ሕዝብ ለመንግሥት የቤት ሥራ ሰጥቷል ተግባራዊ ምላሽ ይጠበቃል!


ውል ክፍል መሄድ ሳያስፈልግና ቃለ ጉባዔ መፈራረም ሳይጠይቅ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመንግሥት የቤት ሥራ ሰጥቷል፤ አደራ አቅርቧል፡፡ ተግባራዊ አዎንታዊ ምላሽም ከመንግሥት ይጠብቃል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት የተሰማውን ሐዘን በሚያስገርም፣ በሚያስመካና ታሪካዊ በሆነ ሁኔታ ከልብ ገልጿል፡፡ ታሪክም ለዘለዓለም ሲዘግበው ይኖራል፡፡ በክብር መዝገብ አስፍሮታል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ሐዘኑን ብቻ አይደለም የገለጸው፡፡ የተጀመረውን የልማት ሒደት ዳር ለማድረስም ቃል ገብቷል፡፡ አሁንም በሕገ መንግሥታችን የሰፈሩትን መብቶችና ጥቅሞች እውን ለማድረግና የኢትዮጵያን ራዕይ ዳር ለማድረስ ዝግጁነቱን ገልጿል፡፡ በእንባም፣ በቃላትም፣ በፀሎትም፣ በሠልፍም፡፡ ሕዝብ መንግሥትን ‹‹ምራ እንከተልሃለን›› ብሏል፡፡

አደራውና የቤት ሥራውም ይኼው ነው፡፡ መንግሥት ይህንን የሕዝብ አደራና የቤት ሥራ በተገቢው መንገድ በተግባር ለመመለስ መንቀሳቀስ ይጀምር፡፡

መንግሥት ይህን የሕዝብ አደራና የቤት ሥራ የሚመልሰው እንዴት ነው? ለመመለስስ ይችላል ወይ?

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና መንግሥት ይህን የሕዝብ አደራና የቤት ሥራ በሚገባ ከተገነዘቡትና መመለስ አለበት ብለው ካመኑበት ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ምንም አያዳግታቸውም፡፡ ይቻላል፡፡

ለመመለስ ግን የሚከተሉትን መፈጸም አለባቸው፡፡
1.    ቀጣይነት
ሕገ መንግሥቱን መንግሥትም እንደ መንግሥት ኢሕአዴግም እንደ ገዥ ፓርቲ ያመኑበትና የተቀበሉት ብቻ ሳይሆን፣ እነሱ ሥልጣን ይዘው ባሉበት ጊዜ በራሳቸው ተነሳሽነት እውን የሆነ ነው፡፡ ስለሆነም ለቀጣይነቱ ችግር የለውም፡፡

የአምስት ዓመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድም ባለው መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የታቀደና የፀደቀ ነው፡፡ ለተግባራዊነቱ ችግር የለም፡፡

በሕግም፣ በዕቅድም፣ በሕገ መንግሥትም ቀጣይነቱ እውን እንዳይሆን የሚያደናቅፍ የለም፡፡ በአመራር ብቃት ችግር እንዳይከሰት ብቁ አመራር መፍጠር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ብቁ ሰዎች አሉ፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ብቁ ሰዎች አሉ፡፡ ብቁ ሰዎች በመንግሥት ውስጥ አሉ፡፡ ሥራና ሠሪውን አገናኝቶ መቀጠል ይቻላል፡፡ መቀጠል ያለበት ይቀጥል መተካት ያለበት ይተካ፡፡ ጉዞው ይቀጥል፡፡ ጉዞው ሲቀጥል የሕዝቡም ጥያቄ ምላሽ ያግኝ፡፡ የሕዝብ የቤት ሥራ በተግባር መልስ ይሰጥበት፡፡

2.    ለድክመቶች እርምት፣ ላልተሳኩት ቆራጥነት፣ ድልን ማጎልበት
ሁሉም ነገር ተሳክቷል ማለት አይደለም፡፡ በየትም አገር ሁሉም ነገር አይሳካም፡፡ በኢትዮጵያችን ረዥም የድል ርቀት ብንጓዝም የተዳከሙ ድሎች አሉ፡፡ የተረሱ ትግሎች አሉ፡፡ ቆራጥነት ያጡ የትግል ዘርፎች አሉ፡፡ የፍትሕ መጓደል አለ፡፡ የሙስና መንሰራፋት አለ፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ፡፡

ስለሆነም የሕዝብ አደራና የቤት ሥራ ለመንግሥት ተሰጠ ስንል አንዱና ትልቁ የቤት ሥራም ድክመቶች ይታረሙ ነው፡፡ ያልጎለበተውን ድል አጎልብቱ፣ ጉልበት ያልበገራቸው የትግል ግንባሮች በቆራጥነት ይመሩና ሁሉም ድል በድል ይሁን የሚል ነው፡፡

