የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ሽብቁ ማጋኔ በክልሉ ጸረ ሙስና ኮሚሽን በቀረበ ጥያቄ መሰረት ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ተደረገ


የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ትናንት ማምሻውን ተጠናቀቀ
ሃዋሳ, የካቲት 21 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - የደቡብ ክልል ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ከ183 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት በማጽደቅ፣ አራት ዳኞችን ከሀላፊነታቸው በማንሳትና የአንድ የምክር ቤት አባል ያለመከሰስ መብት በማንሳት ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል፡፡
ጉባኤው በትናንት ውሎው ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ በተከናውኑ በትምህርት፣ በመንገድ፣ በጤናና ግብር አሰባሰብ ላይ በመወያየት የስድስት ወራት የክልሉን መንግስት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አጽድቋል።

ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ በቀጣይ በ15 ወረዳዎች ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ፣ በ10 ወረዳዎች አዲስ ለሚጀመሩ ፕሮጀክቶች፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለግብርናና ለክልል ቢሮዎች ለመደበኛና ለካፒታል በጀት ማሟያና ለመጠባበቂያ 183 ሚሊዮን 869 ሺህ 652 ብር ተጨማሪ በጀት አጽድቋል።

ጉባኤው የተሰጣቸውን የዳኝነት ስልጣን ተገን በማድረግ በግለሰቦች ላይ በደል ፈጽመዋል የተባሉትን የአርባምንጭ አካባቢ ጋማ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ስንታየሁ ለማ፣ በጌድዮ ዞን የቡሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ፍላሳ ቡርቃ፣ የቦዲቲ ወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ፋንታ ቤርቦና የከፋ ዞን ጠሎ ወረዳ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ አደመ አርጋጎ ከኃላፊነታቸው በማንሳት ጉዳያቸው በህግ እንዲታይ ወስኗል።

በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ሙሉጌታ አጎን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ ሲሾም 24 አዲስ የወረዳ፣ የዞንና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመት አጽድቋል።

ምክር ቤቱ ትናንት ማምሻውን ሲጠናቀቅ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ሽብቁ ማጋኔ በክልሉ ጸረ ሙስና ኮሚሽን በቀረበ ጥያቄ መሰረት ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የተደረገ ሲሆን ግለሰቡ የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅና ከንቲባ በነበሩበት ወቅት ያለአግባብ ስልጣንን በመገልገልና ከመሬት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ተጠርጣሪ በመሆናቸው ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ተደርጓል።

እንዲሁም ወደ ፌዴራል መስሪያ ቤቶች በዕድገትና በዝውውር በሄዱት የትራንስፖርት፣ የባህል፣ ቱሪዝምና የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊዎች ምትክ አዲስ የቢሮ ኃላፊዎች ሹመት ተሰጥቷል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር