ዩኒቨርስቲው 26 አዳዲስ ፕሮግራሞችን ለመክፈት እየሰራ ነው

ሃዋሳ ሐምሌ 8/2005 በድህረና ቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር ለ26 አዲስ ፕሮግራሞች ስርዓተ ትምህርት ቀርጾ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ገለጹ፡፡ በዩኒቨርስቲው የሀዋሳ ግብርና፣ ህከምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተለያየ ሙያ በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ መርሀ ግብር ያሰለጠኗቸውን ከ900 የሚበልጡ ተማሪዎች ትናንት አስመርቀዋል፡፡ የዩኒቨርሰቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ እንደገለጹት በተጠናቀቀው የትምሀርት ዘመን ለ18 አዳዲስ የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ስርዓተ ትምህርት ቀረጻ ተጠናቆ አንዳንዶቹ ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ ከፕሮግራሞቹ መካከል አግሪ ቢዝነስና ቫሊዩ ቼን ማኔጅመንት፣ በባዮቴክኖሎጂ ፣በአግሮ ኢኮሎጂና ሰስቴነብል አግሪካልቸር ይገኙበታል፡፡ በህክምና ትምህርት ቤት ደግሞ በውሰጥ ደዌ፣ በሀጻናት ህክምና፣ በቀዶ ጥገና ፣ በማህጸን ጽንስ ስፔሻሊቲ የስልጠና ፕሮግራም ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ለመክፈት ዝግጅት መደረጉ ተመልክቷል፡፡ በቅድመ ምረቃ በቅርቡ ከተከፈተው የሲዳምኛ ቋንቋ በተጨማሪ ለ7 ፕሮግራሞች ስርዓተ ትምህርት ተቀርጾ በአንዳንዶቹ ተማሪዎችን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ዶክተር ዮሴፍ ጠቁመዋል፡፡ ይህም ዩኒቨርስቲው የቅበላ አቅሙን በመደበኛ ፕሮግራም ብቻ አሁን ያሉትን 17 ሺህ 080 ተማሪዎችን ቁጥር በ2007 ወደ 26 ሺህ ለማድረስ የተያዘው ፕሮግራም አንዱ አካል በመሆኑ ለዚህ ስኬት ከማስፋፊያ ግንባታዎች ባሸገር ቀልጣፋና ዘመናዊ አሰራር መዘርጋታቸውን ገልጠዋል፡፡ የመምህራንን አቅም በማጎልበት ረገድ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ከ400 በላይ መምህራን በሀገር ውስጥና በውጪ የከፍተኛ ትምህርታቸውን እየተማሩ ይገኛል ብለዋል፡፡ በመንግስት የተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ በጥናትና ምርምር ውጤት ለመደገፍ ዩኒቨርሰቲው በማህበረሰብና በባለድርሻ አካላት የተገመገሙ 140 የምርምር ፕሮጀክቶች እያካሄዱ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የገቢ ምንጫቸውን ለማጎልበት መጠነ ሰፊ ስራዎች በየካምፓሶቹ በማከናወን ላይ ሲገኙ በ2005 የበጀት ዓመት ብቻ ገቢያቸውን ወደ 40 ሚሊዮን ብር ማድረስ ተችሏል ብለዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው ስር ከሚገኙት መካከል የሀዋሳ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተለያዩ የጤና ሙያ ዘርፎች 514 ተማሪዎችን በዋናው ግቢ ሲያስመረቅ ከእነዚሀም መካከል 62 በዶክትሬትና 84 በማስተርሰ ደረጃ ያሰለጠኑ መሆናቸውን የኮሌጁ ዲን ዶክተር ዘሪሁን ወልዴ ገልጠዋል፡፡ አንጋፋው የሀዋሳ ግብርና ኮሌጅ ዲን ዶክተር ይብራ በየነ በበኩላቸው በልዩ ልዩ የግብርና ሙያ 288 በመጀመሪያ ዲግሪና 91 በሁለተኛ ዲግሪ አሰልጥነው ለምረቃ ማብቃታቸውን አመልክተው እስካሁን ከ10 ሺህ በላይ የግብርና ባለሙያዎችን በማፍራት ማሰማራታቸውን አብራርተዋል፡፡ ከተመራቂዎች መካከል በከፍተኛ ማዕረግ ከጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቀችውና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ዶክተር ትዝብት አሽኔ ቦጋለ በቀሰመችው የህክምና ሙያ ገጠርን ጨምሮ በየትኛውም ስፍራ ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል የገባችውን ቃል እንደምታከብር ገልጻለች፡፡ በግብርናው ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ በማዕረግ ተመርቃ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው እየሩሳሌም ሲዳ ለዚህ ውጤት ለመብቃት ድጋፍ ላደረጉላት ሁሉ አመስግና የተማረችውን እውቀት በተግባር በመተርጎም ገበሬውን በቅርበት ሆና ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች፡፡ የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ዛሬ፣ ትናንትናና ባለፈው ሳምንት ያስመረቃቸው በአጠቃላይ 4 ሺህ 723 ተማሪዎች ናቸው፡፡ ዩኒቨርሰቲው አምስት ካምፓሶች በአሁኑ ወቅት በመደበኛ፣ በተከታታይና በማታው ፕሮግራም 29 ሺህ 558 ተማሪዎችን እያስተማረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል 6 ሺህ 401 ሴቶች መሆናቸው በምረቃው ስነስርዓት ላይ ተገልጿል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=9706&K=1

Comments

Popular posts from this blog

Israel Eshetu back to his childhood club

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት