ሲዳማን ጭምሮ በደቡብ ክልል መሬትን ሳያርሱ የማልማት ዘዴ የተሳተፉ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ምርት ማግኘታቸውን አስታወቁ

አዋሳ ሐምሌ 15/2005 በደቡብ ክልል መሬትን ሳያርሱ የማልማት ዘዴ የተሳተፉ አርሶ አደሩች ከፍተኛ ምርት ማግኘታቸውን አስታወቁ፡፡ በአውስትራሊያ መንግስት ድጋፍ በወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ተቋም የሀዋሳ መለስተኛ የበቆሎ ምርምር ማዕከል መሬትን ሳያርሱ የማልማት ምርምር ስራ እያካሄደ ነው። በክልሉ ሀድያ፣ ሲዳማና ጉራጌ ዞኖች በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች ከሁለት ዓመት በፊት በአምስት አርሶ አደሮች የተጀመረው መሬትን ሳያርሱ የማልማት የዕቀባ ግብርና በተያዘው ዓመት በ200 አርሶ አደሮች እየተከናወነ ይገኛል። ትናንት በምስራቅ ባድዋቾ ወረዳ ጨፋ 01 ቀበሌ በተከናወነ የመስክ ቀን ላይ ማሳቸው የተጎበኘላቸውና በምርምሩ የታቀፉ አርሶ አደሮች እንደገለጹት በግብርና ምርምር ተቋሙ በተደረገላቸው ድጋፍ መሬት ሳያርሱ በቆሎና ቦሎቄ በማልማት ቀደም ሲል ከሚያገኙት ምርት ብልጫ ያለው መሰብሰብ ችለዋል። አርሶ አደር ሞላ አመሌና እንደገለጹት በምርምሩ ታቅፈው መሬት ሳያርሱ በማልማታቸው ቀደም ሲል በሄክታር ሲያገኙ ከነበረው ምርት በ50 በመቶ ብልጫ ያለው ምርት ማግኘት እንደቻሉ ገልጸዋል። መሬት ሳያርሱ ለዘር የሚሆን መስመር በማዘጋጀት ብቻ የበቆሎና ቦሎቄ በማሰባጠር ዘርተው ቦሎቄ አንድ ዙር እንደሰበሰቡና በቆሎው እስኪደርስ ድረስ ሁለተኛ ዙር ቦሎቄ ዘርተው ቡቃያው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ሌላው ወጣት አርሶ አደር ደግነት ደሳለኝ በበኩሉ እንዳለው ሳያርሱ በመዝራት ዘዴ አሰባጥሮ በማልማት የመሬቱን ለምነት መጠበቅ እንደሚቻል በተደረገው ምርምር ያገኘውን ዕውቀት መሰረት አድርጎ ወደ ልማቱ መግባቱንና በቆሎ ተሰብስቦ እስኪያልቅ በስሩ ቦሎቄ ሁለት ጊዜ በማምረት የቦሎቄ ዘር በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ችሏል። የቤተሰቡ የእርሻ ማሳ በከፍተኛ ደረጃ በጎርፍ የሚጠቃና ውሃ ይተኛበት ስለነበር ብዙውን ጊዜ ለእርሻ ስራ ሳይውል ይቆይ እንደነበር አስታውሶ በመርምር ማዕከሉ በቀሰመው መሬትን ሳያርሱ የመዝራት ዘዴ ተጠቅሞ ማምረት እንደቻለ ተናግሯል። ቀደም ሲል በቆሎ ብቻውን በመዝራት ሌላ ምርት ማምረት እየቻሉ ባለማምረታቸው መጎዳታቸውን ጠቁሞ በቆሎና ቦሎቄ ለአፈር ለምነት ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጨማሪ አረም እንዳይኖር ማድረግ የሚያስችል በመሆኑ ተጠቃሚነታቸውን እንዳጎላው አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል። ምርምር ማዕከሉ ለአርሶ አደሮቹ በማሳቸው ላይ ከሚያደርግላቸው ሙያዊ ድጋፍና ክትትል በተጨማሪ የበቆሎና ቦሎቄ ምርጥ ዘር ማዳበሪያና ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት የአረም ማጥፊያ ኬሚካል እንዳቀረበላቸው ተናግረዋል። በሀዋሳ የበቆሎ ምርምር መለስተኛ ማዕከል ዳይሬክተርና የምርምር ፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጎሽሜ ሙሉነህ እንደገለጹት በአውስትራሊያ መንግስት በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአምስት ሀገራት ምርምሩ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመው ምርምሩ የቦሎቄና በቆሎን ምርታማነት በማሳደግ በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል ያለመ ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ 12 ወረዳዎች መመረጣቸውንና በደቡብ ክልል በሀድያ፣ ሲዳማና ጉራጌ ዞኖች የሚገኙ የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ፣ የመስቃንና የምስራቅ ባድዋቾ ወረዳዎች ታቅፈው ለአራት ዓመት የሚቆይ ምርምር እየተካሄደ እንደሚገኝና ባለፉት ሶስስት ዓመታት የተገኘው ውጤት አርሶ አደሩን በምርምሩ ለመታቀፍ እንዳነሳሳው ጠቁመዋል። ምርምር ማዕከሉ የቦሎቄና በቆሎ ተረፈ ምርት በማሳው ላይ እንዳለ በማቆየት የአፈር ለምነትን ማምጣት እንደሚቻል በተለያዩ ሀገራት የተገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግ መሬትን ሳያርሱ በማልማት ዘዴ ተግባራዊ ለማድረግ ከሁለት ዓመት በፊት በአንድ ወረዳ የተጀመረውን ሙከራ የማስፋት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። መሬትን ሳያርሱ የማልማት ዘዴ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ የመሬት ለምነታቸው በቀነሰባቸው ደቡብና ሰሜን አሜሪካ፣ አውስትራሊያና ኒውዝላንድ ተግባራዊ ተደርጎ ውጤት ማምጣት በመቻሉ በኢትዮጵያ በደቡብ፣ በኦሮሚያና አማራ ክልል በሚገኙ የአፈር ለምነት በቀነሰባቸው 12 ወረዳዎች ምርምር እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር