ሲዳማን ጨምሮ በደቡብ ክልል በመንገድ ግንባታ ጥሮግራም ከ1ሸህ 200ኪሎ ሜትር በላይ የመኪና መንገድ ተሰራ


አዋሳ ነሐሴ 2/2004 በደቡብ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በገጠር የቀበሌ ተደራሽ የመንገድ ግንባታ ፕሮግራም ከ1ሺህ 200 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ መሰራቱን የክልሉ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ ።
የቢሮ ኃላፊ አቶ ታገሠ ኤርሞ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹትመንገዶች በክልሉ የተለያዩ አቅጣጫዎች የተገነቡት ሀገራዊ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ተከትሎ ደረጃውን በጠበቀና ክረምት ከበጋ በሚያገለግል መልኩ ነዉ ።
የመንገዶቹ ገንባታ የተካሄደዉ ለፕሮግራሙ በተመደበ ከ1ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መሆኑን አስታዉቀዋል ።
የመንገዶቹ መገንባት በክልሉ በከተማና በገጠር ፣ በአምራችና አገልግሎት ሰጪው እንዲሁም በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፎች መካከል የሚኖረውን ትስስር በማጠናከር አርሶና አርብቶ አደሮችን እንዲሁም ሸማቹን ህብረተሰብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስታዉቀዋል ።
በክልሉ እስካሁን 39 በመቶ የገጠር ቀበሌዎችን ክረምት ከበጋ የሚያገናኝ መንገድ መኖሩን አቶ ታገሠ ጠቁመው በያዝነው የበጀት ዓመት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ሽፋኑን ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነዉ ብለዋል ።
የገጠር መንገድ ተደራሽ ፕሮግራሙን ስኬታማ ለማድረግ በተያዘዉ እቅድ ከ5ሺህ 200 ኪሎ ሜትር በላይ የቅየሳ፣ የዲዛይንና ሌሎችም ስራዎች በበጀት ዓመቱ መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
የመንገድ ግንባታዉን ለማፋጠን በተያዘዉ እቅድ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የተለያዩ የግንባታ ማሽነሪዎች በአሁኑ ጊዜ ወደ ተለያዩ የግንባታ ሣይቶች መሠራጨታቸውን አቶ ታገሰ አስታዉቀዋል ።
በክልሉ እተመዘገበ ላለውና በቀጣይነት ይመዘገባል ተብሎ ለሚጠበቀዉ ኢኮኖሚያዊ እድገት መንገድ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ቢሮዉ ፕሮግራሙን ውጤታማ ለማድረግ 780 አባላት ያሏቸውን አነስተኛ የስራ ተቋራጮችን አደራጀቶ በማሰልጠን ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረጉም ተገልጧል ።
የቀበሌ ተደራሽ መንገድ ግንባታ ፕሮግራም ከመንገድ ግንባታዉ አላማው ጎን ለጎን ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ በበጀት ዓመቱ ከ162 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ገልጠዋል ።
የስራ እድሉን ካገኙት መካከልም 50 ሺህ ያህሉ ሴቶች ናቸው ብለዋል፡፡
በክልሉ 14 ዞኖችና አራት ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ 4ሺህ የሚጠጉ ቀበሌዎችን በሚቀጥሉት አራት አመታት ከዋናው መንገድ ጋር ለማገናኘት ከ14ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ እንደሚገነባ አቶ ታገሠ ተናግረዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር