በሲዳማ ዞን ከ42 ሺህ ቶን የሚበልጥ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ሊቀርብ ነው
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ቡርቃ ቡላሾ እንዳስታወቁት ከዞኑ ለገበያ የሚቀርበውን የቡና ምርት በማሻሻል ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በበጀት ዓመቱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡
በበጀት ዓመቱ 42ሺህ 680 ቶን እሸት ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው ከዚህም ውስጥ 41ሺህ 285 ቶን ያህሉ የታጠበ እሸት ቡና ነው ብለዋል፡፡
ለማዕከላዊ ገበያ የሚቀርበው እሸት ቡና ካለፈው ዓመት በ12ሺህ 682 ቶን ብልጫ እንዳለው ገልጸው ለስራው ስኬት በበጀት ዓመቱ ብቻ 64 ማህበራትና 92 የግል ባለሃብቶች በግብይት እንዲሰማሩ መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
ለቡና ጥራት መበላሸት መነሻ የሆኑ ህገ ወጥ የቡና ዝውውርና ሌሎች ችግሮችን ለመቆጣጠርና ዕቅዱን ለማሳካት በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የሚመራ ግብረ ሃይል በማቋቋም እስከ ቀበሌ ድረስ የቁጥጥር የክትትክልና የድጋፍ ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም 214 ደረጃቸውን የጠበቁ የግብይት ማዕከላት በማቋቋም ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን የመቆጣጠርና ነፃና ፍትሃዊ የገበያ ስርዓት እንዲሰፍን የማድረግ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
ከዞኑ 19 ወረዳ አብዛኛዎቹ ቡና አብቃይ በመሆናቸው ለገበያ የሚቀርበው ቡና ጥራት ለማሻሻል ለማህበራትና አርሶ አደሮች በቡና ጥራት አጠባበቅና ህገ ወጥ ንግድ ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸው አንዳንድ ማህበራት በአዲስ ቴክኖሎጂ የተሰሩ የቡና መፈልፈያ መጠቀም መጀመራቸውን አስታውቀዋል
Comments
Post a Comment