋሚዎች የፖለቲካ ፕሮግራም አለን ወይ? የተሻለ ፖሊሲ ይዘናል? ማስፈጸሚያ ስትራቴጂ አለን ወይ? ውስጣዊ ዲሞክራሲ አለን ወይ? እየተደረጀን ነው ወይ? ከሙስና የፀዳን ነን ወይ? ለሥልጣን ብለን የጠላት መሣሪያ እየሆንን ነን ወይ? ስህተትን ስናወግዝ አዎንታዊ ነገሮችን አንቀበልም? አናምንም? ወዘተ እያሉ ቢፈትሹና ቢመረምሩ የት በደረሱ? ስህተቶቻቸውን  በተግባር ቢያስተካክሉ ኢትዮጵያ እውነትም ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይኖሯት ነበር፡፡ ሕዝብም ያከብራቸው ነበር፡፡ በምርጫም የላቀ ተወዳዳሪ በሆኑ ነበር፡፡ 
የግል ዘርፉ አባላትም የመንግሥትና የሌላውን ጉድለትና ስህተት ከማየት ባሻገር በራሳችንስ ምን ዓይነት ጉድለትና ስህተት አለ ብለው ቢፈትሹ የተሻለ ነው፡፡ በሕጋዊ ፈቃድ እየሠራን ነው ወይ? ግብር በወቅቱና በሕጉ መሠረት እንከፍላለን ወይ? ከሙስና የፀዳን ነን ወይ? ለአገር እንቆረቆራለን ወይ? ከሕገወጥ ተግባር የራቅን ነን ወይ? ለልማት የቆምን ነን ወይ? ብለው ቢፈትሹና በዚህ ዙሪያ ያለውን ድክመትና ስህተት ለይተውና አርመው ቢጓዙ፣ የአገራችን የግል ዘርፍ ድርሻ እጥፍ ድርብ በሆነ ነበር፡፡
ሲቪል ማኅበረሰቡም ስህተቶችን በመንቀስና በደል ተፈጸመብን ከሚለው ባሻገር በላቀ ደረጃ ውስጣቸውን እየፈተሹ ሕግ እናስከብራለን ወይ? ለሕዝብ እየሠራ ነን ወይ? ከሙስና የፀዳን ነን ወይ? እያሉ ጉድለታቸውንና ስህተታቸውን አርመው ቢጓዙ እጥፍ ድርብ አስተዋፅኦ ባደረጉ ነበር፡፡ 
መገናኛ ብዙኃንም ተበድለናል፣ ተረግጠናል ከማለት ባሻገር እኛ ራሳችን ሕግ እያከበርን ነን ወይ? እኛ ራሳችን የሙያ ብቃትና የሥነ ምግባር አቅም አለን ወይ? እኛ ለሕዝቡ በትክክል እውነቱን እየነገርነው ነን ወይ? እኛ ራሳችን ከአሽከርነት፣ ከሙስና፣ ከተላላኪነትና ከመሣሪያነት ተላቀን በቅድሚያ ሕዝብን ለማገልገል ተነስተናል ወይ? ለሕገ መንግሥቱ ቆመናል ወይ? ብለው ቢፈትሹና ስህተታቸውን በማረም ተደራጅተውና ተጠናክረው ቢሠሩ ሕዝቡ እጥፍ ድርብ በተጠቀመ ነበር፡፡ ሕዝብ ትክክለኛ መረጃ እያገኘ በአገሩ ጉዳይ የላቀ ድርሻ በኖረው ነበር፡፡
የፍትሕ አካላት ለሕገ መንግሥት የቆምን ነን ወይ? ሕዝብን እያገለገልን ነን ወይ? ከሙስና የፀዳን ነን ወይ? ብለው ፈትሸው ችግራቸውን ለይተው፣ አርመውና አስተካክለው ቢሠሩ ኖሮ ኢትዮጵያ የፍትሕ አምባ በሆነች ነበር፡፡
ከመንግሥት እስከ ግለሰብ ድረስ በአገር ላይ ሁሉም ድርሻ አለው፡፡ የሌላውን ድክመትና ጉድለት በማሳየት በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲያስተካከልና ችግሩን እንዲፈታ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ የሌላውን ስህተት አትጠቁሙ፣ አትታገሉ እያልን አይደለም፡፡ 
ይህ እንዳለ ሆኖ የውስጣችንን ችግርም እንይ፡፡ ‹‹የጥበብ መጀመሪያ›› የራሳችንን ችግር ዓይተንና ለይተን ድክመታችንንና ስህተታችንን አውቀን በተግባር በማረም የራስን ድርሻ መወጣት ተገቢ ነው፡፡ 
መንግሥት የድርሻውን ሚና የሚጫወተው ከድክመት ተላቆ ሲጠናከር ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርሻቸውን የሚጫወቱት ከድክመት ተላቀው ሲጠናከሩ ነው፡፡ የግል ዘርፉ በአገር ጉዳይ ልዩ ሚና መጫወት የሚችለው የራሱን ድክመት ዓይቶ ተጠናክሮ ሲሠራ ነው፡፡ የፍትሕ አካላት ለሕገ መንግሥት ተገዥ ሆነው ፍትሕ እንዳይጣስ የሚያደርጉት ከድክመት ተላቀው ሲጠናከሩ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን የሕዝብ አገልጋይ የሚሆኑት ድክመታቸውን አውቀውና አርመው ሲስተካከሉ ነው፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ የድርሻውን ሚና የሚጫወተው ከድክመት ተላቆ ሲጠናከር ነው፡፡
ሁላችንም ለአገራችንና ለሕዝባችን የመሥራት ግዴታ አለብን፡፡ በላቀ ደረጃ ለመሥራትና ሕዝብን ለማገልገል ራሳችንን እናጠናክር፡፡ ራሳችንን በማጠናከር ስህተታችንና ድክመታችንን እናርም፡፡ 
በዚህ መንፈስ ስንነሳ ነው ዕድገት፣ ልማት፣ ዲሞክራሲና ፍትሕ የሚሰፍነው፡፡ ሁላችንም ድክመታችንንና ጉድለታችንን አውቀን፣ አርመንና ተጠናክረን ብንሠራ ኢትዮጵያችን የትና የት ትደርስ ነበር? ይህንን በተግባር ካዋልነው አገራችን ካሰብነው ቦታ ትደርሳለች!   http://www.ethiopianreporter.com/index.php/editorial/item/3073-%E1%88%81%E1%88%8B%E1%89%BD%E1%8A%95%E1%88%9D-%E1%8C%89%E1%8B%B5%E1%88%88%E1%89%B3%E1%89%BD%E1%8A%95%E1%8A%95-%E1%8A%A0%E1%8B%8D%E1%89%80%E1%8A%95-%E1%89%A5%E1%8A%93%E1%88%B5%E1%89%B0%E1%8A%AB%E1%8A%AD%E1%88%8D-%E1%8A%96%E1%88%AE-%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB%E1%89%BD%E1%8A%95-%E1%8B%A8%E1%89%B5%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%89%B5-%E1%89%A0%E1%8B%B0%E1%88%A8%E1%88%B0%E1%89%BD-%E1%8A%90%E1%89%A0%E1%88%AD?

Comments

Popular posts from this blog

Israel Eshetu back to his childhood club

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት