የሀዋሳ ከተማን የመጠጥ ውሃ እጥረት ለማቃለል በ20 ሚሊዮን ብር እየተካሄደ ያለው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ከ90 በመቶ በላይ ተጠናቀቀ

አዲስአበባ፣ታህሳስ12 2003 (ሬዲዮፋና)የሀዋሳ ከተማን የመጠጥ ዉሃ እጥረት ለማቃለል በ20ሚሊዮን ብር 
እየተካሄደ ያለው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ከ90 በመቶ በላይ መጠናቀቁን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ ።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የጥልቅ መጠጥ ዉሃ ግንባታ ለማከናወን የሚያስችል ጥናት
መጠናቀቁም ተገልጧል ።
የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሽብቁ ማጋኔና ሌሎች የካቢኔ አባላት በወንዶ ገነት አካባቢ የሚገኘዉን የመጠጥ
ዉሃ ማስፋፊያ ግንባታ ተዘዋዉረዉ ጎብኝተዋል ።
ከንቲባዉ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በሃዋሳ ከተማ የኢንቨስትመንት መስፋፋትን ተከትሎ 
በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣዉን የመጠጥ ዉሃ ፍላጎት ለማርካት የተለያዩ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸዉ ።
ችግሩን ለማቃለል ከአለም ባንክ በተገኘ 16 ሚሊዮን ብር እና የከተማ አስተዳደር በመደበዉ 
የአራት ሚሊዮን ብር ወጪ የመጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት ስራ ከ90 በመቶ በላይ መከናወኑን አስረድተዋል።
ለከተማዋ ዘላቂ መፍትሄ ለማስገኘት ሃዌላ ወንዶና ጋራ ሊቀታ በተባሉ ስፍራዎች በሰከንድ
ከ200 እስከ 300 ሊትር ዉሃ መስጠት የሚያስችሉ የሁለት ጥልቅ የዉሃ ጉድጓደችን ቆፋሮ ለማካሄድ 
የሚያስችል ጥናት መጠናቀቁን ገልጠዋል ።
በጥናቱ መሰረት ፕሮጀክቱ ለሃያ አመታት ለከተማዋ አስተማማኝ የመጠጥ ዉሀ ለማቅረብ የሚያስችል
መሆኑም ተገልጧል ።
የሃዋሳ ከተማ ዉሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ለጣ የታሞ በበኩላቸዉ 
በወንዶ ገነት አካባቢ በመገንባት ላይ ያለዉ የአምቦ የመጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት በቅርቡ አገልግሎት 
መስጠት ሲጀምር በሰከንድ 55 ሊትር ማምረት እንደሚቻል ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ አማካሪ መሃንዲስ አቶ ታከለ ፍሰሃ በበኩላቸዉ በአሁኑ ወቅት የዋናዉ ምንጭ የማጎልበት 
ስራና የ10 ኪሎ ሜትር የዉሃ መስመር ዝርጋታ መጠናቀቁንና የአንድ ነጥብ ሶስት ኪሎ ሜትር 
መስመር ዝርጋታና ፣ አንድ ሚሊዮን ሊትር ዉሃ የሚይዝ የዉሃ ማጠራቀሚያ ጋን ግንባታ 
በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጠዋል።

Comments

Popular posts from this blog

Israel Eshetu back to his childhood club

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት