ለገናም ለቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓልም ሀዋሳ ተዘጋጅታለች።
የሀዋሳ ከተማ ትናንት ትታወቅበት የነበረችውን የቱሪዝም፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የመኖሪያ ማዕከልነት በ2012 ይበልጥ ተጠናክሮ ይገኝ ዘንድ በስራ ላይ ነች።
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በመሆን ጅማሬዋን ያቀናችው ሀዋሳ በያዝነው አመት በርካታ ክልላዊ፣ ሀገራዊ እና አለማቀፋዊ ይዘት ያላቸው ሁነቶችን በበቂ ዝግጅት ለማስተናገድ ሙሉ አቅም እና ቁምና ያላትም ሆና ትገኛለች።
በዚህ ረገድ በከተማዋ የሚገኙ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እና ሪዞርቶች ይህን ለሀዋሳ ዘርፈ ብዙ ተመራጭነት ምቹ አጋጣሚ ሆነው ከመገኘት ባሻገር ብቁ የመስተንግዶ ማዕከልነታቸውን በማስመስከር እና እርካታ ያለው አግልግሎት በመስጠትም ጭምር የሚታወቁበት አመት ይሆናል።
ከእነዚህ ማሳያዎች መካከል አንዱ የሆነው የሀዋሳ ከተማን ሁለገብ የንግድ እንቅስቃሴን የሚያመላክተው የገና በዓል ንግድ እና ባዛር ዝግጅት ይገኝበታል።
ይህ እስከ በዓሉ ዋዜማ ሸማቹ የከተማዋ ነዋሪ እና የአጎራባች አካባቢ ህዝብ ከተለያዩ የሀገራችን ቦታዎች ከመጡ የንግዱ ማህበረሰብ ጋር የሚያገናኘው ባዛር በሀዋሳ ከተማ ነጋዴ ሴቶች እና በኤላ ፕሮሞሽን የተዘጋጀ ነው።
ሌላው ታህሳስ 19 ቀን ለሀዋሳ ከተማ ልዩ ድምቀት በመሆን በየአመቱ የሚከበረው የቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል አንዱ ሲሆን ለዚህ ሃይማኖታዊ በዓል ከተማዋ ከምዕመኑ እና ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት ከተለያዩ አካባቢዎች ለሚመጡ እንግዶች ልዩ የንግስ በዓል የቆይታ ጊዜ እንዲኖራቸው አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል።
እኚህ ከወዲሁ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማዋ ሀዋሳ በ2012 ከምታስተናግዳቸው ዝግጅቶች ጥቂቶቹ ሲሆኑ በእያንዳንዱ ቀን፣ ሳምንት እና ወር ደግሞ ከተማዋ ቱሪዝሙን፣ ኢንቨስትመንቱን እና ንግዱን ለላቀ ለውጥ እና ለነዋሪው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የምትተጋበት እንደሆኑ ማመላከት ይችላል።
Comments
Post a Comment