ቀጣዩ ፕሬዚዳንት ማን ይሆኑ?
ኢትዮጵያን ላለፉት 12 ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የነበሩት ሁለተኛው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የሥራ ዘመናቸው በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡
በመሆኑም ከአንድ በኋላ ወር በመስከረም 2006 ዓ.ም. ማጠናቀቂያ አካባቢ ሦስተኛው ፕሬዚዳንት ይሰየማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሦስተኛው ፕሬዚዳንት ማን ሊሆኑ ይችላሉ? ወይም ይገመታሉ? ለሚሉ ጥያቄዎች የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ግምታቸውንና በመረጣ ወቅት ምን መደረግ እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ገዥው
ፓርቲ ኢሕአዴግ ሦስተኛውን ፕሬዚዳንት በሚቀጥለው ወር ይፋ ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል የፕሬዚዳንትነቱ የሥራ ኃላፊነት ያን ያህል ትርጉም ስለሌለው እንደማያስጨንቃቸው የሚናገሩም አሉ፡፡ የመጀመሪያው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በ1987 ዓ.ም. በተደረገው የፓርላማ ምርጫ ተወዳድረው ከተመረጡ በኋላ፣ በወቅቱ የአመራር አባል የነበሩበት ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በደረሱበት ውሳኔ መሠረት ፕሬዚዳንትነታቸው በፓርላማ ፀድቆ፣ እስከ 1993 ዓ.ም. ድረስ ከኢሕአዴግ ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስከሚለያዩ ድረስ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ቆይተዋል፡፡
ከእሳቸው በመቀጠል በቅርቡ የሚሰናበቱት አቶ ግርማ ላለፉት አሥራ ሁለት ዓመታት ቆይታ አድርገዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት አንድ ፕሬዚዳንት ከዚህ በላይ ስለማይቆይ በአዲሱ ዓመት ሦስተኛው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ይሰየማሉ፡፡ ምንም እንኳ ኢሕአዴግ ቀደም ብሎ ለሕዝቡ የማሳወቅ ባህል ባይኖረውም፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ የተለያዩ ግለሰቦች ስሞች እየተነሱ ናቸው፡፡ ለፕሬዚዳንትነት በዕጩነት ስማቸው የሚነሱ ግለሰቦችንና የተሰጡ አስተያየቶችን የያዘው ዝርዝር ዘገባ ለመመልከት እዚህ ይጫኑ፡፡
በመሀል አዲስ አበባ ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ በሚወስደው ዳግማዊ ምኒልክ ጎዳና የሚጓዝ ሰው የተንጣለለውን ብሔራዊ [ኢዮቤልዮ] ቤተ መንግሥት ያገኛል፡፡
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የቀድሞውን ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ለቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ወይም ለአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስጦታ ከማስረከባቸው በፊት 25ኛ የብር ኢዮቤልዩ በዓል ሲመታቸውን ሲያከብሩ ያሠሩት ይህ ቤተ መንግሥት ዘመን ተሻጋሪ ውብ የአርክቴክቸር ጥበብ የተንፀባረቀበት ነው፡፡ በ1948 ዓ.ም. የተመረቀው ይህ ውብ ቤተ መንግሥት ሁሉም ነገር የተሟላለት የሚባልለት ነው፡፡
ግዮን ሆቴልንና የፍል ውኃ አስተዳደርን ተዋስኖ ከእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ከፍ ብሎ አሥር ሔክታር በሚጠጋ መሬት ላይ የተገነባው ይህ ቤተ መንግሥት በአገር በቀል ዛፎችና አንበሳን ጨምሮ በተለያዩ የዱር እንስሳት የተሞላና የተዋበ ነው፡፡ የቤተ መንግሥቱ ውስጣዊ ክፍልም እንዲሁ በተለያዩ ውብና ውድ ዕቃዎችና ጌጣጌጦች የተዋበ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በግሪኩ የኮንስትራክሽን ኩባንያ ማሪያሌዝ የተገነባው ቤተ መንግሥት ባለፉት ስድስት አሥርት ዓመታት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ለሥራና ለመኖሪያ ተስተናግደውበታል፡፡ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ አራት ኪሎ ታላቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ በተሠራላቸው ቤት መኖራቸው አይዘነጋም፡፡ ለአንዳንድ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር ብዙም አልተገለገሉበትም፡፡ ንጉሡ በብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ ከተመራው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥትን ለቀው ከ1954 ዓ.ም. ጀምሮ ለ13 ዓመታት እስከ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ድረስ በዚህ ቤተ መንግሥት ውስጥ ኖረዋል፡፡ በኋላም ወታደራዊው መንግሥት ንጉሡን ከሥልጣን አስወርዶ ይህንን ቤተ መንግሥት ተረክቧል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ የሚመራው ደርግ ይህንን ቤተ መንግሥት ኦፊሴላዊ ዝግጅቶችን ለማካሄድና እንግዶችን ለመቀበል ተጠቅሞበታል፡፡
አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኙትና በሁለት ዙር 12 ዓመታት በዚህ ቤተ መንግሥት ውስጥ የኖሩት አቶ ግርማ የሥራ ዘመን በ2005 ዓ.ም. የሚያበቃ በመሆኑ፣ ይህ ውብና በውድ ዕቃዎች የተንቆጠቆጠ ቤተ መንግሥት አዲስ ሰው ይቀበላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኢሕአዴግ አመራሮች መሰንበቻውን ፕሬዚዳንት ግርማን በቀጣይነት ማን ይተካ በሚለው ጉዳይ መጠመዳቸው ይነገራል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 70 ላይ የፕሬዚዳንቱ የሥራ ዘመን ስድስት ዓመት ይሆናል ይላል፡፡ አንድ ሰው ከሁለት ጊዜ በላይ ለፕሬዚዳንትነት ሊመረጥ አይችልም በማለት ይደነግጋል፡፡
ፕሬዚዳንት ግርማ ለ12 ዓመታት የሠሩ በመሆናቸው ሁለተኛው የሥራ ዘመናቸው በ2005 ዓ.ም. መጨረሻ ያበቃል፡፡ በዚህ መሠረት ገዥው ፓርቲ ቀጣዩ ፕሬዚዳንትን ለፓርላማው ለማቅረብ የተለያዩ ሰዎችን ሰብዕና እያጠና መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በእስካሁኑ ሒደት በኢሕአዴግ ካምፕና በማኅበረሰቡ ዘንድ ቀጣይ ፕሬዚዳንት ይሆናሉ እየተባሉ ስማቸው ከሚነሳው መካከል የአዲስ አበባ ከተማ ባላደራ አስተዳደር ከንቲባ የነበሩት አቶ ብርሃነ ደሬሳ፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና፣ ቀድሞ በፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የመንግሥት ቃል አቀባይ የነበሩት ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ፣ በፓርላማ ብቸኛው የግል ተመራጭ ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሊቀመንበር ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን፣ ታዋቂው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉና በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ይገኙበታል፡፡ ምንም እንኳ ያን ያህል የጎላ ባይሆንም የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግርማ ዋቄ ይጠቀሳሉ፡፡
በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚሰበሰቡበት ጊዜ ኢትዮጵያን በርዕሰ ብሔርነት የሚወክለው ሰው ከላይ ከተጠቀሱት ወይም ካልተጠቀሱ ሰዎች መካከል ይሰየማል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ የተመረጠው ፕሬዚዳንትም፣ ‹‹እኔ … በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት በመሆን ሥራዬን ስጀምር የተጣለብኝን ከፍተኛ ኃላፊነት በታማኝነት ለመፈጸም ቃል እገባለሁ፤›› በሚለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ቃል በመግባት በንጉሡ ዘመን የተገነባው ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ይገባል፡፡
በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለፕሬዚዳንትነት ዕጩ የሚያቀርበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ የቀረበው ዕጩ በምክር ቤቱና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ከተደገፈ ፕሬዚዳንት ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ሆኖ የሚመረጠው ሰው በሕገ መንግሥቱ ሰባት ሥልጣኖች ተሰጥተውታል፡፡ የተሰጡት ሥልጣኖች የሁለቱን ምክር ቤቶች የጋራ ዓመታዊ ስብሰባ መክፈት፣ ፓርላማው ያፀደቃቸውን ሕጎችና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በነጋሪት ጋዜጣ ማወጅ፣ አገሪቷን በውጭ አገሮች የሚወክሉትን አምባሳደሮችና ሌሎች መልዕክተኞች በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት መሾም፣ የውጭ አገር አምባሳደሮችንና የልዩ መልዕክተኞችን የሹመት ደብዳቤ መቀበል፣ በሕጉ መሠረት ኒሻኖችንና ሽልማቶችን መስጠት፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕግ በተወሰነው መሠረት ከፍተኛ የውትድርና ማዕረጐችን መስጠትና በሕጉ መሠረት ይቅርታ ማድረግ የሚሉት ናቸው፡፡
የአገሪቱ ምልክት ሆኖ ለቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት እነዚህን ተግባራት የሚያከናውነው ሰው ማነው? የሚለው ጥያቄ በእስካሁኑ ሒደት ባይለይም ገዥው ፓርቲ ማማረጡን ቀጥሏል፡፡ ቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ማን ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማነጋገር የዳሰሳ ዘገባ ተዘጋጅቷል፡፡
ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሦስት ተመሳሳይና መሠረታዊ ጥያቄዎችን በማቅረብ የኅብረተሰቡን የልብ ትርታ ለማወቅ ሙከራ ተደርጓል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ቀጣይ ፕሬዚዳንት ማን ሊሆን ይችላል? ፕሬዚዳንቱ ማን ቢሆን ፍላጎታችሁ ነው? እና ለሰጡት አስተያየት ምክንያታቸውን መጠየቅ ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት የተወሰኑ አስተያየት ሰጪዎች የሚሉት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ታዋቂው ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ ሞላ ዘገዬ በቀጣይ የሚመረጠው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ማን መሆን እንዳለበትና መስፈርቱን በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ አስተያየታቸው ሲሰጡ፣ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት እከሌ ይሁን ተብሎ በቀላሉ የሚሰየም ወይም የሚጠቆም መሆን የለበትም ይላሉ፡፡ ከፖለቲካ ነፃና ለአገር ተቆርቋሪ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተመርጠው ከተመካከሩና በደንብ ካሰቡበት በኋላ ‹‹እከሌ ይሁን›› ማለት እንዳለባቸው አቶ ሞላ ገልጸዋል፡፡
ቀጣዩ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያከብረው መሆን እንዳለበት የሚናገሩት አቶ ሞላ፣ እሳቸው ‹‹እከሌ ቢሆን ይሻላል›› የሚሉት ለጊዜው ባይኖራቸውም መሆን ያለበት ግን፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህል፣ ታሪክና ወግ ጠንቅቆ የሚረዳ፣ የተለያዩ ሃይማኖቶችን የሚከተሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተቻችለው፣ ተከባብረውና ተረዳድተው የሚኖሩ መሆናቸውን ተቀብሎ ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በሕገ መንግሥቱ ለፕሬዚዳንቱ የተሰጠው ሥልጣን የረባ ባይሆንም የመምከር፣ የማስታረቅ ማለትም አንዳንድ የተካረሩ የፖለቲካና የሃይማኖት ግጭቶች በሚከሰቱበት ወቅት፣ የሚያስከትለውን ውጤት ተገንዝቦ ጣልቃ በመግባት ‹‹አንተም ተው አንተም ተው›› የሚልና ተደማጭነት ያለው ፕሬዚዳንት ቢመረጥ፣ የእሳቸውም ሆነ የኅብረተሰቡ ፍላጐት እንደሚሆን አቶ ሞላ አስረድተዋል፡፡
ቀጣዩ ፕሬዚዳንት በዕውቀትና በሕይወት ተሞክሮ ከፍተኛ ልምድ ያለው ሆኖ ዕድሜው ከ55 እስከ 60 ዓመት መሆን እንዳለበትና በማንኛውም ብሔር ብሔረሰብ የሚከበር ሰው ቢሆን በማለት አቶ ሞላ ፍላጐታቸውን ተናግረዋል፡፡ ተመራጩ ፕሬዚዳንት የሚኖረው ልምድ ወይም ተሞክሮ በትምህርት፣ በመንግሥት ሠራተኛነቱ፣ በግል ሥራው ወይም በሌላ ነገር ቢሆን ችግር የለውም፡፡ ‹‹ለሚመረጠው ፕሬዚዳንት ትልቁ ሕጋዊ ነገር ሞራል ነው፡፡ ደፋርና አገሩን የሚወድ መሆን አለበት፡፡ ታሪክ የሠራ መሆን አለበት፡፡ ከፖለቲካ ፍላጐት በላይ መሆን አለበት፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
‹‹በፓርላሜንታዊ ሥርዓት ለፕሬዚዳንት የሚሰጠው ሥልጣን እዚህ ግባ የማይባል ቢሆንም ሰውዬው ግን ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥ ያላቸው ሥልጣን አንድ ነው፡፡ የመማከር (The Right to be Consulted) ሥልጣን ሲባል በመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ ላይ ጣልቃ መግባት ሳይሆን፣ ከፍተኛ የሆኑ ወሳኝ የአገር ጉዳዮች ማለትም ለጦርነት በር የሚከፍቱ ጉዳዮች ሲኖሩ፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ጥላቻ የሚፈጥሩ ነገሮች ሲከሰቱ፣ በዘርና በሃይማኖት ምክንያት የሚነሱ ችግሮች ሲፈጠሩ፣ መንግሥት ዕርምጃ ከመውሰዱ በፊት ፕሬዚዳንቱን ማማከር አለበት፤›› ሲሉ አቶ ሞላ አስረድተዋል፡፡
‹‹እኛ እኮ ሽማግሌ አጣን፤ መንግሥት ዘንድ አማላጅ የሚላክ ማን አለ? ቀደም ባሉት ዘመናት ነገሥታትን የሚያማልዱ ትልልቅ የአገር ሽማግሌዎች ነበሩ፡፡ ሌሎች ሲፈሯቸው የአገር ሽማግሌዎች ይደፍራቸውና ያማክሯቸው ነበር፤›› የሚሉት አቶ ሞላ፣ ‹‹አሁንም ኢትዮጵያ እነዚህ ሰዎች ስላሏት ፕሬዚዳንቱ ይኼንን ሚና የሚወጣ መሆን አለበት፡፡ ፕሬዚዳንቱን ጠቅላይ ማኒስትሩና ካቢኔው በማንኛውም የአገር ጉዳይ ላይ ሊያማክሩት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በርትዕ ሊታዩ የሚገባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ይኼንን የሚሠራ ሰው ያስፈልጋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ‘እከሌ የሚባለው ሚኒስትር ምን ይለኛል?’ በሚል የፖለቲካ ጥገኛ ሳይሆን ብቃት ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን በነፃነት እያማከረ ለአገሩና ለወገኑ ኩራት ሆኖ መሥራት አለበት፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ አሉን፤›› በማለት አቶ ሞላ አብራርተዋል፡፡
የቀድሞው የዕርዳታና ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ሽመልስ አዱኛና የቀድሞ ዲፕሎማት አምባሳደር ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ የአቶ ሞላን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ሁለቱም እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መሆን ያለበት በዕድሜ የበሰለ፣ የቀድሞው ሥራዎቹ ለአገርና ለወገን የጠቀሙ፣ በመንግሥትና በሕዝብ ዘንድ ከበሬታ ያለው፣ አገር ወዳድና ለእውነት የቆመ፣ መንግሥት ሲሳሳት ትክክለኛውን አቅጣጫ ማሳየት የሚችልና በዲፕሎማቲክ ግንኙነትም የተሻለ የሆነ መመረጥ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡
ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ካካፈሉት መካከል አትሌት ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያም ይገኝበታል፡፡ አትሌቱ ቀጣዩ ፕሬዚዳንት የተቸገሩትን ድምፅ የሚሰማና ሥልጣኑን እንደ መተዳደሪያ የማይጠቀምበት ቢሆን ጥሩ ነው ይላል፡፡ ‹‹እኔ ቀጣዩ ፕሬዚዳንት አቶ ኩማ ደመቅሳ ቢሆኑ እመርጣለሁ፡፡ በእኔ ዕይታ እርሳቸው የዓላማ ፅናት ያላቸው ሰው ናቸው፣ ሰላማዊ ናቸው፣ ሕዝባዊ ናቸው፣ አሳቢ ናቸው፤›› በማለት ፕሬዚዳንት ቢሆኑ ምርጫው እንደሆኑ አስረድቷል፡፡ ነገር ግን ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ብዬ የማስባቸው ዶ/ር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስን ነው በማለት ገልጿል፡፡ ይሁንና ፕሬዚዳንት የሚሆነው ሰው ማንም ይሁን ማን ሥራው ሕዝብን ማዕከል የሚያደርግ፣ የግል ጥቅሙን የማያስቀድም፣ መስዋዕትነት የሚከፍል፣ ሥልጣኑን መኖሪያው ወይም መተዳደሪያው የማያደርግ መሆን አለበት ብሎ እንደሚያምን አትሌት ገብረ እግዚአብሔር አስረድቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ እምወድሽ በቀለ በበኩላቸው፣ በግል ተወዳድረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር አሸብር ፕሬዚዳንት ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ይገምታሉ፡፡ ነገር ግን አትሌት ኃይሌ ወደ ፖለቲካው መግባት እንደሚፈልግ በመግለጹ እሱ ቢሆን ግን ደስተኛ እንደሚሆኑ የገለጹት ወ/ሮ እምወድሽ ምክንያታቸውን ሲገልጹ፣ ኃይሌ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስተዋወቀና በስፖርቱ ዓለም ውጤታማ መሆን የቻለ በመሆኑ ፕሬዚዳንት ቢሆን አሁንም ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ፡፡
‹‹ኃይሌ በፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ለዚህች አገር መሥራት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡ ሰዎች ፍላጎታቸውን በግልጽ ሲያስታውቁ ደግሞ ውጤታማ ይሆናሉ ብዬ አምናለሁ፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡
በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የጆርዳና ኪችን አዘጋጅ ወ/ሮ ጆርዳና ከበደ ከወ/ሮ እምወድሽ የተለየ ሐሳብ አላቸው፡፡ ወ/ሮ ጆርዳና ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የሚፈልጉት የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ባለአደራ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብርሃነ ደሬሳን ነው፡፡ ምክንያታቸውም አቶ ብርሃነ የተማሩና ፖለቲካውን በውል የሚረዱ በመሆናቸው የሚል ነው፡፡
የቀድሞ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አሁን የአረና ፓርቲ አመራር አባል ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ የፕሬዚዳንትነት ሹመት ስሜት አይሰጣቸውም፡፡ ‹‹ፕሬዚዳንቱ አምባሳደሮችንና ዲፕሎማቶችን ከመቀበልና ከመሸኘት የዘለለ በአገሪቱ ላይ ለውጥ በሚያመጡ ነገሮች ላይ በመሳተፍ ረገድ ሚና ስለሌለው፣ እገሌ ቢሆን ባይሆን ብዬ የማስብበት ጉዳይ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ፕሬዚዳንት የሆኑ ሰዎች በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን ያህል እንኳ ሚና ኖሯቸው አላየንም፡፡ ስለዚህ ማን ይሁን ወይም ሊሆን ይችላል በሚያስብል ደረጃ የሚያሳስብ ጉዳይ አይደለም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዲፓርትመንት ኃላፊና መምህር ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ፣ ‹‹መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን ከሚወራው ነገር አንፃር ዶ/ር አሸብር ወይም ኃይሌ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ኃይሌ ሩቅ ይመስለኛል፡፡ ዶ/ር አሸብር ግን ፓርላማ ውስጥ ስላሉና ነፃ ነኝ ብለው ተወዳድረው በፓርላማው መቀመጫ አግኝተው ላለፉት ዓመታት እዚያው ስለነበሩ እርሳቸው ሊሆኑ ይችላሉ፤›› ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ዶ/ር ካሳሁን፣ ‹‹ነገር ግን የሚሠራ ሥራ ሲኖር ነው ልምድና ችሎታ ስላለው ከእገሌ ይልቅ እገሌ ይሻላል፣ ወይም እገሌ ይሆናል የምትለው፡፡ ነገር ግን የርዕሰ ብሔሩ ሥራ በጣም በጣም ውስን ወይም አፍአዊ በመሆኑና ያለቀላቸው ጉዳዮች ላይ አሻራውን ማሳረፍ ስለሆነ፣ በሐሳብ ደረጃ ግን የአገሪቱን መልካም ገጽታ ሊያንፀባርቅ ወይም ሊያሳምን የሚችል ሰው ቢሆን ወይም ማኅበራዊ ድርሻ ያለው ቢሆን ይመረጣል፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሥራ አይጠበቅበትም፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ለምሳሌ እዚህ እኔ በማስተምርበት ቦታ ከእገሌ እገሌ ቢሆን ይሻላል ሲባል ጥሩ ማስተማር ይችላል፣ መጽሐፍ ጽፏል፣ ወደፊትም ይጽፋል፣ ተማሪዎቹን በደንብ ያስተናግዳል፣ በሕግ መሠረት ይሠራል… ልትል ትችላለህ፡፡ ስለዚህ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ግን ብዙ ክብደት ያለው ጉዳይ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፖቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዲፓርትመንት መምህር የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን መብሬ በስም እገሌ ነው ብሎ መገመት አይቻልም በማለት ይጀምራሉ፡፡ መገመት የማይቻለው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ ‹‹አንደኛ የኢሕአዴግ መንግሥት አሠራር ለየት ይላል፡፡ የውሳኔ አሰጣጡን በተለያየ ጊዜ ስንመለከት ብዙ ያልተገመቱ ሰዎች ሲመጡ ተመልክተናል፡፡ ለዚህ ቦታና ለዚህ ጉዳይ እገሌ ይሆናል ተብሎ መጨረሻው ሲታይ ግን ሌላ ሰው ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህንን መገመት እንደሚከብድ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይኼን ያህል መረጃዎች ተንሸራሽረው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የበለጠ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ ሰዎች አደባባይ ወጥተው እነሱን በተመለከተ ከሕዝቡ ሐሳብ ሲሰበሰብም አይስተዋልም፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት አሠራርም የሚታይ አይደለም፡፡ መላምቶች ይኖራሉ፡፡ እገሌ ይሆናል በማለት በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን ይኼ ሰው ወይም ይህቺ ሰው ያው ከኢሕአዴግ ውስጥ እንደሚገኙ መታወቁ ነው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
‹‹በዚህ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መገመት የሚቻለው ድርጅቱ ይሆናል ያለውን ሰው ፓርላማው በዚያው መልክ ነው የሚሰይመው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለእኔ ሚዛን የሚደፋው እገሌ የሚለው ሳይሆን ማን እንደሆነ መገመት አለመቻሉ ነው፡፡ ይህን ደግሞ የሥርዓቱ የፖለቲካ ሒደት ከዚህ በፊትም በርከት ባሉ አጋጣሚዎች የታየ በመሆኑ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ሰሞኑን ስማቸው የሚነሱ ግለሰቦች ይሆናሉ ብለው እንደማይገምቱ የሚናገሩት ዶ/ር ሰለሞን፣ ኢሕአዴግ በራሱ መለኪያ ከዚህ በፊትም ሲያደርግ እንደነበረው አሁን ባለው ሁኔታ እገሌ ነው እገሌ ነው ማለት ይከብዳል ይላሉ፡፡ ዞሮ ዞሮ ሥርዓቱ የሚፈልገውና የሚያቀርበው ሰው ስለሚሾም በስም እገሌ ብሎ መገመት አይቻልም ብለዋል፡፡
