አርሶ አደሩን ከመሬት ተጠቃሚ ለማድረግ የሕግና የአተገባበር ችግሮች እንዲፈቱ ምክረ ሐሳብ ቀረበ
የመሬት ፖሊሲው ለአርሶ አደሩ በመሬቱ የመጠቀም መብት ቢሰጠውም፣ በሕጉም ሆነ በአተገባበሩ ላይ ችግሮች በመኖራቸው አርሶ አደሩ ከመሬቱ የሚገባውን ጥቅም ማግኘት እንዳልቻለ፣ በኦሮሚያ ክልል የተጠና አንድ ጥናት አመለከተ፡፡ ችግሮቹን ቀረፎ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻሉባቸው ምክረ ሐሳቦችም ቀርበዋል፡፡
በመሬት አስተዳደር ላይ የሚስተዋሉ የሕግ፣ የተቋምና የአሠራር ክፍተቶችን ለመሙላት፣ የመፍትሔና የውሳኔ ሐሳብ ማመንጨት ላይ የሚሠራው ላንድ ፎር ላይፍ፣ በኦሮሚያ ክልል መሬት ላይ የተመሠረተ ኢንቨስትመንት ባሉ ዕድሎች፣ ክፍተቶችና ተግዳሮቶች ዙሪያ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጥናታዊ ጽሑፍ ዓርብ የካቲት 19 ቀን 2013 ዓ.ም. አቅርቦ ነበር፡፡
ጥናቱን ያቀረቡት ጥላሁን ግርማ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ የመሬት ጉዳይ በፌዴራል ደረጃ ያልተማከለ ሆኖ ለክልሎች ቢሰምጥም፣ ክልሎች የመሬትን ውሳኔ ጉዳይ ለወረዳ ወይም ለዞን ባለመስጠታቸውና በማዕከል በመያዛቸው በትንሽ መሬት ላይ የሚያርሰው አርሶ አደር ከዕለት ጉርሱ የዘለለ ተጠቃሚ እንዳይሆን አንድ ምክንያት ሆኗል፡፡
አርሶ አደሩ መሬቱን የመጠቀም መብት አለው ብሎ በሕግ ቢቀመጥም፣ ለራሱ ለዕለት ጉርሱ ካልሆነ ከሌሎች ጋር ተቀናጅቶ፣ በራሱ ተነጋግሮና ተደራድሮ ግብርናውንም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ሊያሳድግ ቢፈልግ ሊያሠራ የሚችል መንገድ የለም ብለዋል፡፡
በዳሰሳ ጥናቱ ያሉ ሕጎችና ፖሊሲዎች እንዲሁም ሰነዶች የተዳሰሱ ሲሆን፣ በክልሉ በርካታ ኢንቨስትመንት ያለባቸው አዳማ፣ ቦራ፣ ሎሜ፣ ምሥራቅ ሸዋ፣ ሱሉልታና ፊንፊኔ ዙሪያ ያሉ ወረዳዎች ታይተዋል፡፡
በጥናቱ መሠረት፣ መሬት ላይ የተመሠረተ ኢንቨስትመንት ላይ ያሉት ሕጎች እ.ኤ.አ. በ2005 በአገር ደረጃ ከወጣው የመሬት አስተዳደር ሕግ ጋር ተያይዘው በ2007 ኦሮሚያን ጨምሮ በብዙዎቹ ክልሎች ወጥተዋል፡፡ ነገር ግን በኦሮሚያ ደንብ የወጣው በ2012 ነው፡፡ ከዚህ በኋላ የወጡ አዋጆችና ደንቦችም የመሬትን አጀንዳ እያንዳንዱን በኢንቨስትመንት ሕግ አንዳንዱን በካሳ ሕግ ማካተታቸው ክፍተት ፈጥሯል፡፡
የመሬት አስተዳደር ሕጎች ሲታዩ የ1975ቱ መሬትን ከግል ባለቤትነት አሻሚ ትርጉም ወዳለው የሕዝብ ባለቤትነት ያሸጋገረው ቢሆንም፣ በተግባር የሚታየው የመሬቱ ባለቤት ሕዝቡ ሳይሆን ውሳኔ ሰጪ አካሉ መሆኑንም አጥኚው ዶ/ር ጥላሁን አመልክተዋል፡፡
መሬት ከግል ሀብትነት ወጥቶ የገጠሩም ሆነ የከተማው ሰው ያለው መብት የመጠቀም ብቻ ነው ያሉት ዶ/ር ጥላሁን ለትናንሽ መሬት ባለቤቶች ላልተወሰነ ጊዜ መሬት የመጠቀም መብት፣ የማውረስ፣ የማከራየት መብት ቢሰጥም የራሳቸው ውስንነት አለባቸው ብለዋል፡፡
በ2005 የወጣው ሕግም አርሶ አደሩ እንዴት አድርጎ መሬቱን ለኢንቨስትመንት እንደሚጠቀም ቢያስቀምጥም፣ ጥቅል መሆኑና ግልጽነት ስለሚጎድለው፣ ዝርዝሮች ወደፊት ይወጣሉ ብሎ ስላስቀመጠም ወደ ክልሉ ሲወርድ ከፍተት መፍጠሩ አልቀረም፡፡ በኦሮሚያ ክልል ለአነስተኛ መሬት ባለቤቶች ከፍተኛ ጥበቃ የሚያደርግ ሕግ ቢኖርም፣ ማከራየትን ቢፈቅድም አካሄዱ ኢንቨስትመንት ላይ ያጠነጠነ ባለመሆኑ መሬታቸውን ለዕለት ኑሮዋቸው እየተጠቀሙ እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል ተብሏል፡፡
የትናንሽ መሬት ባለቤቶች መሬታቸውን ለኢንቨስትመንት መጠቀም እንደሚችሉ ቢሰፍርም፣ ዝርዝሩ ወደፊት እንደሚወጣ ተፅፎ ብቻ መቅረቱም የታየ ክፍተት ነው፡፡ በመሆኑም አርሶ አደሩ መሬቱን ለኢንቨስትመንት በማዋል በኩል ብዙም ተጠቃሚ እንዳይሆን አድርጓል፡፡
የመሬት ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ከኢንቨስተሮች ጋር ልዩ ስምምነት አድርገውና አልምተው ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ በሕጉ ቢቀመጥም፣ ይህ ተፈጻሚ አልሆነም፡፡
በ2019 ላይ በኦሮሚያ የመጣው የኢንቨስትመንት ሕግ በ2012 ድፍን የነበሩ ሐሳቦችን ዘርዝሮ ማውጣቱን፣ በዚህም አርሶ አደሮች በራሳቸው መሬት ኢንቨስተር እንዲሆኑ ፈቅዷል ያሉት ዶ/ር ጥላሁን፣ ነገር ግን የኢንቨስትመንት ፈቃድ የሚሰጠው በክልል ደረጃ ሆኖ እያንዳንዱ አርሶ አደር እንደ መደበኛ ኢንቨስተር አስጠንቶ፣ ካፒታል ይዞና በሌሎች መደበኛ የኢንቨስትመንት ሒደቶች አልፎ መሆኑ ክፍተት ያለበትና ሀብት ያላቸው አርሶ አደሮችን እንጂ ሌሎችን የማይጠቅም መሆኑ ታይቷል፡፡
ደሃ ሆኖ ያለው የገቢ ምንጭ መሬቱ ብቻ የሆነችውን አብዛኛው አርሶ አደር ከመሬቱ ሳይነቀል ከባለሀብት ጋር ሆኖ እንዲሠራም ዕድል አልተሰጠውም ብለዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ሕጉም ሆነ የመሬት ደንቡ አርሶ አደሩ ከባለሀብቶች ጋር ሆኖ መሬቱን ሊያለማ የሚችልበትን ዕድል ሰጥቻለሁ ቢሉም፣ ይህ በተግባር እንደሌለና ይህ ዕድል ተሰጥቶ ቢሆን ኖሮ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ሆኖ የአገሪቱን ኢኮኖሚም ያሳድግ ነበር፣ ነገር ግን አርሶ አደሩ በእጁ መሬት ይዞ በድህነት እንዲኖር የተፈረደበት ይመስላል ብለዋል አጥኚው፡፡
አርሶ አደሮች ለልማት ሲፈናቀሉ መልሶ ለማደራጀት የወጣው ሕግ ለተፈናቃዮች የተለያዩ የካሳ ዓይነቶችን ለመስጠት የዘረዘረ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ጥላሁን፣ ሕጉ ይህንን ከማለት ባሻገር አርሶ አደሩ ሳይፈናቀል ቦታው ላይ ሆኖ ሊያለሙ ከሚችሉና ክህሎቱና ሀብቱ ካላቸው ጋር የሚያለማበትን መንገድ ቢያበጅ የተሻለ ይሆን ነበር ብለዋል፡፡ ካሳ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅም አርሶ አደሩ ሳይፈናቀል አብሮ የሚሠራበት ላይ ትኩረት እንዲሰጥም መክረዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ሕጎቹ መልካም ቢመስሉም፣ ኢንቨስት ማድረግ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ የገለጹት አጥኚው፣ የመሬት ባለቤትነት ላይ ካርታ በተሰጣቸው አካባቢዎች ጥሩ ነገሮች እንዳሉ፣ ነገር ግን አርሶ አደሩ ከባለሀብቱ ጋር ተወያይቶ መሥራት እንዲችል የሚያስችል አሠራር እንደሌለ በመሆኑም ሰርተፍኬታቸውን ይዘው መጠቀም የሚችሉበትን አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የትኛውም ቦታ ላይ መሬት ለማግኘት የፖለቲካ ይሁንታን ማግኘት ይጠይቃል፣ የሚወስነውም የፖለቲካ ሥልጣን ያለው አካል ነውና ይህ መፈታት ያለበት ጉዳይ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
በፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች መካከል ያለው ግንኙነት ብዥታ ያለበት በመሆኑ ለሙስና ዳርጓል፣ በመሬቱ ኢንቨስተር እሆናለሁ ያለ አርሶ አደርም ቢኖር ከወረዳ ተነስቶ እስከ ክልል የሚሄድበት አሠራርና ውሳኔ የሚሰጠው በክልል ደረጃ መሆኑ መሠረታዊ ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ጥላሁን፣ አርሶ አደሮች መሬታቸውን ሊያለሙ ሲፈለጉ የሚያለሙበት አግባብ መፈጠር፣ የካሳ ክፍያም ቢሆን ከመሬቱ ከመነሳቱ በፊት ያሉት ሦስት ዓመታት ያገኘው ገቢ ላይ መንተራሱ በየጊዜው ያለውን የዋጋ ግሽበት ያላገናዘበ በመሆኑ ሥሌቱ ባመረተው ምርት ብዛትና ዓይነት አሁናዊ ዋጋ መሰላት አለበት፡፡
ዓለም አቀፍ መመርያዎች ወደ አገር ሕግ ሲመጡ የሰብዓዊ መብት፣ እኩል ተጠቃሚነትና ዘላቂነት የሚሉት የመሬት አጠቃቀም አዋጁ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ነገር ግን ከወረቀቱ ባለፈ በተግባር ደረጃ ይቀራቸዋል፡፡ ይህም ኢንቨስተሩ በአግባቡ ወደ ሥራ እንዳይገባ አብዛኛው የትናንሽ መሬት ባለቤት የሆነው አርሶ አደር ያለውን የመሬት ሀብት እንዳይጠቀምበት አድርጓልም ተብሏል፡፡
በመሆኑም ይህንን የሚቆጣጠርና የሚመራ ተቋም ፈጥሮ አገልግሎት በመስጠትና አገር በማልማት ለውጥ ማምጣት የሚቻልበት ሁኔታ እያለ ሕጉ ላይ ተቀምጦ ወደ ሥራ ባለመተግበሩ አገር እየተጎዳ ነው፣ ይህም ለሕዝብ ብሶት ምክንያት ነውና መሬትን መሠረት ያደረገ ኢንቨስትመንት ላይ ባለሀብቶች የመሬት ባለቤቶች ጋር አብረው የሚሠሩበት እንዲጠናከር፣ ይህንን የሚያመቻች ተቋም እንዲደራጅ፣ አርሶ አደሩ እንዳይፈናቀልና ኢንቨስተሮችም መብታቸው እንዲጠበቅ የሚያደርግ ተቋም እንዲኖር፣ መሬት የመጠቀም መብት ያላቸው አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለመሆን የሚሄዱበትን የተንዛዛ የአሠራር ሰንሰለት ማሳጠር ያስፈልጋል የሚሉት ከተሰጡት ምክረ ሐሳቦች ይገኙበታል፡፡
https://www.ethiopianreporter.com/article/21380
Comments
Post a Comment