በሃዋሳ ከተማ የተተከለ ዘመናዊ የተሸከርካሪ አካል ብቃት መመርመሪያ ማሽን ስራ ጀመረ



አዋሳ, ታህሳስ 7 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - በደቡብ ክለል ከአምስት ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገዛ ዘመናዊ የተሸከርካሪ ብቃት መመርመሪያ ማሽን በሃዋሳ ከተማ ተተክሎ ስራ መጀመሩን የክልሉ የትራንስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮው የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ የስራ ሂደት ተወካይ አቶ አረጋ አዊቶ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ጉድለት የሚደርሰውን የህይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት ለመቀነስ መሳሪያው ከፍተኛ እሰተዋጽኦ አለው ፡፡
ቢሮው በሃዋሳ ከተማ በትራንስፖርት ዘርፍ ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱ የግል ባላሃብቶች ጋር በመቀናጀት የገዛው የመመርመሪያ ማሽን የተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ አሰጣጥ ስርዓቱን ዘመናዊ በማድረግ በተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ጉድለት ምክንያት የሚደርሰውን አደጋ በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ እንደሚረዳም ጠቁመዋል፡፡
ማሽኑ በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ መተከሉን የጠቆሙት ተወካዩ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ስራ ላይ ውሎ ውጤታማነቱ መረጋገጡን በተደረገው የልምድ ልውውጥ ማወቅ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ከ35ሺህ የሚበልጡ ተሽከርካሪዎች መካከል አብዘኛዎቹ የተሽከርካሪ ምርመራ በተፈለገው መጠን እንደማይደረግ በመታወቁ ማሽኑ መተከሉን ገልጸው በዘርፉ ይከሰት የነበረውን ችግር ከ70 በመቶ በላይ እንደሚቀርፍም አስታውቀዋል፡፡
ቀደም ሲል በእይታ በሚደረግ የቴክኒክ ምርመራ በቀን ከአምስት የማይበልጡ ተሽከርካሪዎች እንደሚስተናገዱ ጠቁመው በማሽን በሚደረገው ምርመራ ግን በቀን እስከ 30 ተሽከርካሪ በመመርመር ብቃት የማረጋገጥ ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ለእንድ ተሽከርካሪ ከአንድ ሰዓት በላይ የሚፈጅ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የእንድ ተሽከርካሪ ሙሉ አካል ምርመራ ከ15 እስከ 30 ደቂቃ ብቻ እንደሚፈጅ አስታውቀዋል፡፡
አገልግሎቱን በክልሉ ሁሉም አከባቢ ተደራሽ በማድረግ ስራው ቀልጣፋ፣ፈጣንና ተጠያቂነት የሰፈነበት እንዲሆን ቢሮው ተንቀሳቃሽ የምርመራ ማሽን ለመጠቀም በተለያዩ ዞኖች በዘርፉ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አቶ አረጋ ተናግረዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

Israel Eshetu back to his childhood club

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት