ቢ ጂ አይ ቢራ ፋብሪካ በ12 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ መሣሪያ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
አዋሳ, ህዳር 28 ቀን 2004 (ሃዋሳ) - በሀዋሳ ከተማ የሚገኘው ቢ ጂ አይ ቢራ ፋብሪካ በ12 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ መሣሪያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ፡፡ የፋብሪካው ኮርፖሬት ተቆጣጣሪ አቶ በቀለ ሰሙ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ተከላው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው መሣሪያ ፋብሪካው ለቢራ ጠመቃ አገልግሎትና ለጠርሙሰ አጠባ የሚጠቀምበትን ፍሳሽ ከኬሚካል ነጻ በማድረግ በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ብክለት ለመከላከል ያስችላል፡፡ በመሳሪያው አማካይነት ተጣርቶ የሚወጣውን ውሃ በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ለመስኖ አገልግሎት መጠቀም እንደሚችሉ ተናግረዋል። ፋብሪካው የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመገንባት በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአንድ ቢሊዮን ብር ካፒታል ተገንብቶ ባለፈው ግንቦት ወር የሙከራ ስራ የጀመረው ቢ ጂ አይ ቢራ ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት በቀን 363 ሺህ 600 ጠርሙስ ቢራ በማምረት ላይ የሚገኝ መሆኑን ገልፀው ለ273 ሰዎች የስራ እድል መፍጠሩንም አስታውቀዋል፡፡ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምርም የማምረት አቅሙ በእጥፍ እንደሚጨምር አቶ በቀለ ተናግረዋል፡፡ የደቡብ ክልል ንግድ ኢንደስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ሂደት ባለቤት አቶ አበበ ደንጋሞ በበኩላቸው የፍሳሽ ቆሻሻ በአካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ብክለት ለመከላከል ፋብሪካው ያከናወነው ተግባር ለሌሎች ፋብሪካዎች አርአያ ሊሆን እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