ቢሮው በ9 ሚሊዮን ብር ወጪ የትምህርት ሥርጭት መቀበያ ዲሾች ግዥና ተከላ አካሄደ

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 6/2004/ዋኢማ/- የደቡብ ክልል በ9 ሚሊዮን ብር የትምህርት ሥርጭት መቀበያ ዲሾች ግዥና ተከላ ማካሄዱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቀው፤ የትምህርት ሥርጭት  መቀበያ ዲሾች ተከላ  የተካሄደው በክልሉ አዲስ ለተከፈቱ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ነው።

በትምህርት ቤቶቹ የሳተላይት ዲሾች ተከላ መካሄድ በፕላዝማ ከማዕከል የሚተላለፉ ትምህርቶችን በጥራት ለማድረስ እንደሚያስችል በቢሮው የመንግሥት ኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ደረሰ ጋቲሶ ገልጸዋል።

በተለይም ተማሪዎች በአካባቢያቸው የማይገኙ የሳይንስ የሙከራ ናሙና ቁሳቁሶችንና ሂደቶቻቸውን በቀላሉ በፕላዝማ አማካኝነት በመመልከትና በመረዳት የትምህርት ክህሎታቸውን ለማዳበር እንደሚያስችላቸው አመልክተዋል።

በተጨማሪም ትምህርት ቤቶቹ በሳተላይት ዲሾቹ አማካኝነት የሚላክላቸውን በንድፈ ሀሳብና በተግባር የተደገፉ የትምህርት ፕሮግራሞችን ለተማሪዎች በማቅረብና ቀልጣፋ የመማር ማስተማር ሂደትን በመፍጠር ለትምህርት ጥራት መጠበቅ ከፍተኛ እገዛ እንደሚኖረው  አስረድተዋል።

የሥርጭት መቀበያ ዲሾቹ ከመደበኛ የትምህርት ሥራዎች ጎን ለጎን መምህራንና ተማሪዎች የሳተላይት ዲሾቹን በመጠቀም የተለያዩ ክልላዊና አገራዊ ኮንፍረንሶችን በቀጥታ ለመሳተፍ እንደሚያስችሏቸው የሥራ ሂደት ባለቤቱ ጠቁመዋል።

ይህም መምህራን ተማሪዎችና ሌሎች የትምህርት ቤቶቹ ማህበረሰቦች ወቅታዊ መረጃዎች በማግኘት ለትምህርት ሥራዎች መጎልበት የበኩላቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርላቸው የሥራ ሂደት ባለቤቱን መግለፃቸውን ጠቅሶ የዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘገባ ያመለክታል።

Comments

Popular posts from this blog

Israel Eshetu back to his childhood club

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት