የቡና ዋጋ ወሰን ሙሉ ለሙሉ ተነሳ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቡና መገበያያ  የዋጋ ወሰንን ከትናንት በስቲያ ገበያ መዝጊያ ዋጋ አኳያ ወደ ላይና ወደ ታች የአምስት በመቶ ጭማሪና ቅናሽ እንዲያሳይ በማድረግ ሲያገበያይበት የነበረውን አሠራር ላልተወሰነ ጊዜ ማንሳቱን አስታወቀ፡፡ የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የዋጋውን ወሰን ማንሳት ያስፈለገው በኒውዮርክ ዓለም አቀፍ ገበያ ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ የመጣው የቡና ዋጋ፣ ባለፈው ሐሙስ ዕለት በፓውንድ (ግማሽ ኪሎ ገደማ) አንድ ዶላር ከሰባ አምስት ሳንቲም የሆነ ዝቅተኛ ዋጋ በማስመዝገቡ የዋጋ ወሰኑን ሙሉ ለሙሉ ማንሳት አስፈልጓል፡፡

የዓለም የቡና ዋጋ እስኪስተካከል ድረስ የዋጋ ወሰኑ ሙሉ ለሙሉ ተነስቶ እንደሚቆይ የገለጹት ዶክተር እሌኒ፣ የአገር ውስጥ አቅራቢዎች የቡና ዋጋ መውረዱን የማይቀበሉት ከዚህ ቀደም የተሻለ ዋጋ ለማግኘት አስበው በእጃቸው ያቆዩት ቡና ይበልጥ ዋጋው ሲወርድ ለኪሳራ ስለሚያጋልጣቸው ነው ብለዋል፡፡ ይህም ሆኖ አቅራቢዎች በግድ ሽጡ እንዳልተባሉ ገልጸው፣ ምርቱን በእጃቸው ከማቆየት ይልቅ ግን እንዲህ ያለ ያልታሰበ የዋጋ ማሽቆልቆል እንዳይከሰት በእጃቸው ያለውን ቡና ቶሎ ለገበያ እንዲያቀርቡ መክረዋል፡፡

ከሦስት ወራት በፊት የቡና ዋጋ እስኪጨምር ድረስ ምርቱን በእጃቸው ይዘው ሲጠባበቁ የነበሩ አቅራቢዎች የዋጋው መውረድ እንደጎዳቸው ገልጸው፣ አምና በፓውንድ ሦስት ዶላር ያወጣ የነበረው ቡና ባለፈው ወር ወደ ሁለት ዶላር ሊወርድ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ያላቆመው የዋጋ ማሽቆልቆል ከሁለት ሳምንት በፊት የኒውዮርክ ገበያ ዋጋው ወደ አንድ ዶላር ከዘጠና ሊወርድ መቻሉን፣ ባለፈው ሐሙስ ደግሞ ብሶበት አንድ ዶላር ከሰባ አምስት ሳንቲም ማውጣቱን ይገልጻሉ፡፡ 

በአንፃሩ በምርት ገበያው ባለፈው ሐሙስ የነበረው የአንድ ፓውንድ ዋጋ አንድ ዶላር ከሰማንያ አምስት ሳንቲም በመሆኑ፣ ይህ ዋጋ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል የዋጋ ወሰኑን በማንሳት ከዓለም ገበያ ጋር ማስተካከል አስፈልጓል ብለዋል፡፡ ይህ ዋጋ ገና ቡናው ሳይበጠርና የወደብ ማጓጓዣ ወጪን ሳያካትት እንዲህ በመሰቀሉ የግድ እንዲቀንስ ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ግን የቡና ዋጋ ወሰኑ ከሚነሳ ይልቅ ከፍና ዝቅ የሚልበት መጠን በአሥር በመቶ ወይም ከዚያ በላይ ተደርጎ ሊስተካከል ይገባ እንደነበር የሚገልጹት ቡና አቅራቢዎች፣ የወሰኑ መነሳት የግብይት ፍትሐዊነትን ሊያሳጣ እንደሚችል ስጋት ገብቷቸዋል፡፡

የዋጋው ዝቅተኛ የመሸጫ ወሰን መነሳቱ ማንም እንደፈለገው ዋጋውን ዝቅ አድርጎ በመሸጥ ገበያውን ሊያዛባው እንደሚችል ይናገራሉ፡፡ ይህም ሆኖ አቅራቢዎች የታጠበ ቡና ወደ ምርት ገበያው ይህን ያህል ባለማምጣታቸው ኪሳራ ላይ እንዳልወደቁ ገልጸው፣ ግብይት የተፈጸመባቸው ደረቅና የጫካ ቡናዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ከሳምንት በፊት ዝቅተኛው የቡና መገበያያ ወሰን 12 በመቶ እንዲሆን ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ የምርት ገበያው የቡና ዋጋ ከዓለም ገበያ ጋር ተቀራራቢ ሆኖ በተገኘበት ወቅት መልሶ ወደ አምስት በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጎ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ካለፈው ዓርብ ጀምሮ ሰባት መቶ ብር እንዳወጣ የሚነገርለት ፈረሱላ ቡና ከሳምንት በፊት ወደ 12 በመቶ ዝቅ እንዲል የተደረገውን የግብይት ወሰን ተከትሎ ከአንድ ሺሕ ብር ወደ ዘጠኝ መቶ ብር እንዳወረደው ዶክተር እሌኒ ገልጸው ነበር፡፡   

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር