የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን የትምህርት ፕሮግራም ከፈተ፤ በአምስት የትምህርት መስኮችም የድህረ ምረቃ ኘሮግራም ሊጀምር ነው

ሃዋሳ, ህዳር 21 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በተያዘው የትምህርት ዘመን የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን የትምህርት ፕሮግራም በመጀመሪያ ዲግሪ መክፈቱን አስታወቀ፡፡ በአምስት የትምህርት መስኮችም የድህረ ምረቃ ኘሮግራም ሊጀምር ነው፡፡
የዩኒቨርሰቲው የማህበረሰብና ሂዩማኒቲ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ንጉሴ መሸሻ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት ዩኒቨርስቲው ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን የትምህርት ፕሮግራም ከ30 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ጀምሯል፡፡
ፕሮግራሙ የተከፈተው ለመማር ማስተማሩ ስራ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች ከተሟሉ በኋላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተለይ ተማሪዎች ከንድፈ ሀሳብ ትምህርት በተጨማሪ በተግባር የተደገፈ ልምምድ የሚያደርጉበት በዩኒቨርስቲው የማህበረሰብ ሬዲዮ እንዲሁም ከደቡብ ክልል መንግስት ጋር በመተባበር የክልሉን ኤፍ ኤም ሬዲዮና ቴሌቭዥን ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ በመፈጠር ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፕሮግራሙ መከፈት ብቃት ያለው የመገናኛና የኮሚኒኬሽን ባለሙያ በጥራት በማፍራት ሀገሪቱ ለተያያዘችው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማነት አስተዋጾኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ከዚህም ሌላ ዩኒቨርስቲው በጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ፣ እንግሊዘኛን እንደ መነጋገሪያ ቋንቋ ማስተማር ፣ የባህልና ዘርፈ ብዙ የቋንቋዎች ጥናት፣ ሶሻል አንትሮፖሎጂ ፣ ማስታወቂያና ህዝብ ግንኙነት የትምህርት መስኮች የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ለዚሁ ኘሮግራም የስርዓተ ትምህርት ቀረጻና ግምገማ፣ የመምህራን ምደባና የመሳሰሉ ዝግጅቶች በማካሄድ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በእያንዳንዱ ፕሮግራምም ከ10 በላይ ተማሪዎችን ተቀብለው እንደሚያሰለጥኑ አስረድተዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

Israel Eshetu back to his childhood club

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት