የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዘመናዊ የመስኖ አጠቃቀም ዘዴዎችን ለአርሶ አደሮች እያስተዋወቀ ነው


ሀዋሳ፤ ህዳር 30/2004/ዋኢማ/ - ዘመናዊ የመስኖ አጠቃቀም ዘዴዎችን ለአርሶ አደሩ ለማስተዋወቅ የሚያስችለውን ፕሮጀክት ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው የመስኖ ልማትና ውሃ አጠቃቀም ምህንድስና ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ወሰኑ ለማ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ፕሮጀክቱ ካለፈው ጥቅምት ጀምሮ በደቡብ ክልል በተመረጡ ዝናብ አጠር አካባቢዎች ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።

ዘመናዊ የመስኖ አጠቃቀም ዘዴ ፕሮጀክቱን ለአርሶ አደሩ የማስተዋወቅ ሥራ የሚሰራው ከኢትዮጵያ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር መሆኑ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱ አርሶ አደሩ የጎርፍ ውሃን በማሰባሰብና የከርሰ ምድር ውሃን በቀላሉ በማውጣት ለእርሻ ሥራዎች ሊያውል የሚችልባቸውን ዘዴዎች እንደሚያስተዋውቅ የትምህርት ክፍል ኃላፊው አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ እየተካሄደ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሥሩ ባቋቋማቸው ስድስት የቴክኖሎጂ መንደሮች አማካኝነት መሆኑን የገለፁት ኃላፊው ይህም አርሶ አደሩ በፕሮጀክቱ አማካኝነት በንድፈ ሀሳብና በተግባር የሚሰጡ ሥልጠናዎች በቅርበት ለመከታተል እንደሚያስችለው ተናግረዋል። 

ለሦስት ዓመት የሚቆየው ይኼው ፕሮጀክት በ14 የገበሬዎች የሕብረት ሥራ ማህበራት ሥር የተደራጁ ከ8ሺ በላይ አባወራ አርሶ አደሮችን የመስኖ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ አስረድተዋል። 

ፕሮጀክቱ በዝናብ አጠር አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የመስኖ አማራጮችን ተጠቅመው፤ በዓመት ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ በማምረት በተደጋጋሚ የሚያጋጥማቸው የምግብ እጥረት ለመቅረፍ እንደሚያስችላቸው ኃላፊው አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛ የመማር ማስተማር ሥራዎቹ በተጨማሪ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ችግር ፈቺና የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ የቴክኖሎጂ ትውውቅና የምርምር ሥራዎችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከ23ሺ በላይ ተማሪዎችን በቀን በማታና በተከታታይ ፕሮግራሞች በማስተማር ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በ2004 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ደግሞ ከ5ሺ በላይ አዳዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር መጀመሩን ከኃላፊው ገለጻ ለመረዳት መቻሉን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

Israel Eshetu back to his childhood club

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት