ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የ69 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ስምምነት ከሲዳማ ክልል ጋር ተፈራረመ
ሀዋሳ፤ የካቲት 19/2013 (ኢዜአ) ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት አንድ ቢሊዮን 200 ሚሊዮን ብር ለሚያካሄደው የተቀናጀ የልማት ፕሮግራም ከሲዳማና ደቡብ ክልሎች ጋር ስምምነት ተፈራረመ።
በሀዋሳ ከተማ ዛሬ በተካሄደው የፊርማ ሥነ -ሥርዓት ላይ ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያን በመወከል ከሁለቱም ክልሎች ጋር ስምምነቱን የተፈራረሙት የፊልድ ፕሮግራምና ስፖንሰርሺፕ አስተዳደር ዳይሬክተር ወይዘሮ እሌኒ መርጊያ ናቸው።
በደቡብ ክልል ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ለሚካሄደው የልማት ፕሮግራም ስምምነት የተፈራረሙት የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አያሌው ዝና ሲሆን የሲዳማ ክልልን በመወከል ደግሞ የ69 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ስምምነት የተፈራረሙት ደግሞ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አራርሶ ገረመው ናቸው።
በስምምነቱ መሰረት በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና 12 ወረዳዎች ተግባራዊ በሚደረገው ፕሮግራም 2 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ፤በሲዳማ ክልል ሁላ ወረዳ ደግሞ ከ66 ሺህ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ወይዘሮ እሌኒ መርጊያ አስታውቀዋል።
በፕሮግራሙ ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል ፤ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ አካባቢ ጥበቃ ፣ ትምህርት፣ ምግብ ዋስትና፣ የግል ንጽህና አጠባበቅ እና የሕጻናት ጥበቃ የማህበረሰብ ልማት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ዛሬ ከተፈራረሙት ስምምነት በተጨማሪ በሁለቱም ክልሎች በሚገኙ 10 ዞኖችና 54 ወረዳዎች ውስጥ በ2 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር በበጀት የአደጋ ጊዜ ምላሽን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ለማካሄድ መታቀዱን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ባለፉት 20 ዓመታት ወርልድ ቢዥን በሁለቱም ክልሎች የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ከመንግስትና ማህበረሰቡ ጋር በመስራት ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረጉን አውስተዋል።
መንግስት እስካሁን ላደረገው ያላሰለሰ እገዛና ማህበረሰቡ ላሳየው የላቀ ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል።
በስምምነት ፊርማው ሥነ-ሥርዓት የተገኙት የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ በየነ በራሶ ወርልድ ቪዥን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ስራዎችን በአካባቢው ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የአሁኑ ፕሮግራም የተሳካ እንዲሆን የመንግስትና ህዝቡ እገዛና ተሳትፎ እንደሚደረጉ አስታውቀዋል።
የሚመጡ ሃብቶችን በአግባቡ በመጠቀምና ውጤታማ በማድረግ የተጀመሩ የአጋርነት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም እንዲሁ።
የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አያሌው ዝና በፕሮግራሙ ዙሪያ ጊዜ ወስደን የፕሮጀክቱን ተግባራትና ዓላማ ፈትሸንና አስተካክለን ነው የተፈራርም ነው ብለዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፈ ፕሮግራም በመሆኑ ደህነትን ለመቀነስ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ምንጭ፤ ኢዜአ

Comments
Post a Comment