የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ፕሮግራም በሁለተኛ ድግሪ ደረጃ ሊከፍት ነው


የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ፕሮግራም በሁለተኛ ድግሪ ደረጃ ሊከፍት ነው
አዋሳ, ታህሳስ 13 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በብሄር ብሄረሰቦች ልማት ላይ ያተኮረ የሶሻል አንትሮፖሎጂ የትምህርት ፕሮግራም በሁለተኛ ድግሪ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመክፈት መዘጋጀቱን ገለጸ፡፡
የፕሮግራሙ መከፈት ለሀገሪቱ ህዝቦች ባህልና ቋንቋ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጾኦ እንዳለው የደቡብ ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ ገልጸዋል፡፡

ለፕሮግራሙ የተዘጋጀውን ስርዓተ ትምህርት ለመገምገም ከአሜሪካ የመጡና የሀገር ውስጥ ከፍተኛ ባለሙያዎች ትናንት ለግማሽ ቀን ባካሄዱት አውደ ጥናት ላይ የዩኒቨርሰቲው ፕሬዜደንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ እንደገለጹት አንዳንድ ቋንቋዎችና ባህሎች ሳይታወቁ የሚጠፉበት ሁኔታ እንዳለ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

ፕሮግራሙ ይህንን ችግር ከመቅረፍ ባሻገር የክልሉና የሀገሪቱን ብሄር ብሄረሰበችን ባህል ፣ ቋንቋ ፣ ወግ ፣ ታሪክና ዕድገት በማጥናት ፣ በመንከባከብና በማልማት ጠብቆ ለማቆየት ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ ዋና ከተማ የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመጪው የካቲት 2004 ጀምሮ የሚከፍተው ፕሮግራም በተለይ በደቡብ የሚገኙትን ከ56 በላይ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቋንቋዎች ፣ባህሎች ሀይማኖቶች ፣ወጎችና ታሪካዊ እሴቶች በዘላቂነት ለማልማት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው የክልሉን የሰው ሃይል አቅም ከመገንባት ባሸገር ፖሊሲዎችንና ውሳኔዎችን ለማስተዋወቅ ከክልሉ መንግስትና የብሄረሰቦች ምክር ቤት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው በሁለተኛ ድግሪ ደረጃ የሚከፍተው የሶሻል እንትሮፖሎጂ የትምህርት ፕሮግራም የክልሉና የሀገሪቱ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ያላቸውን ባህላዊና ሌሎችም እሴቶቻቸውን ለማቆየትና ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።

በዩኒቨርስቲው የሶሻል ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ንጉሴ መሸሻ በሁለተኛ ድግሪ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከፈተው ፕሮግራም ቀደም ሲል በመጀመሪያ ድግሪ የነበረውን ተሞክሮ ለማሳደግ ከስርዓተ ትምህርት ባሻገር ከአሜሪካ በመጡ የዘርፉ ፕሮፌሰሮችን ጨምሮ በቂ መምህራን፣ ለመማር ማስተማሩ ስራ የትምህርት ቁሳቁሶና ሌሎችም ዝግጅቶች ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ የትምህርት ደረጃ በቅርቡ እንግሊዘኛን እንደውጪ ቋንቋ የማስተማር የትምህርት ዘርፍ ላይ 16 ተማሪዎችን ተቀብለው ማሰልጠን መጀመራቸውንና ሌሎች 3 ፕሮግራሞች በቅርቡ ለመክፈት ዝግጅት እያጠናቀቁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በአሁኑ ወቅት በሁለተኛና 3ኛ ድግሪ 45 የትምህርት ፕሮግራሞች በመጀመሪያ ድግሪ 60 ፕሮግራሞችን ከ20ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን የዩኒቨርሰቲው ፕሬዜደንት ገልጸዋል፡፡


Comments

Popular posts from this blog

Israel Eshetu back to his childhood club

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት