የአስትሮኖሚና የስፔስ ሳይንስ ዕድገት ለአገር ልማት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው አቶ ደሴ ዳልኬ

አዲስ አበባ መስከረም 28/2005 የአስትሮኖሚና የስፔስ ሳይንስ ዘርፍ ዕድገት ለአገር ልማት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ መንግሥት በዘርፉ በሚከናወኑ ተግባራት ሙሉ ተሳትፎ በማደረግ ላይ እንደሚገኝ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ከተባበሩት መንግስታት አውተር ስፔስ ጉዳዮች ቢሮ እና ከዓለም አቀፉ አስትሮኖሚካል ኀብረት ጋር በመተባበር በአስትሮኖሚና ስፔስ ሳይንስ ላይ የሚያተኩር የአቅም ግንባታ ስልጠና ለሁለተኛ ደረጃ እና ለዩኒቨርሲቲ መምህራን ዛሬ መስጠት ጀመረ።
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አቶ ደሴ ዳልኬ በተወካያቸው በኩል እንደገለጹት በአስትሮኖሚና በስፔስ ሳይንስ መስክ የሚሰጡ ስልጠናዎች ለአገር ልማት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
በአስትሮኖሚና በስፔስ ሳይንስ መስክ የሚከናወኑ ተግባራትና ፕሮጀክቶች ለመደገፍ መንግሥት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው የእንጦጦ አስትሮኖሚካል ኦብዞርቫቶሪና የስፔስ ሳይንስ ምርምር ማዕከልን ለማጠናከር ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
አቶ ደሴ እንዳሉት በአገሪቱ የአስትሮኖሚና የስፔስ ሳይንስ ምርምር ተቋምና ትምህርት ለማጠናከርና በመስኩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከብሔራዊ፣ ከክፍለ አህጉራዊና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በትብብር ይሰራል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ እንዳሉት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምርና ትምህርትን ለማሳደግ የትምህርት ሚኒስቴር ከብሔራዊና ዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት ጋር አብሮ በመስራት ድጋፍ ያደርጋል።
የአስትሮኖሚ ትምህርት በሁለተኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት በማድረግ በአፍሪካ አህጉር ለማስተዋወቅ ከእንጦጦ አስትሮኖሚካል ኦብዞርቫቶሪና ከስፔስ ሳይንስ ምርምር ማዕከል እንዲሁም ከብሔራዊ፣ ዓለም አቀፍ ምርምር ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ውይይት የሚደረግበት መሆኑን አስረድተዋል።
የእንጦጦ አስትሮኖሚካል ኦብዞርቫቶሪ ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ በበኩላቸው ስልጠናው የአስትሮኖሚና የስፔስ ሳይንስ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት ተማሪዎች ወደ ሳይንስ ትምህቶች ፍላጎት እንዲያድርባቸው ለማደረግ ነው ብለዋል።
የእንጦጦ አስትሮኖሚካል ኦብዞርቫቶሪ የምርምር ማዕከልን ከዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት ጋር በማቀነጀት ትልቅ የምርምር ማዕከል ለማድረግ ውይይት የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
በአስትሮኖሚና ስፔስ ሳይንስ ዘርፍ የተጠናከረ የምርምር ማዕከል በአገሪቱ ባለመኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የዶክትሬት ትምህርታቸውን በውጭ ከተከታተሉ በኋላ ወደ አገር ስለማይመለሱ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር ገልጸዋል።
የእንጦጦ አስትሮኖሚካል ኦብዞርቫቶሪ የምርምር ማዕከል በዘርፉ ያለውን የሙያተኛ ችግር ለማስወገድ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ማዕከሉ ለጥናትና ምርምር ዝግጁ መሆኑን በመገለጽ በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት 15 የአስትሮኖሚፊዚክስና ስፔስ ሳይንስ ምሁራን እንደሚመጡም ጠቁመዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1992/93 የመሬት ሳይንስና የአስትሮኖሚ ትምህርት በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ለሳይንስ ተማሪዎች በዲፕሎማ መስጠት የተጀመረ ሲሆን በአሁን ወቅት ከ20 በላይ በሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች የአስትሮኖሚ ፊዚክስ በዲግሪ እየተሰጠ መሆኑን ዶክተር ሰለሞን አስረድተዋል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሳታፊዎቹ የንድፈ ሀሳብና በኮምፒዩተር የተደገፈ የተግባር ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=2724&K=1

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር