አሥራ አምስት የመንግሥት ሆስፒታሎች የልቀት ማዕከል ሊሆኑ ነው


በታደሰ ገብረ ማርያም
በመላ አገሪቱ የሚገኙና በአጠቃላይ የ15 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ የነበሩ 15 ምርጥ የመንግሥት ሆስፒታሎችን ከፍተኛና ጥራት ባለው የሕክምና ቴክኖሎጂ በማደራጀት፣ የልቀት ማዕከል እንዲሆኑ የማድረግ እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ መሆኑ ታወቀ፡፡ እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ አዲስ አበባ ከተማ ለሚገኝ አንድ ምርጥ ሆስፒታል ኤምአርአይ የተባለ ዘመናዊ የሕክምና መሣርያ የቀረበለት መሆኑን፣ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሜዲካል ሰርቪስ ዳይሬክቶሬት ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

ምንጮች በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የትኛውንም የአካል ክፍል ጥራት ባለው ምስል የሚያሳየው የተራቀቀ ቴክኖሎጂ የቀረበውም ለቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ አጠቃላይ ሆስፒታል ነው፡፡ በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ሌሎችም ምርጥ ሆስፒታሎች አቅም በፈቀደ መጠን በየተራ የዚሁ የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ባለቤት የሚሆኑበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተጠቁሟል፡፡

በመላ አገሪቱ ከሚገኙ 119 የመንግሥት ሆስፒታሎች መካከል፣ 15ቱ ብቻ ምርጥ ተብለው ሊለዩ የቻሉት የተለያዩ ደረጃዎች ያሉትና የተገልጋዩን እርካታ ማዕከል ያደረገ መስፈርት በማውጣት መሆኑን ምንጮች ጠቅሰው፣ የመጀመርያው መስፈርት የሆስፒታሎቹን አገልግሎትና የአፈጻጸም ሁኔታን የሚመለከት መሆኑንና በመስፈርቱ 30 ሆስፒታሎች መመረጣቸውን አስረድተዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው መስፈርት ተግባራዊ የሆነው የሰላሳዎቹን ሆስፒታሎች የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥን በአካል ተገኝቶ በማየትና በመገምገም ሲሆን፣ በዚህ ዓይነቱም አካሄድ 15 ሆስፒታሎች የሚፈለገውን ደረጃና መስፈርት አሟልተው በመገኘታቸው፣ ‹‹ምርጥ ሆስፒታሎች›› ተብለው መመረጣቸውን ከምንጮች ማብራሪያ ለመዳት ተችሏል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ትብብር ለጥራት›› በሚል ፕሮጀክት አማካይነት መስፈርቱን በሚገባ ካሟሉት 15 ምርጥ ሆስፒታሎች መካከል አንዱ የአዲስ አበባው የቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲሆን፣ ከኦሮሚያ ክልል ደግሞ የቢሾፍቱ፣ የአዳማ፣ የሻሸመኔ፣ የነቀምቴና የቢሲዲሞ ሆስፒታሎች ናቸው፡፡

በትግራይ ክልል የቅድስት ማርያም አክሱምና የለምለም ካርል፣ በደቡብ ክልል የቀርጫ፣ የጅንካና የቡታጅራ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል የደብረ ብርሃንና ደብረ ታቦር፣ ከድሬዳዋ አስተዳደር ካውንስል የድል ጮራ ሆስፒታሎች ምርጥ መባላቸውን ተናግረዋል፡፡

እያንዳንዳቸው ምርጥ ሆስፒታሎች በአካባቢያቸው ከሚገኙ ከ15 እስከ 20 ከሚሆኑ ሌሎች ሆስፒታሎች ጋር በጥምረት ተሳስረዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ከቅዱስ ጳውሎስ ሪፈራል አጠቃላይ ሆስፒታል ጋር የተሳሰሩት ሌሎች ሆስፒታሎች የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጥምረት (ክላስተር) እንደሚባሉ ነው ምንጮች ያመለከቱት፡፡

በዚህ መንገድ የተሳሰሩት ሆስፒታሎች በየሁለት ወሩ እየተገናኙ ልምድና ተሞክሮ ይለዋወጣሉ፡፡ በጠንካራና ደካማ ጎኖቻቸው ላይ በመወያየት ለድክመቶቻቸው መፍትሔ የሚሆን አቅጣጫ ይቀይሳሉ፡፡ የበሽተኞች ቅብብሎሽም (ሪፈራል) ያለምንም ችግር ያካሂዳሉ ተብሏል፡፡ ይህ ዓይነቱ የሕክምና አካሄድ ለአገሪቱ እንግዳ ቢሆንም፣ ባደጉ አገሮች ዘንድ በሰፊው እየተሠራበት መሆኑን ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡

ከምርጥ ሆስፒታሎች ጋር ትስስር የፈጠሩት ሌሎች ሆስፒታሎች በበጀትና በባለሙያ እጥረት የተነሳ ሁለገብ አገልግሎት ለመስጠት የአቅም ማነስ ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ትስስር ግን ችግሩን በመጠኑም ቢሆን ይቀርፈዋል የሚል እምነት ማሳደሩንም አክለዋል፡፡

የመንግሥት ድጋፍ ሲታከልበት ውጤቱ የበለጠ አመርቂ ሊሆን እንደሚችል ምንጮች ገልጸው፣ ከዚህ ቀደም የፅኑ ሕሙማን ማቆያ (አይሲ) የነበረው በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ አጠቃላይ ሆስፒታል ብቻ እንደነበር፣ አሁን ግን የቅዱስ ጳውሎስ፣ የቢሾፍቱና የደብረ ብርሃን ሆስፒታሎች በቅርቡ ይህ ዓይነቱ ማቆያ እንዲኖራቸው የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ምርጥ ሆስፒታሎቹ በይፋ የታወቁት ወይም የተመረቁት ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ በተከናወነው ሥነ ሥርዓት ሲሆን፣ በዚህም ሥነ ሥርዓት ላይ እያንዳንዳቸው የአንድ ሚሊዮን ብር ሽልማት አግኝተዋል፡፡ ሽልማቱንም የሰጠውና ለሥራቸውም ማንቀሳቀሻ የሚሆን የፋይናንስ ድጋፍ የሚያደርገው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነው፡፡    
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/8297-2012-10-31-07-07-52.html

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር