በደቡብ ክልል የግብርና ግብይት ማሻሻያ ፕሮግራምን ለማጠናከር እየተሰራ ነው፡፡

አዋሳ ሚያዚያ 21/2005 በደቡብ ክልል ከሰባት ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት የሚካሄደው አርሶ አደሩን ያሳተፈ የግብርና ግብይት ማሻሻያ ፕሮግራምን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን የክልሉ ግብይትና ህብረት ስራ ቢሮ አስታወቀ፡፡ በክልሉ በተጀመረው በዚሁ ፕሮግራም አፈጻጸም ላይ የሚመክር ክልል አቀፍ ጉባኤ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በጉባኤው ላይ እንደገለጹት ለሰባት አመታት የተነደፈው ይኸው ፕሮግራም አርሶ አደሮች በግብርና ግብይት ተጠቃሚ እንዲሆኑና ኑሮቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያደርግ የድህነት ቅነሳ ፕሮግራም አካል ነው፡፡ በኘሮግራሙ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከልም ተቋማዊ የአቅም ግንባታ፣ የገበያ መሰረተ ልማት ማስፋፋትና ለድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ግዥ የሚሆን ብድር ለአርሶ አደሮች ማቅረብ እንደሚገኙበት ገልፀዋል፡፡ ፕሮግራሙ ከተጀመረበት ከ1998 ዓ.ም መጨረሻ አንስቶ እስካሁን በክልሉ 14 ዞኖች በተመረጡ 40 ወረዳዎች በተለያዩ ሰብሎች ጥራት፣ አመራረት፣ የድህረ ምርት አያያዝና ግብይት ላይ ከ3 ሺህ 500 በላይ ባለሙያዎችና የልማት ጣቢያ ሰራተኞች ሰልጥነዋል፡፡ በገበሬ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች አማካኝነትም ከ100 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች እንዲሰለጥኑ መደረጉም አመልክተዋል፡፡ እንዲሁም በገበያ መሰረተ ልማት ማስፋፋት በኩልም በሀዋሳ፣ በዲላ፣ በሶዶና በቦንጋ ከተሞች አራት የቡና ቅምሻና የጨረታ ማዕከላት ግንባታ ተካሄዷል ብለዋል፡፡ የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ በተመለከተም 1ሺህ 512 የእሻት ቡና መፈልፈያና ማድረቂያ፣ የዝንጅብል ማጠቢያና ማድረቂያ፣ በሞተርና በእጅ የሚሰሩ የበቆሎ መፈልፈያ፣ በእንስሳት የሚጎተት ጋሪ ፣ የእንሰት መፋቂያን ጨምሮ ሌሎችን ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን መሰራጨታቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች፣ የአርሶ አደሩን ምርት ጥራትና የምርት ብክነት ለመጠበቅ፣ የጉልበት ጫና ለመቀነስና የገበሬው ምርት እሴት እንዲጨምር እንዲሁም ገቢው እንዲያድግ የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ እነዚህንና ሌሎችንም የፕሮግራሙ ስራዎች አርሶ አደሩን ባሳተፈ መልኩ ለማጠናከር እየሰሩ መሆናቸውንም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ የፕሮግራሙ የእሰካሁኑ አፈጻጸም የሚፈለገውን ያህል አይደለም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ከክልል እስከ ወረዳ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው የመስራት ጉዳይ አነስተኛ መሆን፣ በወቅቱ የብድር ስርጭት አፈጻጸም ሪፖርት አለማድረግ፣ የብድር ገንዘብ ወቅቱን ጠብቆ አለመለቀቅና ለተጠቃሚው በፍጥነት ያለማሰራጨት ፣ ከቴክኖሎጂ አመራረጥ አንጻር እሴት በሚጨምሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ አለማተኮር የሚሉት እንደሚገኙበት በጉባኤው ላይ ተመልክቷል፡፡ በሀዋሳ ከተማ የተጀመረውና ለሶስት ቀናት በሚቆየው የፕሮግራሙ አፈጻጸም የምክክር ጉባኤ ላይ ከክልሉና ከ14ቱም ዞኖች የተወጣጡ የግብይትና የህብረት ስራ መምሪያ ሃላፊዎች፣ የስራ ሂደት አስተባባሪዎች፣ የየዞኑ አሰተዳደር አማካሪዎችና የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ በአፈጻጸም ላይ የታዩትን ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመገምገም ፕሮግራሙን ለማጠናከር የሚያስችሉ የተሻሉ የአፈጻጸም አቅጣጫዎችንና ስልቶችን እንደሚቀይሱም ተመልክቷል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=7529&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር