በሲዳማ ዞን በወንሾ ወረዳ የተሻሻለ የቡና ዝርያ በመሰራጨት ላይ ነው
አዋሳ, ህዳር 26 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - በሲዳማ ዞን በወንሾ ወረዳ ለሚገኙ አርሶ አደሮች በሽታና ድርቅን መቋቋም የሚችሉና የተሻለ ምርት የሚሰጡ የቡና ዝርያዎች በመሰራጨት ላይ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ በቀለ ሁሞ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በወንዶ ገነት ደን ኮሌጅና በጅማ ግብርና ምርምር ተቋም በአዋዳ ማዕከል በምርምር የተገኙ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡና በሽታና ድርቅ መቋቋም የሚችሉ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ሶስት ዓይነት የሲዳማ ስፔሻሊቲ ቡና ዝርያዎች እየተሰራጩ ነው።
በመሰራጨት ላይ የሚገኙት የቡና ዝርያዎች በሁለት አመት ጊዜ ምርት መስጠት የሚችሉና ከነባሩ የቡና ዝርያ ጋር ሲነጻጸር ከ8 እስከ 12 ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት በሄክታር መስጨት የሚችል መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ በመሰራጨት ላይ የሚገኘው የቡና ዝርያ እስካሁን ከስድስት መቶ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች መሰራጨቱንና በሄክታር ከ20 እስከ 25 ኩንታል ምርት መስጠት እንደቻለ አቶ በቀለ ገልጸዋል።
በመጪው ሚያዚያ 2004 ለአርሶ አደሮች የሚሰራጭ ከስድስት መቶ ሺህ በላይ የሲዳማ ስፔሻሊቲ ቡና ችግኝ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ጠቁመው በመንግስት ችግኝ ጣቢያ ብቻ የሚዘጋጀው የቡና ችግኝ በቂ ባለመሆኑ በሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ እንዲባዛ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የቡና ችግኙን በማልማት ላይ ከሚገኙት አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር አፀደ ጎኔሶ እንደገለጹት በምርምር ከተገኘው የቡና ዝርያ ለሙከራ ወስደው ካለሙት 700 ችግኝ ያገኙት ምርት ከፍተኛ በመሆኑ ችግኙን በብዛት ወስደው ለማልማት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
Comments
Post a Comment