ገጣሚና ጸሐፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ዕጩዎችን ባለማወቃቸው ቀጣዩ ፕሬዚዳንት ማን ሊሆን ይችላል ብለው መገመት እንደማይችሉ ገልጸው፣ ነገር ግን ሦስት ጉዳዮችን ያሟላ ሰው ቢሆን ምርጫቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
አቶ አያልነህ ባስቀመጧቸው ሦስት ነጥቦች የሚመረጠው ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምን፣ የተማረና የዲሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ በደንብ የገባው ቢሆን እንደሚመርጡ ፍላጎታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም ማን እንደሚሆን መገመት እንደማይችሉና ውሳኔው የኢሕአዴግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር ነጋሶ እንዳሉት በእስካሁኑ ሒደት ፕሬዚዳንት ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ስማቸው እየተሰማ ያሉት አትሌት ኃይሌ፣ ዶ/ር አሸብር፣ ወ/ሮ ሙሉና ፕሮፌሰር መርጋ ናቸው ካሉ በኋላ፣ ከእነዚህ ውስጥ ግን ወ/ሮ ሙሉ ፕሬዚዳንት ቢሆኑ ምርጫቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ምክንያታቸውም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መሆን ያለበት ሰው ጤነኛ የሆነ፣ ዕድሜው በጣም ያልገፋ፣ በትምህርቱ ጥሩ ደረጃ የደረሰ፣ በሕዝብ ዘንድ መልካም ስም ያለውና በስፋት የሚታወቅ ሲሆን ጥሩ ነው በሚል ነው፡፡ በተጨማሪም በአገሪቱ ከሚነገሩ ቋንቋዎች ሁለትና ከዚያ በላይ የሚናገር፣ ከውጭ አገር ቋንቋዎችም ቢያንስ እንግሊዝኛ አቀላጥፎ የሚናገር፣ ሲሆን ዓረብኛና ፈረንሣይኛ ቋንቋዎች የሚችል ይመረጣል ይላሉ፡፡ ‹‹ከዚህ አኳያ ወ/ሮ ሙሉ ብትሆን እመርጣለሁ፤›› ያሉት ዶ/ር ነጋሶ ምክንያታቸውን ሲገልጹ፣ እስካሁን ድረስ በአገሪቱ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያሉት ወንዶች በመሆናቸው ያንን ክፍተት ይሸፍናል፡፡ ‹‹ከአገር ውስጥ ኦሮሚኛና አማርኛ እንደምትናገር አውቃለሁ፡፡ ከውጭ ቋንቋዎችም ጥሩ እንግሊዝኛ የምትናገር ይመስለኛል፡፡ ሴት ከመሆኗ ባሻገር በሕዝቡም በመንግሥትም ዘንድ መልካም ስም አላት፡፡ አንድ ሁለቴ መድረክ ላይ ንግግር ስታደርግ ሰምቼያለሁ፡፡ ጥሩ የሐሳብ አቀራረብ ችሎታ አላት፡፡ ግርማ ሞገስ አላት፡፡ ወጣትም ናት፡፡ ፕሬዚዳንት የሚሆን ሕመምተኛና ያረጀ ሰው መሆን የለበትም፤›› ሲሉ ዶ/ር ነጋሶ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡
የወቅቱ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ ፕሬዚዳንት የሚሆነውን ሰው መገመት እንደማይችሉ ገልጸው፣ ሴቶች ፕሬዚዳንት ቢሆኑ ምርጫቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከወንዶች የሚመረጥ ከሆነ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ቢሆኑ የሚል ሐሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹መንግሥት ሊያደርገው የሚችለው ከቆየው የሥልጣን ክፍፍል ሒደት አንፃር አሁን ፕሬዚዳንት የመሆን ዕድሉ ለኦሮሞ ብሔር ከፍተኛ ነው፡፡ እገሌ ይሆናል ለማለት ግን ክፍተቱ ሰፊ ነው፡፡ ምክንያቱም ከተወካዮች ምክር ቤትና ከየትም ሊሆን ስለሚችል መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ከሴቶች እስካሁን ሥልጣን ላይ አይተን አናውቅም፡፡ በምክር ቤትም ውስጥ ቁጥራቸው ትንሽ ነው፡፡ ተፅዕኖአቸውም በጣም ትንሽ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችና ሚኒስትሮች በሙሉ ማለት ይቻላል ወንዶች ናቸው፡፡ ከወንዶች መሆኑ ካልቀረ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ቢሆኑ ያልኩበት ምክንያት ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ ፖለቲካ ውስጥ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ከብሔር ተዋፅኦም ኦሮሞ ናቸው፡፡ በትምህርትም እጅግ የበሰሉ ኢኮኖሚስት ናቸው፡፡ በበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሠርተዋል፡፡ በአብዛኛው የሚናገሩት በኢዴፓ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ ያ ማለት ግን የፓርቲያቸውን አቋም በሙሉ እንደግፋለን ማለት አይደለም፡፡ እንደ ግለሰብ ግን ለእንደዚህ ዓይነት ቦታ የሚመጥኑ ሰው ናቸው ብዬ አምናለሁ፤›› በማለት አቶ ሙሼ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም አቶ ቡልቻ አሁን ከፓርቲ ፖለቲካ ራሳቸውን ያገለሉ መሆናቸውን አቶ ሙሼ ገልጸው፣ አቋማቸውን ለመግለጽ ያላቸው ድፍረትና ወኔም በጣም ነው ደስ የሚለው በማለት ይገልጿቸዋል፡፡ ‹‹ለኢሕአዴግ እጅግ ጥሩ ነገር ነው የሚሆነው፡፡ ኢሕአዴግ የነበረን ሰው ፕሬዚዳንት ከማድረግ፣ ገለልተኛ የሆነ ሰው እዚህ ቦታ ላይ ቢቀመጥ ለተለየ አስተሳሰብ በር የሚከፍት ነው፡፡ ከጽንፈኝነት የፀዱ ከመሆናቸውም በላይ የበሰለ አስተሳሰብ ስላላቸው ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ተቆርቋሪ ሰው ናቸው፡፡ ብዙ መስዋዕትነት እየከፈሉ የመጡ ሰው ናቸው፤›› በማለት አቶ ሙሼ አቶ ቡልቻን ገልጸዋቸዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሰዎች የተስማሙበት ነጥብ የፕሬዚዳንትነት መንበር ሕዝብንና አገርን የሚወክል ቦታ እንደመሆኑ፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚስማማበት ብሎም ኢትዮጵያን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡ ይህንን ሰው ለመለየት መንግሥት ብቻውን ሳይሆን ራሱን የቻለ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ አፈላላጊ ኮሚቴ እንዲሰይም ፍላጎት ያሳያሉ፡፡ ኮሚቴው የተስማማባቸውን ዕጩ ፕሬዚዳንቶች ገዥው ፓርቲ ተቀብሎ የሚያፀድቅበት ሥርዓት ቢዘረጋ የሚል አስተያየትም አለ፡፡ የተቀሩት አስተያየት ሰጭዎች የፕሬዚዳንት መንበር ያን ያህል ትልቅ ቦታ እንዳልሆነና ፕሬዚዳንት ግርማ ዕድሜ ሰጥቷቸው ቢቀጥሉ ግድ የለንም በማለትም አስተያየት ተሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከቁጥጥሩ ውጭ አፈንግጦ የሚወጣ ሰው በቦታው ላይ ይሾማል ተብሎ እንደማይጠበቅ ይገልጻሉ፡፡ ለምሳሌ እንደ አትሌት ኃይሌ ዓይነት የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት የሚስብ ሰው አያመጣም የሚሉ ተከራካሪዎች አሉ፡፡ ምክንያቱም ኃይሌ የአገር ውሰጥና የውጭ ሚዲያዎችን ትኩረት የሚስብ በመሆኑና ሚዲያዎቹ ጐትጉተው የተሳሳተ ንግግር እንዲያደርግ ሊያደርጉት ስለሚችሉ፣ ኢሕአዴግ ኃይሌን ለመሳሰሉ ሰዎች ፍላጎት አይኖረውም የሚል ትንታኔ የሚያቀርቡም አሉ፡፡
አስተያየታቸውን የተጠየቁ የተለያዩ ግለሰቦች የተለያዩ ስሞችን በመጥራት ፕሬዚዳንት ሊሆኑ ይችላሉ በማለት ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በሌላ በኩል የተለያዩ መመዘኛዎችንና መስፈርቶችን በማስቀመጥ ለፕሬዚዳንትነት የሚመረጡ ሰዎች በተቻለ መጠን አገርንና ሕዝብን የሚወክሉ ቢሆን የተሻለ ነው ብለዋል፡፡ ለዕጩነት የሚቀርቡ ሰዎች በገዥው ፓርቲ ፍላጎት ብቻ ከሚመረጡ የሕዝብ አስተያየት ቢሰጥባቸው በማለት ምክር የሚያቀርቡ አሉ፡፡
የሚያስገርመው ግን ሪፖርተር ካነጋገራቸው በርካታ ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ የፕሬዚዳንትነት ሹመት ግድ እንደማይሰጣቸውና ጉዳዩንም በቅርበት እንደማያውቁት ገልጸዋል፡፡ (ለዚህ ዘገባ የሪፖርተር ጋዜጠኞች አስተዋጽኦ አበርክተዋል)
Comments
Post a Comment