ገዥው ፓርቲና መንግሥት ለዚህም ትግል ይረባረቡ፡፡ የቤት ሥራቸውን ይሥሩ፤ ድሉ ቀጣይነቱ ይረጋገጥ፤ ያልተሟላው ድልም ትግሉ ተጠናክሮ የተሟላ ይሁን የሚል ነው፡፡ መንግሥት በቆራጥነት ከተንቀሳቀሰ ሁሉንም ድል በድል ማድረግ ይችላል፡፡

3.    ግምገማና ጥራትን ‹‹የጥበብ መጀመርያ›› ማድረግ
ያስመዘገብናቸውን ድሎችና ያቀድናቸውን ዕቅዶች ዳር ለማድረስ ብቁ መንግሥታዊ አመራር ያስፈልጋል፡፡ ብቁ አመራር መስጠት ይችላል ተብሎ የተቀመጠ ግለሰብን፣ ድርጅትን፣ ቡድንን በየጊዜው አፈጻጸማቸውን መከታተል፣ መገምገምና ይበልጥ እየጠነከሩና እየተጠናከሩ እንዲሄዱ ማድረግ የግድ ይላል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ እንደ ኢሕአዴግ በጋራ መገምገምና የጠራና ጠንካራ ድርጅት መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልገዋል፡፡ በመንግሥት በኩል ግምገማ በማካሄድ ጥራትን መጠበቅና መጠናከር የዘወትር ተግባር መሆን አለበት፡፡

እየገመገሙ ማጥራትና ማጠናከር በኢሕአዴግ የሚታወቅ ባህል ቢሆንም፣ ቀስ በቀስ ባህሉ እየተዳከመ መጥቷል፡፡ ይህም ድርጅቱን በመጉዳትና በሙስና በማቆሸሽ የሚፈጥረው አሉታዊ አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም፡፡

ግምገማና የማጥራት ዕርምጃ ከሌለ ተጠያቂነት አይኖርም፡፡ በሽታን ማስወገድ አይኖርም፡፡ ግንኙነት ይላላል፡፡ አንድነት ይዳከማል፡፡

ስለዚህ የሕዝብን አደራና የቤት ሥራ በተገቢው ፍጥነትና ጥንካሬ መልስ ሰጥቶ የልማትና የዲሞክራሲ ጉዞን እውን ለማድረግ ግምገማ ባህል ይሁን፤ ጥራት ዕለታዊ ሥራ ይሁን፤ ተጠያቂነት ዕለታዊ እንቅስቃሴ ይሁን፤ በልማትና በዲሞክራሲ ግምገማ ጥራት የጥበብ መጀመርያ መሆኑ ይታመንበት፡፡

ሕዝቡ አደራውንና የቤት ሥራውን ለመንግሥት ሰጥቷል ስንል ዳር ሆኖ ውጤት ይጠብቃል ማለት አይደለም፡፡ ሕዝብ ራሱም ትግል ውስጥ ገብቶ ቀጣይነት ያለው ልማትና እውን የሆነ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ይፈልጋል፡፡

ሕዝብ የጠራ መንግሥት፣ ፓርቲና ብቁ ተቋማት እንዲኖሩ ይፈልጋል ብቻ ሳይሆን፣ የጠራና ኃላፊነት የሚሰማው የግልና የሲቪል ማኅበረሰብ እንዲኖርም ይፈልጋል፡፡ መፈለግ ብቻ ሳይሆን ይታገላል፤ ለመታገልም ዝግጁ ነው፡፡

አመራር ግን ያስፈልጋል፡፡ ሊመራ የሚችለው ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትና ፓርቲ ስለሆነ አደራውንና የቤት ሥራውን ሰጠ እንጂ፣ ራሱ ታዛቢ ሆኖ ከሩቅ ለማየት ይፈልጋል ማለት አይደለም፡፡

ሕዝብ መንግሥትን ምራኝ ልከተል እያለ ነው፡፡ ሕዝብ ሕዝባዊነቱን እያስመሰከረ ነው፡፡ መሪ ካለ ለመከተል ዝግጁ መሆኑን እያረጋገጠ ነው፡፡ በሚያኮራ መንገድ፡፡

መንግሥትም ሕዝባዊ አደራውን ይወጣ፤ የቤት ሥራውን ይሥራ፡፡ በድል ላይ ተጨማሪ ድል እያስመዘገብን እንጓዝ፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገባው ‹‹የዳር እናደርሰዋለን›› ቃል ተግባር ላይ ይዋል፡፡ መንግሥት አደራውን ተቀብሎ የቤት ሥራውን ከሠራ ይ - ቻ - ላ - ል!!     

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር